Skip to content
← 2 Kings

Chapter 1 · Amharic

2 Kings

1አክአብም፡ከሞተ፡በዃላ፡ሞዐብ፡በእስራኤል፡ላይ፡ዐመፀ።

2አካዝያስም፡በሰማርያ፡በሰገነቱ፡ላይ፡ሳለ፡ከዐይነ፡ርግቡ፡ወድቆ፡ታመመ፤ርሱም፦ኺዱ፡ከዚህም፡ደዌ፡ እድን፡እንደ፡ኾነ፡የዐቃሮንን፡አምላክ፡ብዔልዜቡልን፡ጠይቁ፡ብሎ፡መልእክተኛዎችን፡ላከ።

3የእግዚአብሔርም፡መልአክ፡ቴስብያዊውን፡ኤልያስን፦ተነሣ፥የሰማርያን፡ንጉሥ፡መልእክተኛዎች፡ ለመገናኘት፡ውጣና።የዐቃሮንን፡አምላክ፡ብዔልዜቡልን፡ትጠይቁ፡ዘንድ፡የምትኼዱት፡በእስራኤል፡ዘንድ፡ አምላክ፡ስለሌለ፡ነውን፧

4ስለዚህም፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ትሞታለኽ፡እንጂ፡ከወጣኽበት፡ዐልጋ፡አትወርድም፡በላቸው፡ አለው።ኤልያስም፡ኼደ።

5መልእክተኛዎችም፡ወደ፡አካዝያስ፡ተመለሱ፥ርሱም፦ለምን፡ተመለሳችኹ፧አላቸው።

6እነርሱም፦አንድ፡ሰው፡ሊገናኘን፡መጣና፦ኺዱ፥ወደላካችኹም፡ንጉሥ፡ተመልሳችኹ፦እግዚአብሔር፡ እንዲህ፡ይላል፦የዐቃሮንን፡አምላክ፡ብዔልዜቡልን፡ትጠይቅ፡ዘንድ፡የላከኽ፡በእስራኤል፡ዘንድ፡አምላክ፡ ስለሌለ፡ነውን፧ስለዚህ፡ትሞታለኽ፡እንጂ፡ከወጣኽበት፡ዐልጋ፡አትወርድም፡በሉት፡አለን፡አሉት።

7ርሱም፦ሊገናኛችኹ፡የወጣው፥ይህንስ፡ቃል፡የነገራችኹ፡ሰው፡መልኩ፡ምን፡ይመስላል፧አላቸው።

8እነርሱም፦ሰውዮው፡ጠጕራም፡ነው፥በወገቡም፡ጠፍር፡ታጥቆ፡ነበር፡አሉት።ርሱም፦ቴስብያዊው፡ ኤልያስ፡ነው፡አለ።

9ንጉሡም፡የዐምሳ፡አለቃውን፡ከዐምሳ፡ሰዎች፡ጋራ፡ሰደደ፥ወደ፡ርሱም፡ወጣ፤እንሆም፥በተራራ፡ራስ፡ ላይ፡ተቀምጦ፡ነበር።ርሱም፦የእግዚአብሔር፡ሰው፡ሆይ፥ንጉሡ፦ውረድ፡ይልኻል፡አለው።

10ኤልያስም፡መልሶ፡የዐምሳ፡አለቃውን፦እኔስ፡የእግዚአብሔር፡ሰው፡እንደ፡ኾንኹ፡እሳት፡ከሰማይ፡ ትውረድ፥አንተንም፥ዐምሳውንም፡ሰዎችኽን፡ትብላ፡አለው።እሳትም፡ከሰማይ፡ወርዳ፡ርሱንና፡ዐምሳውን፡ ሰዎቹን፡በላች።

11ደግሞም፡ሌላ፡የዐምሳ፡አለቃ፡ከዐምሳ፡ሰዎች፡ጋራ፡ላከበት፤ርሱም፦የእግዚአብሔር፡ሰው፡ ሆይ፥ንጉሡ፦ፈጥነኽ፡ውረድ፡ይላል፡ብሎ፡ተናገረ።

12ኤልያስም፦እኔስ፡የእግዚአብሔር፡ሰው፡እንደ፡ኾንኹ፡እሳት፡ከሰማይ፡ትውረድ፥አንተንም፡ዐምሳውንም፡ ሰዎችኽን፡ትብላ፡አለው።የእግዚአብሔርም፡እሳት፡ከሰማይ፡ወርዳ፡ርሱንና፡ዐምሳውን፡ሰዎቹን፡በላች።

13ደግሞም፡ሦስተኛ፡የዐምሳ፡አለቃ፡ከዐምሳ፡ሰዎች፡ጋራ፡ሰደደ፤ሦስተኛውም፡የዐምሳ፡አለቃ፡ወጥቶ፡ በኤልያስ፡ፊት፡በጕልበቱ፡ተንበረከከና፦የእግዚአብሔር፡ሰው፡ሆይ፥ነፍሴና፡የእነዚህ፡የዐምሳው፡ባሪያዎችኽ፡ ነፍስ፡በፊትኽ፡የከበረች፡ትኹን።

14እንሆ፥እሳት፡ከሰማይ፡ወርዳ፡የፊተኛዎቹን፡ኹለቱን፡የዐምሳ፡አለቃዎችና፡ዐምሳ፡ዐምሳውን፡ሰዎቻቸውን፡ በላች፤አኹን፡ግን፡ነፍሴ፡በፊትኽ፡የከበረች፡ትኹን፡ብሎ፡ለመነው።

15የእግዚአብሔርም፡መልአክ፡ኤልያስን፦ከርሱ፡ጋራ፡ውረድ፥አትፍራውም፡አለው።ተነሥቶም፡ከርሱ፡ ጋራ፡ወደ፡ንጉሡ፡ወረደ።

16ኤልያስም፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የዐቃሮንን፡አምላክ፡ብዔልዜቡልን፡ትጠይቅ፡ዘንድ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org መልእክተኛዎችን፡ልከኻልና፥ትሞታለኽ፡እንጂ፡ከወጣኽበት፡ዐልጋ፡አትወርድም፡አለው።

17ኤልያስም፡እንደተናገረው፡እንደእግዚአብሔር፡ቃል፡ሞተ።ልጅም፡አልነበረውምና፡በይሁዳ፡ንጉሥ፡ በኢዮሳፍጥ፡ልጅ፡በኢዮራም፡በኹለተኛው፡ዓመት፡ወንድሙ፡ኢዮራም፡በርሱ፡ፋንታ፡ነገሠ።

18አካዝያስ፡ያደረገው፡የቀረው፡ነገር፡በእስራኤል፡ነገሥታት፡ታሪክ፡መጽሐፍ፡የተጻፈ፡አይደለምን፧

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source