1በመጠበቂያዬ፡ላይ፡እቆማለኹ፥በዐምባ፡ላይም፡እወጣለኹ፤የሚናገረኝንም፥ስለ፡ክርክሬም፡የምመልሰውን፡ ዐውቅ፡ዘንድ፡እመለከታለኹ።
2እግዚአብሔርም፡መለሰልኝ፡እንዲህም፡አለ፦አንባቢው፡ይፈጥን፡ዘንድ፡ራእዩን፡ጻፍ፥በጽላትም፡ላይ፡ ግለጠው።
3ራእዩ፡ገና፡እስከተወሰነው፡ጊዜ፡ነው፥ወደ፡ፍጻሜውም፡ይቸኵላል፥ርሱም፡አይዋሽም፤ቢዘገይም፡በርግጥ፡ ይመጣልና፥ታገሠው፤ርሱ፡አይዘገይም።
4እንሆ፥ነፍሱ፡ኰርታለች፥በውስጡም፡ቅን፡አይደለችም፤ጻድቅ፡ግን፡በእምነቱ፡በሕይወት፡ይኖራል።
5ርሱ፡አታላይና፡ኵሩ፡ሰው፡ነው፤በስፍራው፡ዐርፎ፡አይቀመጥም፤ሥሥቱን፡እንደ፡ሲኦል፡ያሰፋል፥ርሱም፡ እንደ፡ሞት፡አይጠግብም፤አሕዛብንም፡ዅሉ፡ወደ፡ርሱ፡ይሰበስባል፥ወገኖቹንም፡ዅሉ፡ወደ፡ርሱ፡ያከማቻል።
6እነዚህ፡ዅሉ፦ለርሱ፡ያልኾነውን፡ወደ፡ርሱ፡ለሚሰበስብ፡መያዣውንም፡ለራሱ፡የሚያበዛ፡ወዮለት! እስከ፡ መቼ፡ነው፧እያሉ፡ምሳሌ፡አይመስሉበትምን፧
7ተረትም፡አይተርቱበትምን፧የሚነክሱኽ፡ድንገት፡አይነሡብኽምን፧የሚያስጨንቁኽም፡ይነቃሉ፤ለእነርሱም፡ ብዝበዛ፡ትኾናለኽ።
8የሰውን፡ደም፡ስላፈሰስኽ፥በምድሪቱና፡በከተማዪቱም፡በርሷም፡በሚኖሩ፡ዅሉ፡ላይ፡ስላደረግኸው፡ ግፍ፥አንተ፡ብዙዎችን፡አሕዛብን፡በዝብዘኻልና፥ከአሕዛብ፡የቀሩት፡ዅሉ፡ይበዘብዙኻል።
9ከክፉ፡እንዲድን፡ጐዦውን፡በከፍታ፡ላይ፡ያደርግ፡ዘንድ፡ለቤቱ፡ክፉ፡ትርፍን፡ለሚሰበስብ፡ወዮለት!
10ብዙ፡አሕዛብን፡አጥፍተኻልና፥ለቤትኽ፡ዕፍረትን፡መክረኻል፥በነፍስኽም፡ላይ፡ኀጢአትን፡አድርገኻል።
11ድንጋይም፡ከግንብ፡ውስጥ፡ይጮኻል፥ዕንጨትም፡ከውቅር፡ውስጥ፡ይመልስለታል።
12ከተማን፡በደም፡ለሚሠራ፥ከተማንም፡በኀጢአት፡ለሚመሠርት፡ወዮለት!
13እንሆ፥አሕዛብ፡ስለ፡እሳት፡እንዲሠሩ፥ወገኖችም፡ስለ፡ከንቱነት፡እንዲደክሙ፡ከሰራዊት፡ጌታ፡ ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡የኾነ፡አይደለምን፧
14ውሃ፡ባሕርን፡እንደሚከድን፥ምድር፡የእግዚአብሔርን፡ክብር፡በማወቅ፡ትሞላለችና።
15ኀፍረተ፡ሥጋውን፡ለማየት፡ባልንጀራውን፡ለሚያጠጣ፥ክፉንም፡ለሚጨምርበት፥ለሚያሰክረውም፡ወዮለት!
16በክብር፡ፋንታ፡ዕፍረት፡ሞልቶብኻል፤አንተ፡ደግሞ፡ጠጥተኽ፡ተንገድገድ፤የእግዚአብሔር፡የቀኙ፡ጽዋ፡ ይመለስብኻል፥ዕፍረትም፡በክብርኽ፡ላይ፡ይኾናል።
17የሰውንም፡ደም፡ስላፈሰስኽ፥በምድሪቱና፡በከተማዪቱም፡በርሷም፡በሚኖሩ፡ዅሉ፡ላይ፡ስላደረግኸው፡ ግፍ፥በሊባኖስ፡ላይ፡የሠራኸው፡ግፍ፡ይከድንኻል፤የአራዊትም፡አደጋ፡ያስፈራራኻል።
18የተቀረጸውን፡ምስል፡ሠሪው፡የቀረጸው፡ለምን፡ጥቅም፡ነው፧ዲዳንም፡ጣዖት፡ይሠራ፡ዘንድ፡ሠሪው፡ የታመነበቱ፥ሐሰትን፡የሚያስተምር፡ቀልጦ፡የተሠራ፡ምን፡ይጠቅማል፧
19ዕንጨቱን፦ንቃ፥ዲዳውንም፡ድንጋይ፦ተነሣ፡ለሚለው፡ወዮለት! በእውኑ፡ይህ፡ ያስተምራልን፧እንሆ፥በወርቅና፡በብር፡ተለብጧል፥ምንም፡እስትንፋስ፡የለበትም።
20እግዚአብሔር፡ግን፡በተቀደሰ፡መቅደሱ፡አለ፤ምድርም፡ዅሉ፡በፊቱ፡ዝም፡ትበል።