1ነቢዩ፡ዕንባቆም፡ያየው፡ሸክም፡ይህ፡ነው።
2አቤቱ፥እኔ፡ስጮኽ፡የማትሰማው፡እስከ፡መቼ፡ነው፧ስለ፡ግፍ፡ወዳንተ፡እጮኻለኹ፥አንተም፡ አታድንም።
3በደልንስ፡ስለ፡ምን፡አሳየኸኝ፧ጠማምነትንስ፡ስለ፡ምን፡ትመለከታለኽ፧ጥፋትና፡ግፍ፡በፊቴ፡ ነው፤ጠብና፡ክርክር፡ይነሣሉ።
4ስለዚህ፥ሕግ፡ላልቷል፥ፍርድም፡ድል፡ነሥቶ፡አይወጣም፤ኀጢአተኛ፡ጻድቅን፡ይከባ፟ልና፤ስለዚህ፥ፍርድ፡ ጠማማ፡ኾኖ፡ይወጣል።
5እናንተ፡የምትንቁ፡ሆይ፥አንድ፡ቢተርክላችኹ፡ስንኳ፡የማታምኑትን፡ሥራ፡በዘመናችኹ፡እሠራለኹና፡ እዩ፥ተመልከቱ፥ተደነቁ።
6እንሆ፥የእነርሱ፡ያልኾነውን፡መኖሪያ፡ይወርሱ፡ዘንድ፡በምድር፡ስፋት፡ላይ፡የሚኼዱትን፡መራሮችንና፡ ፈጣኖችን፡ሕዝብ፡ከለዳውያንን፡አስነሣለኹ።
7እነርሱ፡የሚያስፈሩና፡የሚያስደነግጡ፡ናቸው፤ፍርዳቸውና፡ክብራቸው፡ከራሳቸው፡ይወጣል።
8ፈረሶቻቸውም፡ከነብር፡ይልቅ፡ፈጣኖች፡ናቸው፥ከማታም፡ተኵላ፡ይልቅ፡ጨካኞች፡ ናቸው፤ፈረሰኛዎቻቸውም፡ይንሳፈፋሉ፥ከሩቅም፡ይመጣሉ፥ለመብልም፡እንደሚቸኵል፡ንስር፡ይበራ፟ሉ።
9ዅሉም፡ለግፍ፡ሥራ፡ይመጣሉ፥ፊታቸውንም፡እንደ፡ምሥራቅ፡ነፋስ፡ያቀናሉ፤ምርኮኛዎችንም፡እንደ፡ አሸዋ፡ይሰበስባሉ።
10በነገሥታት፡ላይ፡ያላግጣሉ፥መሳፍንትም፡ዋዛ፡ኾነውላቸዋል፤በምሽጉ፡ዅሉ፡ይሥቃሉ፥ዐፈሩንም፡ ከምረው፡ይወስዱታል።
11የዚያን፡ጊዜም፡እንደ፡ነፋስ፡ዐልፎ፡ይኼዳል፥ይበድልማል፤ኀይሉንም፡አምላክ፡ያደርገዋል።
12አቤቱ፥የተቀደስኽ፡አምላኬ፡ሆይ፥አንተ፡ከዘለዓለም፡ዠምሮ፡አልነበርኽምን፧እኛ፡ አንሞትም፤አቤቱ፥ለፍርድ፡ሠርተኸዋል፥ለተግሣጽም፡አድርገኸዋል።
13ዐይኖችኽ፡ክፉ፡እንዳያዩ፡ንጹሓን፡ናቸው፥ጠማምነትንም፡ትመለከት፡ዘንድ፡አትችልም፤አታላዮችንስ፡ ለምን፡ትመለከታለኽ፧ኀጢአተኛውስ፡ከርሱ፡ይልቅ፡ጻድቅ፡የኾነውን፡ሲውጠው፡ስለ፡ምን፡ዝም፡ትላለኽ፧
14ሰዎችንም፡እንደ፡ባሕር፡ዓሣዎች፥አለቃም፡እንደሌላቸው፡ተንቀሳቃሾች፡ለምን፡ታደርጋቸዋለኽ፧
15ዅሉን፡በመቃጥን፡ያወጣል፥በመረቡም፡ይይዛቸዋል፥በአሽክላውም፡ውስጥ፡ያከማቻቸዋል፤ስለዚህ፥ደስ፡ እያለው፡እልል፡ይላል።
16ዕድል፡ፈንታው፡በእነርሱ፡ሰብታለችና፥መብሉም፡በዝቷልና፥ስለዚህ፡ለመረቡ፡ይሠዋል፥ለአሽክላውም፡ ያጥናል።
17ስለዚህ፥መረቡን፡ይጥላልን፧አሕዛብንም፡ዘወትር፡ይገድል፡ዘንድ፡አይራራምን፧