1ኢዮስያስም፡ለእግዚአብሔር፡በኢየሩሳሌም፡ፋሲካ፡አደረገ፤በመዠመሪያውም፡ወር፡በዐሥራ፡አራተኛው፡ ቀን፡ፋሲካውን፡ዐረዱ።
2ካህናቱንም፡በየሥርዐታቸውም፡አቆመ፥በእግዚአብሔርም፡ቤት፡ያገለግሉ፡ዘንድ፡አጸናቸው።
3እስራኤልንም፡ዅሉ፡ያስተምሩ፡ለነበሩት፥ለእግዚአብሔርም፡ለተቀደሱት፡ሌዋውያን፡እንዲህ፡አለ።ቅዱሱን፡ ታቦት፡የእስራኤል፡ንጉሥ፡የዳዊት፡ልጅ፡ሰሎሞን፡በሠራው፡ቤት፡ውስጥ፡አኑሩት፤ከዚህም፡በዃላ፡ በትከሻችኹ፡ላይ፡ሸክም፡አይኾንባችኹም፤አኹንም፡አምላካችኹን፡እግዚአብሔርንና፡ሕዝቡን፡እስራኤልን፡ አገልግሉ፤
4የእስራኤልም፡ንጉሥ፡ዳዊት፡እንደ፡ጻፈው፡ልጁም፡ሰሎሞን፡እንደ፡ጻፈው፡በየሰሞናችኹና፡በያባቶቻችኹ፡ ቤቶች፡ተዘጋጁ፤
5እንደ፡ሕዝቡም፡ልጆች፡እንደ፡ወንድሞቻችኹ፡በያባቶች፡ቤቶች፡ኾናችኹ፡በመቅደሱ፡ ቁሙ፤የሌዋውያንም፡ነገድ፡በየወገናቸው፡እንደ፡ተከፈሉ፡እናንተ፡ተከፈሉ፤ፋሲካውንም፡ዕረዱ፥
6እናንተም፡ተቀደሱ፥እግዚአብሔርም፡በሙሴ፡እጅ፡የተናገረውን፡ቃል፡ያደርጉ፡ዘንድ፡ለወንድሞቻችኹ፡ አዘጋጁ።
7ኢዮስያስም፡ለፋሲካው፡መሥዋዕት፡እንዲኾን፡በዚያ፡ለነበሩት፡ለሕዝቡ፡ልጆች፡ከመንጋው፡ሠላሳ፡ሺሕ፡ የበግና፡የፍየል፡ጠቦቶች፥ሦስት፡ሺሕም፡ወይፈኖች፡ሰጣቸው፤እነዚህም፡ከንጉሡ፡ሀብት፡ነበሩ።
8መሳፍንቱም፡ለሕዝቡና፡ለካህናቱ፡ለሌዋውያኑም፡በፈቃዳቸው፡ሰጡ፤የእግዚአብሔርም፡ቤት፡ አለቃዎች፥ኬልቅያስ፥ዘካርያስ፥ይሒኤል፥ለፋሲካው፡መሥዋዕት፡እንዲኾን፡ኹለት፡ሺሕ፡ስድስት፡መቶ፡ በጎችና፡ፍየሎች፥ሦስት፡መቶም፡በሬዎች፡ለካህናቱ፡ሰጡ።
9የሌዋውያኑም፡አለቃዎች፡ኮናንያ፥ወንድሞቹም፡ሸማያና፡ናትናኤል፥ሐሸቢያ፥ይዒኤል፥ዮዛባት፡ለፋሲካው፡ መሥዋዕት፡እንዲኾን፡ዐምስት፡ሺሕ፡በጎችና፡ፍየሎች፥ዐምስት፡መቶም፡በሬዎች፡ለሌዋውያን፡ሰጡ።
10አገልግሎቱም፡ተዘጋጀ፥ካህናቱም፡በስፍራቸው፥ሌዋውያኑም፡በየክፍላቸው፡እንደ፡ንጉሥ፡ትእዛዝ፡ ቆሙ።
11ፋሲካውንም፡ዐረዱ፥ሌዋውያኑም፡ቍርበቱን፡ገፈፉ፥ካህናቱም፡ከእጃቸው፡የተቀበሉትን፡ደም፡ረጩ።
12በሙሴም፡መጽሐፍ፡እንደ፡ተጻፈ፡ለእግዚአብሔር፡ያቀርቡ፡ዘንድ፡በያባቶቻቸው፡ቤቶች፡ለሕዝቡ፡ ልጆች፡እንዲሰጡ፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡ለዩ።እንዲሁም፡በበሬዎቹ፡አደረጉ።
13ፋሲካውንም፡እንደ፡ሥርዐቱ፡በእሳት፡ጠበሱ፤የተቀደሰውንም፡ቍርባን፡በምንቸትና፡በሰታቴ፡በድስትም፡ ቀቀሉ፥ለሕዝቡም፡ልጆች፡ዅሉ፡በፍጥነት፡አደረሱ።
14ከዚያም፡በዃላ፡ለራሳቸውና፡ለካህናቱ፡አዘጋጁ፤የአሮንም፡ልጆች፡ካህናቱ፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕትና፡ ስቡን፡ለማቅረብ፡እስከ፡ሌሊት፡ድረስ፡ይሠሩ፡ነበርና፥ስለዚህ፡ሌዋውያን፡ለራሳቸውና፡ለአሮን፡ልጆች፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ለካህናቱ፡አዘጋጁ።
