1የዐብድዩ፡ራእይ፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡ስለ፡ኤዶምያስ፡እንዲህ፡ይላል፦ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ወሬ፡ ሰምተናል፤መልእክተኛ፡ወደ፡አሕዛብ፡ተልኮ፦ተነሡ፥በላይዋም፡በሰልፍ፡እንነሣ፡ብሏል።
2እንሆ፥በአሕዛብ፡ዘንድ፡ታናሽ፡አድርጌኻለኹ፤አንተ፡እጅግ፡ተንቀኻል።
3በተሰነጠቀ፡አለት፡ውስጥ፡የምትኖር፥ማደሪያኽንም፡ከፍ፡ከፍ፡ያደረግኽ፥በልብኽም፦ወደ፡ምድር፡ የሚያወርደኝ፡ማን፡ነው፧የምትል፡አንተ፡ሆይ፥የልብኽ፡ትዕቢት፡አታሎ፟ኻል።
4እንደ፡ንስር፡መጥቀኽ፡ብትወጣ፥ቤትኽም፡በከዋክብት፡መካከል፡ቢኾን፥ከዚያ፡አወርድኻለኹ፥ይላል፡ እግዚአብሔር።
5ሌባዎች፡ቢመጡብኽ፡ወይም፡ወንበዴዎች፡በሌሊት፡ቢመጡ፥የሚበቃቸውን፡የሚሰርቁ፡ አይደሉምን፧ወይንንም፡የሚቈርጡ፡ወዳንተ፡ቢመጡ፡ቃርሚያ፡አያስቀሩምን፧
6አንተ፡ግን፡ምንኛ፡ጠፋኽ! ዔሳው፡ምንኛ፡ተመረመረ! የተሸሸገበት፡ነገር፡ምንኛ፡ተፈለገ!
7የተማማልኻቸው፡ሰዎች፡ዅሉ፡ወደ፡ዳርቻኽ፡ሰደዱኽ፤የታመንኻቸው፡ሰዎች፡ አታለሉኽ፥አሸነፉኽም፤በበታችኽም፡አሽክላ፡ዘረጉብኽ፥እነርሱም፡ማስተዋል፡የላቸውም።
8በዚያ፡ቀን፡ከኤዶምያስ፡ጥበበኛዎችን፥ከዔሳውም፡ተራራ፡ማስተዋልን፡አላጠፋምን፧ይላል፡እግዚአብሔር።
9ቴማን፡ሆይ፥ሰዎች፡ዅሉ፡ከዔሳው፡ተራራ፡በመገደል፡ይጠፉ፡ዘንድ፡ኀያላንኽ፡ይደነግጣሉ።
10በወንድምኽ፡በያዕቆብ፡ላይ፡ስለተደረገ፡ግፍ፡ዕፍረት፡ይከድንኻል፥ለዘለዓለምም፡ትጠፋለኽ።
11በፊቱ፡አንጻር፡በቆምኽ፡ቀን፥አሕዛብ፡ጭፍራውን፡በማረኩበት፥እንግዳዎችም፡በበሩ፡ በገቡበት፥በኢየሩሳሌምም፡ዕጣ፡በተጣጣሉበት፡ቀን፡አንተ፡ደግሞ፡ከነርሱ፡እንደ፡አንዱ፡ነበርኽ።
12ነገር፡ግን፥በመከራው፡ቀን፡ወንድምኽን፡ትመለከት፡ዘንድ፥በጥፋታቸውም፡ቀን፡በይሁዳ፡ልጆች፡ላይ፡ ደስ፡ይልኽ፡ዘንድ፥በጭንቀትም፡ቀን፡በትዕቢት፡ትናገር፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ኽም፡ነበር።
13በጥፋታቸውም፡ቀን፡በሕዝቤ፡በር፡ትገባ፡ዘንድ፥በጥፋታቸውም፡ቀን፡መከራቸውን፡ትመለከት፡ ዘንድ፥በጥፋታቸውም፡ቀን፡በሀብታቸው፡ላይ፡እጅኽን፡ትዘረጋ፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ኽም፡ነበር።
14የሸሹትንም፡ለመግደል፡በመንታ፡መንገድ፡ላይ፡ትቆም፡ዘንድ፥በጭንቀትም፡ቀን፡ከርሱ፡የቀሩትን፡ አሳልፈኽ፡ትሰጥ፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ኽም፡ነበር።
15የእግዚአብሔር፡ቀን፡በአሕዛብ፡ዅሉ፡ላይ፡ቀርቧልና፤አንተ፡እንዳደረግኸው፡እንዲሁ፡ ይደረግብኻል፥ፍዳኽም፡በራስኽ፡ላይ፡ይመለሳል።
16በቅዱስ፡ተራራዬ፡ላይ፡እንደ፡ጠጣችኹ፡እንዲሁ፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ዘወትር፡ይጠጣሉ፤አዎን፡ ይጠጣሉ፥ይጨልጡማል፥እንዳልኾኑም፡ይኾናሉ።
17ነገር፡ግን፥በጽዮን፡ተራራ፡ላይ፡የሚያመልጡ፡ይኾናሉ፥ርሱም፡ቅዱስ፡ይኾናል፤የያዕቆብም፡ቤት፡ ሰዎች፡ርስታቸውን፡ይወርሳሉ።
18እግዚአብሔርም፡ተናግሯልና፥የያዕቆብ፡ቤት፡እሳት፥የዮሴፍ፡ቤት፡ነበልባልም፥የዔሳው፡ቤት፡ገለባ፡ ይኾናሉ፤እነርሱንም፡ያቃጥሏቸዋል፡ይበሏቸውማል፤ከዔሳውም፡ቤት፡ቅሬታ፡የለውም። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
19የደቡብም፡ሰዎች፡የዔሳውን፡ተራራ፥የቈላውም፡ሰዎች፡ፍልስጥኤማውያንን፡ይወርሳሉ፤የኤፍሬምንም፡ አገር፡የሰማርያንም፡አገር፡ይወርሳሉ፤ብንያምም፡ገለዓድን፡ይወርሳል።
20ይህም፡የእስራኤል፡ልጆች፡የጭፍራቸው፡ምርኮ፡የከነዓንን፡ስፍራ፡ዅሉ፡እስከ፡ሰራጵታ፡ድረስ፡ ይወርሳል፤በስፋራድም፡የሚኖሩ፡የኢየሩሳሌም፡ምርኮኛዎች፡የደቡብን፡ከተማዎች፡ይወርሳሉ።
21በዔሳውም፡ተራራ፡ላይ፡ይፈርዱ፡ዘንድ፡አዳኞች፡ወደጽዮን፡ተራራ፡ላይ፡ይወጣሉ፤መንግሥቱም፡ ለእግዚአብሔር፡ይኾናል፨ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org