Skip to content
← Job

Chapter 1 · Amharic

Job

1ዖፅ፡በሚባል፡አገር፡ስሙ፡ኢዮብ፡የተባለ፡አንድ፡ሰው፡ነበረ፤ያም፡ሰው፡ፍጹምና፡ ቅን፥እግዚአብሔርንም፡የሚፈራ፥ከክፋትም፡የራቀ፡ነበረ።

2ሰባትም፡ወንዶች፡ሦስትም፡ሴቶች፡ልጆች፡ተወልደውለት፡ነበር።

3ሀብቱም፡ሰባት፡ሺሕ፡በጎች፥ሦስት፡ሺሕም፡ግመሎች፥ዐምስት፡መቶም፡ጥማድ፡በሬ፥ዐምስት፡መቶም፡ እንስት፡አህያዎች፡ነበረ፥እጅግ፡ብዙም፡ባሪያዎች፡ነበሩት፤ያም፡ሰው፡በምሥራቅ፡ካሉ፡ሰዎች፡ዅሉ፡ይልቅ፡ ታላቅ፡ነበረ።

4ወንዶች፡ልጆቹም፡ኼደው፡በየተራ፡በያንዳንዳቸው፡ቤት፡ግብዣ፡ያደርጉ፡ነበር፤ሦስቱ፡እኅቶቻቸውም፡ ከነርሱ፡ጋራ፡ይበሉና፡ይጠጡ፡ዘንድ፡እነርሱ፡ልከው፡ይጠሯቸው፡ነበር።

5የግብዣውም፡ቀኖች፡ባለፉ፡ጊዜ፡ኢዮብ፦ምናልባት፡ልጆቼ፡በድለው፥እግዚአብሔርንም፡በልባቸው፡ ሰድበው፡ይኾናል፡ብሎ፡ይልክና፡ይቀድሳቸው፡ነበር፤ኢዮብም፡ማልዶ፡ተነሣ፥እንደ፡ቍጥራቸውም፡ዅሉ፡ የሚቃጠል፡መሥዋዕት፡አቀረበ።እንዲሁ፡ኢዮብ፡ዅልጊዜ፡ያደርግ፡ነበር።

6ከዕለታት፡አንድ፡ቀን፡እንዲህ፡ኾነ፤የአምላክ፡ልጆች፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ለመቆም፡መጡ፥ሰይጣንም፡ ደግሞ፡በመካከላቸው፡መጣ።

7እግዚአብሔርም፡ሰይጣንን፦ከወዴት፡መጣኽ፧አለው።ሰይጣንም፦ምድርን፡ዅሉ፡ዞርዃት፥በርሷም፡ ተመላለስኹ፡ብሎ፡ለእግዚአብሔር፡መለሰ።

8እግዚአብሔርም፡ሰይጣንን፦በእውኑ፡ባሪያዬን፡ኢዮብን፡ተመለከትኸውን፧በምድር፡ላይ፡እንደ፡ርሱ፡ ፍጹምና፡ቅን፥እግዚአብሔርንም፡የሚፈራ፥ከክፋትም፡የራቀ፡ሰው፡የለም፡አለው።

9ሰይጣንም፡ለእግዚአብሔር፡እንዲህ፡ብሎ፡መለሰለት፦በእውኑ፡ኢዮብ፡እግዚአብሔርን፡የሚፈራ፡በከንቱ፡ ነውን፧

10ርሱንና፡ቤቱን፡በዙሪያውም፡ያሉትን፡ዅሉ፡አላጠርኽለትምን፧የእጁን፡ሥራ፡ባርከኽለታል፥ከብቱም፡ በምድር፡ላይ፡በዝቷል።

11ነገር፡ግን፥እጅኽን፡ዘርግተኽ፡ያለውን፡ዅሉ፡ዳብስ፤በእውነት፡በፊትኽ፡ይሰድብኻል።

12እግዚአብሔርም፡ሰይጣንን፦እንሆ፥ለርሱ፡ያለው፡ዅሉ፡በእጅኽ፡ነው፥ነገር፡ግን፥በርሱ፡ላይ፡ እጅኽን፡አትዘርጋ፡አለው።ሰይጣንም፡ከእግዚአብሔር፡ፊት፡ወጣ።

13አንድ፡ቀንም፡እንዲህ፡ኾነ፤የኢዮብ፡ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆች፡በታላቅ፡ወንድማቸው፡ቤት፡ይበሉና፡ የወይን፡ጠጅ፡ይጠጡ፡ነበር።

14መልክተኛም፡ወደ፡ኢዮብ፡መጥቶ፦በሬዎች፡ዕርሻ፡ያርሱ፥በአጠገባቸውም፡አህያዎች፡ይሰማሩ፡ነበር፤

15የሳባም፡ሰዎች፡አደጋ፡ጣሉ፥ወሰዷቸውም፥ብላቴናዎቹንም፡በሰይፍ፡ስለት፡ገደሉ፤እኔም፡እነግርኽ፡ ዘንድ፡ብቻዬን፡አመለጥኹ፡አለው።

16ርሱም፡ገና፡ሲናገር፡ሌላ፡መጥቶ፦የእግዚአብሔር፡እሳት፡ከሰማይ፡ወደቀች፥በጎቹንም፡ አቃጠለች፥ጠባቂዎችንም፡በላች፤እኔም፡እነግርኽ፡ዘንድ፡ብቻዬን፡አመለጥኹ፡አለው።

17ርሱም፡ገና፡ሲናገር፡ሌላ፡መጥቶ፦ከለዳውያን፡በሦስት፡ረድፍ፡ተከፍለው፡በግመሎች፡ላይ፡አደጋ፡ ጣሉ፥ወሰዷቸውም፥ብላቴናዎቹንም፡በሰይፍ፡ስለት፡ገደሉ፤እኔም፡እነግርኽ፡ዘንድ፡ብቻዬን፡አመለጥኹ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org አለው።

18ርሱም፡ገና፡ሲናገር፡ሌላ፡መጥቶ፦ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆችኽ፡በታላቅ፡ወንድማቸው፡ቤት፡ይበሉና፡ የወይን፡ጠጅ፡ይጠጡ፡ነበር፤

19እንሆም፥ዐውሎ፡ነፋስ፡ከምድረ፡በዳ፡መጥቶ፡የቤቱን፡አራቱን፡ማእዘን፡መታው፥በብላቴናዎቹም፡ላይ፡ ወደቀ፥ሞቱም፤እኔም፡እነግርኽ፡ዘንድ፡ብቻዬን፡አመለጥኹ፡አለው።

20ኢዮብም፡ተነሣ፡መጐናጸፊያውንም፡ቀደደ፥ራሱንም፡ተላጨ፥በምድርም፡ላይ፡ተደፍቶ፡ሰገደ፤

21እንዲህም፡አለ፦ዕራቍቴን፡ከእናቴ፡ማሕፀን፡ወጥቻለኹ፥ዕራቍቴንም፡ወደዚያ፡ እመለሳለኹ፤እግዚአብሔር፡ሰጠ፥እግዚአብሔርም፡ነሣ፤የእግዚአብሔር፡ስም፡የተባረከ፡ይኹን።

22በዚህ፡ዅሉ፡ኢዮብ፡አልበደለም፥ለእግዚአብሔርም፡ስንፍናን፡አልሰጠም።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source