1የአገሩም፡ሰዎች፡የኢዮስያስን፡ልጅ፡ኢዮአክስን፡ወስደው፡በአባቱ፡ፋንታ፡በኢየሩሳሌም፡አነገሡት።
2ኢዮአክስም፡መንገሥ፡በዠመረ፡ጊዜ፡የኻያ፡ሦስት፡ዓመት፡ጕልማሳ፡ነበረ፥በኢየሩሳሌምም፡ሦስት፡ወር፡ ነገሠ።
3የግብጽም፡ንጉሥ፡በኢየሩሳሌም፡ከመንግሥቱ፡አወጣው፥መቶም፡መክሊት፡ብርና፡አንድ፡መክሊት፡ ወርቅ፡ዕዳ፡ጣለበት።
4የግብጽም፡ንጉሥ፡ወንድሙን፡ኤልያቄምን፡በይሁዳና፡በኢየሩሳሌም፡ላይ፡አነገሠ፥ስሙንም፡ኢዮአቄም፡ ብሎ፡ለወጠ፤ኒካዑም፡ወንድሙን፡ኢዮአክስን፡ይዞ፡ወደ፡ግብጽ፡ወሰደው። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
5ኢዮአቄምም፡መንገሥ፡በዠመረ፡ጊዜ፡የኻያ፡ዐምስት፡ዓመት፡ጕልማሳ፡ነበረ፥በኢየሩሳሌምም፡ዐሥራ፡ አንድ፡ዓመት፡ነገሠ፤በአምላኩም፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ክፉ፡አደረገ።
6የባቢሎንም፡ንጉሥ፡ናቡከደነጾር፡በርሱ፡ላይ፡መጥቶ፡ወደ፡ባቢሎን፡ይወስደው፡ዘንድ፡በሰንሰለት፡ አሰረው።
7ናቡከደነጾርም፡ከእግዚአብሔር፡ቤት፡ዕቃ፡ዐያሌውን፡ወደ፡ባቢሎን፡አፈለሰ፥በባቢሎንም፡በመቅደሱ፡ ውስጥ፡አኖረው።
8የቀረውም፡የኢዮአቄም፡ነገር፥ያደረገውም፡ርኵሰት፥በርሱም፡የተገኘው፡ዅሉ፥እንሆ፥በእስራኤልና፡ በይሁዳ፡ነገሥታት፡መጽሐፍ፡ተጽፏል፤ልጁም፡ዮአኪን፡በርሱ፡ፋንታ፡ነገሠ።
9ዮአኪንም፡መንገሥ፡በዠመረ፡ጊዜ፡የዐሥራ፡ስምንት፡ዓመት፡ጕልማሳ፡ነበረ፥በኢየሩሳሌምም፡ሦስት፡ ወርና፡ዐሥር፡ቀን፡ነገሠ፤በእግዚአብሔርም፡ፊት፡ክፉ፡አደረገ።
10ዓመቱ፡ባለፈ፡ጊዜ፡ንጉሡ፡ናቡከደነጾር፡ልኮ፡ወደ፡ባቢሎን፡ወሰደው፥የከበረውንም፡የእግዚአብሔርን፡ ቤት፡ዕቃ፡ከርሱ፡ጋራ፡አስወሰደ፤ወንድሙንም፡ሴዴቅያስን፡በይሁዳና፡በኢየሩሳሌም፡ላይ፡አነገሠ።
11ሴዴቅያስ፡መንገሥ፡በዠመረ፡ጊዜ፡የኻያ፡አንድ፡ዓመት፡ጕልማሳ፡ነበረ፥በኢየሩሳሌምም፡ዐሥራ፡አንድ፡ ዓመት፡ነገሠ።
12በአምላኩም፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ክፉ፡አደረገ፤በእግዚአብሔርም፡አፍ፡በተናገረው፡በነቢዩ፡በኤርምያስ፡ ፊት፡ራሱን፡አላወረደም።
13ደግሞም፡በእግዚአብሔር፡አምሎት፡በነበረው፡በንጉሡ፡በናቡከደነጾር፡ላይ፡ዐመፀ፤ወደእስራኤልም፡ አምላክ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡እንዳይመለስ፡ዐንገቱን፡አደነደነ፡ልቡንም፡አጠነከረ።
14ደግሞም፡የካህናቱ፡አለቃዎች፡ዅሉ፡ሕዝቡም፡እንደ፡አሕዛብ፡ያለ፡ርኵሰት፡ዅሉ፡መተላለፍን፡ አበዙ፤በኢየሩሳሌምም፡የቀደሰውን፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡አረከሱ።
