1ከዚህም፡ነገር፡በዃላ፡ንጉሡ፡አርጤክስስ፡የአጋጋዊውን፡የሐመዳቱን፡ልጅ፡ሐማን፡ከፍ፡ከፍ፡ አደረገው፥አከበረውም፥ወንበሩንም፡ከርሱ፡ጋራ፡ከነበሩት፡ዐዛውንት፡ዅሉ፡በላይ፡አደረገለት።
2ንጉሡም፡ስለ፡ርሱ፡እንዲሁ፡አዞ፟፡ነበርና፥በንጉሡ፡በር፡ያሉት፡የንጉሡ፡ባሪያዎች፡ዅሉ፡ተደፍተው፡ ለሐማ፡ይሰግዱ፡ነበር።መርዶክዮስ፡ግን፡አልተደፋም፥አልሰገደለትም።
3በንጉሡም፡በር፡ያሉት፡የንጉሡ፡ባሪያዎች፡መርዶክዮስን፦የንጉሡን፡ትእዛዝ፡ለምን፡ ትተላለፋለኽ፧አሉት።
4ይህንም፡ዕለት፡ዕለት፡እየተናገሩ፡ርሱ፡ባልሰማቸው፡ጊዜ፡አይሁዳዊ፡እንደ፡ኾነ፡ነግሯቸው፡ ነበርና፥የመርዶክዮስ፡ነገር፡እንዴት፡እንደ፡ኾነ፡ያዩ፡ዘንድ፡ለሐማ፡ነገሩት። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
5ሐማም፡መርዶክዮስ፡እንዳልተደፋለት፡እንዳልሰገደለትም፡ባየ፡ጊዜ፡እጅግ፡ተቈጣ።
6የመርዶክዮስን፡ወገን፡ነግረውት፡ነበርና፥በመርዶክዮስ፡ብቻ፡እጁን፡ይጭን፡ዘንድ፡በዐይኑ፡ ተናቀ፤ሐማም፡በአርጤክስስ፡መንግሥት፡ዅሉ፡የነበሩትን፡የመርዶክዮስን፡ሕዝብ፡አይሁድን፡ዅሉ፡ሊያጠፋ፡ ፈለገ።
7በንጉሡም፡በአርጤክስስ፡በዐሥራ፡ኹለተኛው፡ዓመት፡ከመዠመሪያው፡ወር፡ከኒሳን፡ዠምሮ፡በየዕለቱና፡ በየወሩ፡እስከ፡ዐሥራ፡ኹለተኛው፡ወር፡እስከ፡አዳር፡ድረስ፡በሐማ፡ፊት፡ፉር፡የተባለውን፡ዕጣ፡ይጥሉ፡ ነበር።
8ሐማም፡ንጉሡን፡አርጤክስስን፦አንድ፡ሕዝብ፡በአሕዛብ፡መካከል፡በመንግሥትኽ፡አገሮች፡ዅሉ፡ ተበትነዋል፤ሕጋቸውም፡ከሕዝቡ፡ዅሉ፡ሕግ፡የተለየ፡ነው፥የንጉሡንም፡ሕግ፡አይጠብቁም፤ንጉሡም፡ ይተዋቸው፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ውም።
9ንጉሡም፡ቢፈቅድ፡እንዲጠፉ፡ይጻፍ፤እኔም፡ወደንጉሡ፡ግምጃ፡ቤት፡ያገቡት፡ዘንድ፡ዐሥር፡ሺሕ፡ መክሊት፡ብር፡የንጉሡን፡ሥራ፡በሚሠሩት፡እጅ፡እመዝናለኹ፡አለው።
10ንጉሡም፡ቀለበቱን፡ከእጁ፡አወለቀ፥ለአይሁድም፡ጠላት፡ለአጋጋዊው፡ለሐመዳቱ፡ልጅ፡ለሐማ፡ሰጠው።
11ንጉሡም፡ሐማን፦ደስ፡የሚያሠኝኽን፡ነገር፡ታደርግባቸው፡ዘንድ፡ብሩም፡ሕዝቡም፡ለአንተ፡ተሰጥቶኻል፡ አለው።
12በመዠመሪያውም፡ወር፡ከወሩም፡በዐሥራ፡ሦስተኛው፡ቀን፡የንጉሡ፡ጸሓፊዎች፡ተጠሩ፤ከህንድ፡ዠምሮ፡ እስከ፡ኢትዮጵያ፡ድረስ፡ወዳሉ፡መቶ፡ኻያ፡ሰባት፡አገሮች፥በያገሩ፡ወዳሉ፡ሹማምትና፡አለቃዎች፡ወደ፡ አሕዛብም፡ዅሉ፡ገዢዎች፡እንደ፡ቋንቋቸው፡በንጉሡ፡በአርጤክስስ፡ቃል፡ሐማ፡እንዳዘዘ፡ተጻፈ፥በንጉሡም፡ ቀለበት፡ታተመ።
13በዐሥራ፡ኹለተኛው፡ወር፡በአዳር፡በዐሥራ፡ሦስተኛው፡ቀን፡አይሁድን፡ዅሉ፥ልጆችንና፡ ሽማግሌዎችን፥ሕፃናትንና፡ሴቶችን፥ባንድ፡ቀን፡ያጠፉና፡ይገድሉ፡ዘንድ፥ይደመስሱም፡ዘንድ፥ምርኳቸውንም፡ ይዘርፉ፡ዘንድ፡ደብዳቤዎች፡በመልእክተኛዎች፡እጅ፡ወደንጉሡ፡አገሮች፡ዅሉ፡ተላኩ።
14በዚያም፡ቀን፡ይዘጋጁ፡ዘንድ፡የደብዳቤው፡ቅጅ፡በያገሩ፡ላሉ፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ታወጀ።
15መልእክተኛዎቹም፡በንጉሡ፡ትእዛዝ፡እየቸኰሉ፡ኼዱ፥ዐዋጁም፡በሱሳ፡ግንብ፡ተነገረ።ንጉሡና፡ሐማ፡ ሊጠጡ፡ተቀመጡ፤ከተማዪቱ፡ሱሳ፡ግን፡ተደናገጠች።