Skip to content
← Esther

Chapter 2 · Amharic

Esther

1ከዚህም፡ነገር፡በዃላ፡የንጉሡ፡የአርጤክስስ፡ቍጣ፡በበረደ፡ጊዜ፡አስጢንና፡ያደረገችውን፡የፈረደባትንም፡ ነገር፡ዐሰበ።

2ንጉሡንም፡የሚያገለግሉ፡ብላቴናዎች፡እንዲህ፡አሉት፦መልከ፡መልካም፡የኾኑ፡ደናግል፡ለንጉሡ፡ ይፈለጉለት፤

3ሴቶችን፡ከሚጠብቅ፡ከንጉሡ፡ጃን፡ደረባ፡ከሄጌ፡እጅ፡በታች፡እንዲያደርጓቸው፥መልከ፡መልካሞቹን፡ ደናግል፡ዅሉ፡ወደሱሳ፡ግንብ፡ወደ፡ሴቶች፡ቤት፡ይሰበስቧቸው፡ዘንድ፡ንጉሡ፡በመንግሥቱ፡አገሮች፡ዅሉ፡ ሹማምቶችን፡ያኑር፤ቅባትና፡የሚያስፈልጋቸውም፡ይሰጣቸው፤

4ንጉሡንም፡ደስ፡የምታሠኝ፡ቈንዦ፡በአስጢን፡ስፍራ፡ትንገሥ።ይህም፡ነገር፡ንጉሡን፡ደስ፡ አሠኘው፥እንዲሁም፡አደረገ።

5አንድ፡አይሁዳዊ፡የቂስ፡ልጅ፡የሰሜኢ፡ልጅ፡የኢያዕር፡ልጅ፡መርዶክዮስ፡የሚባል፡ብንያማዊ፡በሱሳ፡ ግንብ፡ነበረ።

6ርሱም፡የባቢሎን፡ንጉሥ፡ናቡከደነጾር፡ከማረካቸው፡ከይሁዳ፡ንጉሥ፡ከኢኮንያን፡ጋራ፡ከተማረኩት፡ ምርኮኛዎች፡ጋራ፡ከኢየሩሳሌም፡የተማረከ፡ነበረ።

7አባትና፡እናትም፡አልነበራትምና፥የአጎቱ፡ልጅ፡ሀደሳ፡የተባለችውን፡አስቴርን፡አሳድጎ፡ነበር፤ቈንዦዪቱም፡ የተዋበችና፡መልከ፡መልካም፡ነበረች፤አባቷና፡እናቷም፡ከሞቱ፡በዃላ፡መርዶክዮስ፡እንደ፡ልጁ፡አድርጎ፡ ወስዷት፡ነበር።

8የንጉሡም፡ትእዛዝና፡ዐዋጅ፡በተሰማ፡ጊዜ፥ብዙም፡ቈነዣዥት፡ወደሱሳ፡ግንብ፡ወደሄጌ፡እጅ፡በተሰበሰቡ፡ ጊዜ፥አስቴር፡ወደንጉሡ፡ቤት፡ወደሴቶች፡ጠባቂው፡ወደ፡ሄጌ፡ተወሰደች።

9ቈንዦዪቱም፡ደስ፡አሠኘችው፥በርሱም፡ዘንድ፡ሞገስ፡አገኘች፤ቅባቷንም፡ድርሻዋንም፡ከንጉሡም፡ቤት፡ ልታገኝ፡የሚገ፟ባ፟ትን፡ሰባት፡ደንገጥሮች፡ፈጥኖ፡ሰጣት፤ርሷንና፡ደንገጥሮቿንም፡በሴቶች፡ቤት፡በተመረጠ፡ ስፍራ፡አኖረ።

10ይህንም፡እንዳትናገር፡መርዶክዮስ፡አዟ፟ት፡ነበርና፥አስቴር፡ሕዝቧንና፡ወገኗን፡አልተናገረችም። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

11መርዶክዮስም፡የአስቴርን፡ደኅንነትና፡የሚኾንላትን፡ያውቅ፡ዘንድ፡ዕለት፡ዕለት፡በሴቶች፡ቤት፡ወለል፡ ትይዩ፡ይመላለስ፡ነበር።

12የመንጻታቸውም፡ወራት፡ስድስት፡ወር፡ያኽል፡በከርቤ፡ዘይት፥ስድስት፡ወርም፡በጣፋጭ፡ሽቱና፡በልዩ፡ ልዩም፡በሚያነጻ፡ነገር፡ይፈጸም፡ነበርና፥እንደ፡ሴቶች፡ወግ፡ዐሥራ፡ኹለት፡ወር፡እንዲሁ፡ከተደረገላት፡ በዃላ፡ወደ፡ንጉሡ፡ወደ፡አርጤክስስ፡ለመግባት፡የአንዳንዲቱ፡ቈንዦ፡ተራ፡በደረሰ፡ጊዜ፥