15የአባቶቻቸውም፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ለሕዝቡና፡ለማደሪያው፡ስላዘነ፡ማለዳ፡ተነሥቶ፡በመልእክተኛዎቹ፡ እጅ፡ወደ፡እነርሱ፡ይልክ፡ነበር።
16እነርሱ፡ግን፡የእግዚአብሔር፡ቍጣ፡በሕዝቡ፡ላይ፡እስኪወጣ፡ድረስ፥ፈውስም፡እስከማይገኝላቸው፡ ድረስ፥በእግዚአብሔር፡መልእክተኛዎች፡ይሣለቁ፥ቃሉንም፡ያቃልሉ፥በነቢያቱም፡ላይ፡ያፌዙ፡ነበር።
17ስለዚህም፡የከለዳውያንን፡ንጉሥ፡አመጣባቸው፤ርሱም፡ጕልማሳዎቻቸውን፡በቤተ፡መቅደሱ፡ውስጥ፡ በሰይፍ፡ገደላቸው፤ጕልማሳውንና፡ቈንዦዪቱን፡ሽማግሌውንና፡አሮጌውን፡አልማረም፤ዅሉንም፡በእጁ፡ አሳልፎ፡ሰጠው።
18የእግዚአብሔርንም፡ቤት፡ዕቃ፡ዅሉ፡ታላቁንና፡ታናሹን፥የእግዚአብሔርንም፡ቤት፡መዝገብ፥የንጉሡንና፡ የአለቃዎቹን፡መዝገብ፥እነዚህን፡ዅሉ፡ወደ፡ባቢሎን፡ወሰደ።
19የእግዚአብሔርንም፡ቤት፡አቃጠሉ፥የኢየሩሳሌምንም፡ቅጥር፡አፈረሱ፥አዳራሾቿንም፡በእሳት፡ አቃጠሉ፥መልካሙንም፡ዕቃዋን፡ዅሉ፡አጠፉ።
20ከሰይፍም፡ያመለጡትን፡ወደ፡ባቢሎን፡ማረካቸው፤የፋርስ፡ንጉሥም፡እስኪነግሥ፡ድረስ፡ለንጉሡና፡ ለልጆቹ፡ባሪያዎች፡ኾኑ፤
21በኤርምያስም፡አፍ፡የተነገረው፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡እንዲፈጸም፥ምድሪቱ፡ሰንበትን፡በማድረጓ፡ እስክታርፍ፡ድረስ፤በተፈታችበትም፡ዘመን፡ዅሉ፥ሰባ፡ዓመት፡እስኪፈጸም፡ድረስ፥ሰንበትን፡አገኘች።
22በኤርምያስም፡አፍ፡የተነገረው፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ይፈጸም፡ዘንድ፡በፋርስ፡ንጉሥ፡በቂሮስ፡ በመዠመሪያው፡ዓመት፡እግዚአብሔር፡የፋርስን፡ንጉሥ፡የቂሮስን፡መንፈስ፡አስነሣ፤ርሱም፦የፋርስ፡ንጉሥ፡ ቂሮስ፡እንዲህ፡ይላል፦ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
23የሰማይ፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡የምድርን፡መንግሥታት፡ዅሉ፡ሰጥቶኛል፤በይሁዳም፡ባለችው፡ በኢየሩሳሌም፡ቤት፡እሠራለት፡ዘንድ፡አዞ፟ኛል፤ከሕዝቡ፡ዅሉ፡በእናንተ፡ዘንድ፡ማንም፡ቢኾን፡አምላኩ፡ እግዚአብሔር፡ከርሱ፡ጋራ፡ይኹን፥ርሱም፡ይውጣ፡ብሎ፡በመንግሥቱ፡ዅሉ፡ዐዋጅ፡አስነገረ፥ደግሞም፡ በጽሕፈት፡አደረገው፨ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org