1በይሁዳ፡ነገሥታት፡በዖዝያንና፡በኢዮአታም፡በአካዝና፡በሕዝቅያስም፡ዘመን፡በእስራኤልም፡ንጉሥ፡በዮአስ፡ ልጅ፡በኢዮርብዓም፡ዘመን፡ወደብኤሪ፡ልጅ፡ወደ፡ሆሴዕ፡የመጣ፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ይህ፡ነው፦
2እግዚአብሔር፡መዠመሪያ፡በሆሴዕ፡በተናገረ፡ጊዜ፥እግዚአብሔር፡ሆሴዕን፦ምድሪቱ፡ከእግዚአብሔር፡ ርቃ፡ታላቅ፡ግልሙትና፡ታደርጋለችና፡ኺድ፤ጋለሞታን፡ሴትና፡የግልሙትናን፡ልጆች፡ለአንተ፡ውሰድ፡ አለው።
3ርሱም፡ኼዶ፡የዴቤላይምን፡ልጅ፡ጎሜርን፡አገባ፤ርሷም፡ፀነሰች፡ወንድ፡ልጅንም፡ወለደችለት።
4እግዚአብሔርም፦ከጥቂት፡ዘመን፡በዃላ፡የኢይዝራኤልን፡ደም፡በኢዩ፡ቤት፡ላይ፡ እበቀላለኹና፥ከእስራኤልም፡ቤት፡መንግሥትን፡እሽራለኹና፡ስሙን፡ኢይዝራኤል፡ብለኽ፡ጥራው፤
5በዚያም፡ቀን፡በኢይዝራኤል፡ሸለቆ፡ውስጥ፡የእስራኤልን፡ቀስት፡እሰብራለኹ፡አለው።
6ደግሞ፡ፀነሰች፡ሴት፡ልጅንም፡ወለደች።እግዚአብሔርም፦ይቅር፡እላቸው፡ዘንድ፡የእስራኤልን፡ቤት፡ ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አልምርምና፡ስሟን፡ሎሩሃማ፡ብለኽ፡ጥራት፤
7ነገር፡ግን፥የይሁዳን፡ቤት፡እምራለኹ፤በአምላካቸውም፡በእግዚአብሔር፡አድናቸዋለኹ፡እንጂ፡በቀስት፡ ወይም፡በሰይፍ፡ወይም፡በሰልፍ፡ወይም፡በፈረሶች፡ወይም፡በፈረሰኛዎች፡አላድናቸውም፡አለው።
8ሎሩሃማም፡ጡት፡ባስጣለች፡ጊዜ፥ደግሞ፡ፀነሰች፡ወንድ፡ልጅንም፡ወለደች።
9እግዚአብሔርም፦ሕዝቤ፡አይደላችኹምና፥እኔም፡አምላክ፡አልኾናችኹምና፡ስሙን፡ሎዓሚ፡ብለኽ፡ ጥራው፡አለው።