13በዚህ፡ወግ፡ቈንዦዪቱ፡ወደ፡ንጉሡ፡ትገባ፡ነበር፤ከሴቶች፡ቤት፡ወደንጉሡ፡ቤት፡ለመውሰድ፡ የምትሻውን፡ዅሉ፡ይሰጧት፡ነበር።

14ማታም፡ትገባ፡ነበር፥ሲነጋም፡ተመልሳ፡ወደኹለተኛው፡ሴቶች፡ቤት፡ቁባቶችን፡ወደሚጠብቅ፡ ወደንጉሡ፡ጃን፡ደረባ፡ወደ፡ጋይ፡ትመጣ፡ነበር፤ንጉሡም፡ያልፈለጋት፡እንደ፡ኾነ፥በስሟም፡ያልተጠራች፡ እንደ፡ኾነ፥ከዚያ፡ወዲያ፡ወደ፡ንጉሡ፡አትገባም፡ነበር።

15ወደ፡ንጉሡም፡ትገባ፡ዘንድ፡የመርዶክዮስ፡አጎት፡የአቢካኢል፡ልጅ፡የአስቴር፡ተራ፡በደረሰ፡ጊዜ፡ የሴቶች፡ጠባቂው፡የንጉሡ፡ጃን፡ደረባ፡ሄጌ፡ከሚለው፡በቀር፡ምንም፡አልፈለገችም፡ነበር፤አስቴርም፡ በሚያይዋት፡ዅሉ፡ዐይን፡ሞገስ፡አግኝታ፡ነበርና።

16አርጤክስስም፡በነገሠ፡በሰባተኛው፡ዓመት፡አዳር፡በሚባለው፡በዐሥራ፡ኹለተኛው፡ወር፡አስቴር፡ ወደንጉሡ፡ቤት፡ተወሰደች።

17ንጉሡም፡ከሴቶች፡ዅሉ፡ይልቅ፡አስቴርን፡ወደደ፥በዐይኑም፡ከደናግል፡ዅሉ፡ይልቅ፡ሞገስንና፡ መወደድን፡አገኘች፤የመንግሥቱንም፡ዘውድ፡በራሷ፡ላይ፡አደረገ፥በአስጢንም፡ፋንታ፡አነገሣት።

18ንጉሡም፡ስለ፡አስቴር፡ለባለሟሎቹና፡ለአገልጋዮቹ፡ዅሉ፡ሰባት፡ቀን፡ያኽል፡ትልቅ፡ግብዣ፡ አደረገ፤ለአገሮቹም፡ዅሉ፡ይቅርታ፡አደረገ፥እንደ፡ንጉሡም፡ለጋስነት፡መጠን፡ስጦታ፡ሰጠ።

19ደናግሉም፡ዳግመኛ፡በተሰበሰቡ፡ጊዜ፡መርዶክዮስ፡በንጉሡ፡በር፡ይቀመጥ፡ነበር።

20አስቴርም፡ከርሱ፡ጋራ፡እንዳደገችበት፡ጊዜ፡የመርዶክዮስን፡ትእዛዝ፡ታደርግ፡ነበርና፥መርዶክዮስ፡ እንዳዘዛት፡አስቴር፡ወገኗንና፡ሕዝቧን፡አልተናገረችም።

21በዚያም፡ወራት፡መርዶክዮስ፡በንጉሡ፡በር፡ተቀምጦ፡ሳለ፡ደጁን፡ከሚጠብቁት፡ከንጉሡ፡ጃን፡ደረባዎች፡ ኹለቱ፡ገበታና፡ታራ፡ተቈጡ፥እጃቸውንም፡በንጉሡ፡በአርጤክስስ፡ላይ፡ያነሡ፡ዘንድ፡ፈለጉ።

22ነገሩም፡ለመርዶክዮስ፡ተገለጠ፥ርሱም፡ለንግሥቲቱ፡ለአስቴር፡ነገራት፤አስቴርም፡በመርዶክዮስ፡ስም፡ ለንጉሡ፡ነገረች።

23ነገሩም፡ተመረመረ፥እንዲህም፡ኾኖ፡ተገኘ፥ኹለቱም፡በዛፍ፡ላይ፡ተሰቀሉ፤ያም፡በንጉሡ፡ፊት፡ በታሪክ፡መጽሐፍ፡ተጻፈ።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source