1በአርጤክስስም፡ዘመን፡እንዲህ፡ኾነ፤ይህም፡አርጤክስስ፡ከህንድ፡ዠምሮ፡እስከ፡ኢትዮጵያ፡ድረስ፡በመቶ፡ ኻያ፡ሰባት፡አገሮች፡ላይ፡ነገሠ።
2በዚያም፡ዘመን፡ንጉሡ፡አርጤክስስ፡በሱሳ፡ግንብ፡በነበረው፡በመንግሥቱ፡ዙፋን፡ላይ፡ተቀምጦ፡ሳለ፥
3በነገሠ፡በሦስተኛው፡ዓመት፡ለባለሟሎቹና፡ለአገልጋዮቹ፡ዅሉ፡ግብዣ፡አደረገ፤የፋርስና፡የሜዶን፡ ታላላቆች፡ዅሉ፥የየአገሩ፡ዐዛውንትና፡ሹማምት፥በፊቱ፡ነበሩ፤
4የከበረውንም፡የመንግሥቱን፡ሀብት፥የታላቁንም፡የግርማዊነቱን፡ክብር፡መቶ፡ሰማንያ፡ቀን፡ያኽል፡ አሳያቸው።
5ይህም፡ቀን፡በተፈጸመ፡ጊዜ፡በሱሳ፡ግንብ፡ውስጥ፡ለተገኙት፡ሕዝብ፡ዅሉ፡ከታላቁ፡ዠምሮ፡እስከ፡ ታናሹ፡ድረስ፡ንጉሡ፡በንጉሡ፡ቤት፡አታክልት፡ውስጥ፡ባለው፡አደባባይ፡ሰባት፡ቀን፡ግብዣ፡አደረገ።
6ነጭ፥አረንጓዴ፥ሰማያዊም፡መጋረጃዎች፡ከጥሩ፡በፍታና፡ከሐምራዊ፡ግምጃ፡በተሠራ፡ገመድ፥በብር፡ ቀለበትና፡በእብነ፡በረድ፡አዕማድ፡ላይ፡ተዘርግተው፡ነበር፤ዐልጋዎቹም፡ከወርቅና፡ከብር፡ተሠርተው፡በቀይና፡ በነጭ፡በብጫና፡በጥቍር፡እብነ፡በረድ፡ወለል፡ላይ፡ነበሩ።
7መጠጡም፡በልዩ፡ልዩ፡በወርቅ፡ዕቃ፡ይታደል፡ነበር፤የንጉሡም፡የወይን፡ጠጅ፡እንደ፡ንጉሡ፡ለጋስነት፡ መጠን፡እጅግ፡ብዙ፡ነበረ።
8ንጉሡም፡እንደ፡ሰው፡ዅሉ፡ፈቃድ፡ያደርጉ፡ዘንድ፡ለቤቱ፡አዛዦች፡ዅሉ፡አዞ፟፡ነበርና፥መጠጡ፡እንደ፡ ወግ፡አልነበረም።
9ንግሥቲቱም፡አስጢን ፡በንጉሡ፡በአርጤክስስ፡ቤተ፡መንግሥት፡ለሴቶች፡ግብዣ፡አደረገች።
11በሰባተኛውም፡ቀን፡ንጉሡ፡አርጤክስስ፡የወይን፡ጠጅ፡ጠጥቶ፡ደስ፡ባለው፡ጊዜ፥ንግሥቲቱ፡ አስጢን፡መልከ፡መልካም፡ነበረችና፡ውበቷ፡ለአሕዛብና፡ለአለቃዎች፡እንዲታይ፡የመንግሥቱን፡ዘውድ፡ጭነው፡ ወደ፡ንጉሡ፡ፊት፡ያመጧት፡ዘንድ፡በፊቱ፡የሚያገለግሉትን፡ሰባቱን፡ጃን፡ደረባዎች፡ ምሁማንን፥ባዛንን፥ሐርቦናን፥ገበታን፥ዘቶልታን፥ዜታርን፥ከርከስን፡አዘዛቸው።
12ነገር፡ግን፥ንግሥቲቱ፡አስጢን፡በጃን፡ደረባዎቹ፡እጅ፡በላከው፡በንጉሡ፡ትእዛዝ፡ትመጣ፡ዘንድ፡እንቢ፡ አለች፤ንጉሡም፡እጅግ፡ተቈጣ፥በቍጣውም፡ተናደደ።
