1በሠላሳኛው፡ዓመት፡በአራተኛው፡ወር፡ከወሩም፡በዐምስተኛው፡ቀን፡በኮቦር፡ወንዝ፡በምርኮኛዎች፡ መካከል፡ሳለኹ፡ሰማያት፡ተከፈቱ፥የእግዚአብሔርንም፡ራእይ፡አየኹ።
2ንጉሡ፡ዮአኪን፡በተማረከ፡በዐምስተኛው፡ዓመት፡
3ከወሩም፡በዐምስተኛው፡ቀን፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡በከለዳውያን፡አገር፡በኮቦር፡ወንዝ፡ወደቡዝ፡ልጅ፡ ወደ፡ካህኑ፡ወደ፡ሕዝቅኤል፡መጣ።የእግዚአብሔርም፡እጅ፡በዚያ፡በእኔ፡ላይ፡ኾነች፥
4እኔም፡አየኹ፤እንሆም፥ከሰሜን፡በኩል፡ዐውሎ፡ነፋስና፡ታላቅ፡ደመና፡የሚበርቅም፡እሳት፡ መጣ፥በዙሪያውም፡ጸዳል፡ነበረ፥በመካከልም፡በእሳቱ፡ውስጥ፡እንደሚብለጨለጭ፡የወርቅ፡ምስያ፡ነበረ።
5ከመካከልም፡የአራት፡እንስሳዎች፡አምሳያ፡ወጣ።መልካቸውም፡እንደዚህ፡ነበረ፥ሰውም፡ይመስሉ፡ነበር።
6ለያዳንዱም፡አራት፡አራት፡ፊት፥ለያንዳንዱም፡አራት፡አራት፡ክንፍ፡ነበሩት።
7እግሮቻቸውም፡ቀጥ፡ያሉ፡እግሮች፡ነበሩ፤የእግራቸውም፡ኰቴ፡እንደ፡ጥጃ፡እግር፡ኰቴ፡ነበረ፤እንደ፡ ተወለወለ፡ናስም፡ይብለጨለጭ፡ነበር።
8በክንፎቻቸውም፡በታች፡በያራቱ፡ጐድናቸው፡እንደሰው፡እጅ፡ነበረ፤ለአራቱም፡እንደዚህ፡ያሉ፡ፊትና፡ ክንፍ፡ነበሯቸው።
9ክንፎቻቸው፡ርስ፡በርሱ፡የተያያዘ፡ነበረ፤ሲኼዱም፡አይገላመጡም፡ነበር፥እያንዳንዱም፡ፊቱን፡አቅንቶ፡ ይኼድ፡ነበር።
10የፊታቸው፡አምሳያ፡እንደ፡ሰው፡ፊት፡ነበረ፥ለአራቱም፡በስተቀኛቸው፡እንደ፡አንበሳ፡ ፊት፥በስተግራቸውም፡እንደ፡ላም፡ፊት፡ነበራቸው፥ለአራቱም፡ደግሞ፡የንስር፡ፊት፡ነበራቸው።
11ክንፋቸውም፡በላይ፡ተዘርግቶ፡ነበር፥የያንዳንዱም፡ኹለት፡ኹለት፡ክንፋቸው፡የተያያዙ፡ነበሩ፥ኹለት፡ ኹለቱም፡ገላቸውን፡ይከድኑ፡ነበር።
12እያንዳንዱም፡ወደ፡ፊት፡ቀጥ፡ብሎ፡ይኼድ፡ነበር፤መንፈስም፡ወደሚኼድበት፡ዅሉ፡ይኼዱ፡ ነበር፥ሲኼዱም፡አይገላመጡም፡ነበር።
13በእንስሳዎቹ፡መካከል፡እንደሚነድ፟፡የእሳት፡ፍም፡ያለ፡ምስያ፡ነበረ፤በእንስሳዎች፡መካከል፡ወዲህና፡ ወዲያ፡የሚኼድ፡እንደ፡ፋና፡ያለ፡ምስያ፡ነበረ፤ለእሳቱም፡ጸዳል፡ነበረው፥ከእሳቱም፡መብረቅ፡ይወጣ፡ ነበር።
14እንስሳዎቹም፡እንደ፡መብረቅ፡ምስያ፡ይሮጡና፡ይመለሱ፡ነበር።
15እንስሳዎችንም፡ስመለከት፥እንሆ፥በአራቱ፡እንስሳዎች፡አጠገብ፡በምድር፡ላይ፡አንድ፡አንድ፡ መንኰራኵር፡አየኹ።