15የአሣፍም፡ልጆች፡መዘምራን፡እንደ፡ዳዊት፥እንደ፡አሣፍም፡እንደ፡ኤማንም፡የንጉሡም፡ባለራእይ፡ እንደ፡ነበረው፡እንደ፡ኤዶታም፡ትእዛዝ፡በየስፍራቸው፡ነበሩ፤በረኛዎቹም፡በሮቹን፡ዅሉ፡ይጠብቁ፡ ነበር፤ወንድሞቻቸውም፡ሌዋውያን፡ያዘጋጁላቸው፡ነበርና፥ከአገልግሎታቸው፡ይርቁ፡ዘንድ፡አያስፈልጋቸውም፡ ነበር።
16እንደ፡ንጉሡም፡እንደ፡ኢዮስያስ፡ትእዛዝ፡በእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡ላይ፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡ ያቀርቡ፡ዘንድ፥ፋሲካውንም፡ያደርጉ፡ዘንድ፡የእግዚአብሔር፡አገልግሎት፡ዅሉ፡በዚያ፡ቀን፡ተዘጋጀ።
17የተገኙትም፡የእስራኤል፡ልጆች፡በዚያ፡ቀን፡ፋሲካውን፥ሰባት፡ቀንም፡የቂጣ፡በዓልን፡አደረጉ።
18ከነቢዩ፡ከሳሙኤል፡ዘመን፡ዠምሮ፡እንደዚህ፡ያለ፡ፋሲካ፡በእስራኤል፡ዘንድ፡ከቶ፡ አልተደረገም፤ከእስራኤልም፡ነገሥታት፡ዅሉ፡ኢዮስያስና፡ካህናቱ፥ሌዋውያኑም፥በዚያም፡የተገኙ፡የይሁዳና፡ የእስራኤል፡ሰዎች፡ዅሉ፥በኢየሩሳሌምም፡የሚኖሩት፡እንዳደረጉት፡ያለ፡ፋሲካ፡ያደረገ፡የለም።
19ይህም፡ፋሲካ፡ኢዮስያስ፡በነገሠ፡በዐሥራ፡ስምንተኛው፡ዓመት፡ተደረገ።
20ከዚህም፡ዅሉ፡በዃላ፥ኢዮስያስም፡ቤተ፡መቅደሱን፡ካሰናዳ፡በዃላ፥የግብጽ፡ንጉሥ፡ኒካዑ፡በኤፍራጥስ፡ ወንዝ፡አጠገብ፡ባለው፡በከርከሚሽ፡ላይ፡ይዋጋ፡ዘንድ፡ወጣ፤ኢዮስያስም፡ሊጋጠመው፡ወጣ።
21ርሱም፦የይሁዳ፡ንጉሥ፡ሆይ፥ከአንተ፡ጋራ፡ምን፡አለኝ፧በምዋጋበት፡በሌላ፡ቤት፡ላይ፡ነው፡እንጂ፡ ባንተ፡ላይ፡ዛሬ፡አልመጣኹም፤እግዚአብሔርም፡እንድቸኵል፡አዞ፟ኛል፤ከእኔ፡ጋራ፡ያለው፡እግዚአብሔር፡ እንዳያጠፋኽ፡ይህን፡በርሱ፡ላይ፡ከማድረግ፡ተመለስ፡ብሎ፡መልእክተኛዎችን፡ላከበት።
22ኢዮስያስ፡ግን፡ይዋጋው፡ዘንድ፡ተጸናና፡እንጂ፡ፊቱን፡ከርሱ፡አልመለሰም፤በእግዚአብሔርም፡አፍ፡ የተነገረውን፡የኒካዑን፡ቃል፡አልሰማም፥በመጊዶም፡ሸለቆ፡ይዋጋ፡ዘንድ፡መጣ።
23ቀስተኛዎችም፡ንጉሡን፡ኢዮስያስን፡ወጉት፤ንጉሡም፡ብላቴናዎቹን፦አጥብቄ፡ቈስያለኹና፡ከሰልፉ፡ ውስጥ፡አውጡኝ፡አላቸው።
24ብላቴናዎቹም፡ከሠረገላው፡አውርደው፡ለርሱ፡በነበረው፡በኹለተኛው፡ሠረገላ፡ውስጥ፡ አስቀመጡት፥ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡አመጡት፤ርሱም፡ሞተ፥በአባቶቹም፡መቃብር፡ተቀበረ፤ይሁዳና፡ ኢየሩሳሌምም፡ዅሉ፡ለኢዮስያስ፡አለቀሱ።
25ኤርምያስም፡ለኢዮስያስ፡የልቅሶ፡ግጥም፡ገጠመለት፤እስከ፡ዛሬም፡ድረስ፡ወንዶችና፡ሴቶች፡መዘምራን፡ ዅሉ፡በልቅሶ፡ግጥማቸው፡ስለ፡ኢዮስያስ፡ይናገሩ፡ነበር፤ይህም፡በእስራኤል፡ዘንድ፡ወግ፡ኾኖ፡በልቅሶ፡ ግጥም፡ተጽፏል።
26የቀረውም፡የኢዮስያስ፡ነገር፥በእግዚአብሔርም፡ሕግ፡አንደ፡ተጻፈ፡ያደረገው፡ቸርነት፥
27የፊተኛውና፡የዃለኛውም፡ነገሩ፥እንሆ፥በእስራኤልና፡በይሁዳ፡ነገሥታት፡መጽሐፍ፡ተጽፏል።