13ሕግንና፡ፍርድን፡በሚያውቁ፥ዅሉ፡ፊት፡የንጉሡ፡ወግ፡እንዲህ፡ነበረና፡ንጉሡ፡የዘመኑን፡ነገር፡ የሚያውቁትን፡ጥበበኛዎችን፥
14በመንግሥቱም፡ቀዳሚዎች፡ኾነው፡የሚቀመጡ፡የንጉሡ፡ባለሟሎች፡ሰባቱ፡የፋርስና፡የሜዶን፡መሳፍንት፡ አርቄስዮስ ፥ሼታር፥አድማታ፥ተርሺሽ፥ሜሬስ፥ማሌሴዓር ፥ምሙካን፡በአጠገቡ፡ሳሉ፦
15በጃን፡ደረባዎች፡እጅ፡የተላከባትን፡የንጉሡን፡የአርጤክስስን፡ትእዛዝ፡ስላላደረገች፥በንግሥቲቱ፡ በአስጢን፡ላይ፥እንደ፡ሕጉ፥የምናደርገው፡ምንድር፡ነው፧አላቸው።
16ምሙካንም፡በንጉሡና፡በዐዛውንቱ፡ፊት፡እንዲህ፡አለ፦ንግሥቲቱ፡አስጢን፡ዐዛውንቱን፡ዅሉና፡ 252ፋር.፥ቫሽቲ። 253 ዕብ.፥ካርሼና። 254ዕብ.፥ማርስና። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org በንጉሡ፡በአርጤክስስ፡አገር፡ያሉትን፡አሕዛብ፡ዅሉ፡በድላለች፡እንጂ፡ንጉሡን፡ብቻ፡የበደለች፡አይደለችም።
17ይህ፡የንግሥቲቱ፡ነገር፡ወደ፡ሴቶች፡ዅሉ፡ይደርሳልና፦ንጉሡ፡አርጤክስስ፡ንግሥቲቱ፡አስጢን፡ወደ፡ ርሱ፡ትገባ፡ዘንድ፡አዘዘ፥ርሷ፡ግን፡አልገባችም፡ተብሎ፡በተነገረ፡ጊዜ፡ባሎቻቸው፡በዐይናቸው፡ዘንድ፡ የተናቁ፡ይኾናሉ።
18ዛሬም፡የንግሥቲቱን፡ነገር፡የሰሙት፡የፋርስና፡የሜዶን፡ወይዛዝር፡እንዲህና፡እንዲህ፡ብለው፡ለንጉሡ፡ ዐዛውንት፡ዅሉ፡ይናገራሉ፥ንቀትና፡ቍጣም፡ይበዛል።
19ንጉሡም፡ቢፈቅድ፥አስጢን፡ወደ፡ንጉሡ፡ወደ፡አርጤክስስ፡ፊት፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡እንዳትገባ፡ የንጉሡ፡ትእዛዝ፡ከርሱ፡ይውጣ፥እንዳይፈርስም፡በፋርስና፡በሜዶን፡ሕግ፡ይጻፍ፤ንጉሡም፡ንግሥትነቷን፡ ከርሷ፡ለተሻለችው፡ለሌላዪቱ፡ይስጥ።
20የንጉሡም፡ትእዛዝ፡በሰፊው፡መንግሥቱ፡ዅሉ፡በተነገረ፡ጊዜ፡ሴቶች፡ዅሉ፡ባሎቻቸውን፡ታላቁንም፡ ታናሹንም፡ያከብራሉ።
21ይህም፡ምክር፡ንጉሡንና፡ዐዛውንቱን፡ደስ፡አሠኛቸው፤ንጉሡም፡እንደ፡ምሙካን፡ቃል፡አደረገ።
22ሰው፡ዅሉ፡በቤቱ፡አለቃ፡ይኹን፤በሕዝቡም፡ቋንቋ፡ይናገር፡ብሎ፡ለአገሩ፡ዅሉ፡እንደ፡ጽሕፈቱ፡ ለሕዝቡም፡ዅሉ፡እንደ፡ቋንቋው፡ደብዳቤዎችን፡ወደንጉሡ፡አገሮች፡ዅሉ፡ሰደደ።