16የመንኰራኵሩም፡መልክ፡እንደ፡ቢረሌ፡ነበረ፤አራቱም፡አንድ፡አምሳያ፡ነበሩ፤ሥራቸውም፡ በመንኰራኵር፡ውስጥ፡እንዳለ፡መንኰራኵር፡ነበረ።
17በያራቱ፡ጐድናቸው፡ይኼዱ፡ነበር፤ሲኼዱም፡አይገላመጡም፡ነበር።
18ቁመታቸውም፡የረዘመና፡የሚያስፈራ፡ነበረ፤የአራቱም፡ክበብ፡ዙሪያው፡በዐይን፡ተሞልቶ፡ነበር። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
19እንስሳዎቹም፡በኼዱ፡ጊዜ፡መንኰራኵሮቹ፡በአጠገባቸው፡ኼዱ።እንስሳዎቹም፡ከምድር፡ከፍ፡ከፍ፡ባሉ፡ ጊዜ፡መንኰራኵሮቹ፡ከፍ፡ከፍ፡አሉ።
20መንፈሱ፡ወደሚኼድበት፡ዅሉ፡እነርሱ፡ኼዱ፤የእንስሳዎች፡መንፈስ፡በመንኰራኵሮቹ፡ውስጥ፡ነበረና፡ መንኰራኵሮቹ፡በእነርሱ፡አጠገብ፡ከፍ፡ከፍ፡አሉ።
21የእንስሳዎች፡መንፈስ፡በመንኰራኵሮቹ፡ውስጥ፡ነበረና፡እነዚያ፡ሲኼዱ፡እነዚህ፡ይኼዱ፡ነበር፤እነዚያም፡ ሲቆሙ፡እነዚህ፡ይቆሙ፡ነበር፤እነዚያም፡ከምድር፡ከፍ፡ከፍ፡ሲሉ፡መንኰራኵሮቹ፡በአጠገባቸው፡ከፍ፡ከፍ፡ ይሉ፡ነበር።
22ከእንስሳዎች፡ራስ፡በላይ፡የሚያስፈራ፡በረዶ፡የሚመስል፡የጠፈር፡አምሳያ፡በራሳቸው፡ላይ፡ተዘርግቶ፡ ነበር።
23ከጠፈሩም፡በታች፡ክንፎቻቸው፡ርስ፡በርሳቸው፡ተቃንተው፡ነበር፤ለያንዳንዱም፡ገላውን፡የሚከድኑ፡ ኹለት፡ኹለት፡ክንፎች፡ነበሩት።
24ሲኼዱም፡የክንፎቻቸው፡ድምፅ፡እንደ፡ብዙ፡ውሃ፡ድምፅ፥እንደ፡ዅሉን፡የሚችል፡የአምላክም፡ ድምፅ፥እንደ፡ታላቅም፡ሰራዊት፡ድምፅ፡ኾኖ፡ሰማኹ፤ሲቆሙም፡ክንፎቻቸውን፡ዝቅ፡ያደርጉ፡ነበር።
25በራሳቸውም፡ላይ፡ካለው፡ጠፈር፡በላይ፡ድምፅ፡ተሰማ፤ሲቆሙም፡ክንፎቻቸውን፡ዝቅ፡ያደርጉ፡ነበር።
26በራሳቸውም፡በላይ፡ካለው፡ጠፈር፡በላይ፡የሰንፔር፡ድንጋይ፡የሚመስል፡የዙፋን፡አምሳያ፡ ነበረ፤በዙፋኑም፡አምሳያ፡ላይ፡እንደ፡ሰው፡መልክ፡አምሳያ፡ነበረ።
27ከወገቡም፡አምሳያ፡ወደ፡ላይ፡የሚብለጨለጭ፡የወርቅ፡ምስያ፡አየኹ፤ከወገቡም፡አምሳያ፡ወደ፡ታች፡ እንደ፡እሳት፡ምስያ፡አየኹ፤በዙሪያውም፡ጸዳል፡ነበረ።
28በዝናብ፡ቀን፡በደመና፡ውስጥ፡እንደ፡ቀስተ፡ደመና፡አምሳያ፥እንዲሁ፡በዙሪያው፡ያለ፡ጸዳል፡አምሳያ፡ ነበረ።የእግዚአብሔር፡ክብር፡ምሳሌ፡መልክ፡ይህ፡ነበረ።ባየኹም፡ጊዜ፡በግንባሬ፡ተደፋኹ፥የሚናገርንም፡ ድምፅ፡ሰማኹ።