1በይሁዳ፡ነገሥታት፡በኢዮአታምና፡በአካዝ፡በሕዝቅያስም፡ዘመን፡ወደ፡ሞሬታዊው፡ወደ፡ሚክያስ፡ የመጣው፥ስለ፡ሰማርያና፡ስለ፡ኢየሩሳሌም፡ያየው፥የእግዚአብሔር፡ቃል፡ይህ፡ነው፦
2እናንተ፡አሕዛብ፡ዅሉ፥ስሙ፤ምድርም፡መላ፟ዋም፡ታድምጥ፤ጌታ፡እግዚአብሔርም፥ርሱም፡በቅዱስ፡ መቅደሱ፡የኾነ፡ጌታ፥ይመስክርባችኹ።
3እንሆ፥እግዚአብሔር፡ከስፍራው፡ይወጣል፥ወርዶም፡በምድር፡ከፍታዎች፡ላይ፡ይረግጣል።
4ተራራዎችም፡በእሳት፡ፊት፡እንዳለ፡ሠም፥በገደልም፡ወርዶ፡እንደሚፈስ፟፡ውሃ፥በበታቹ፡ ይቀልጣሉ፥ሸለቆዎችም፡ይሰነጠቃሉ።
5ይህ፡ዅሉ፡ስለያዕቆብ፡በደልና፡ስለእስራኤል፡ቤት፡ኀጢአት፡ነው።የያዕቆብም፡በደል፡ምንድር፡ ነው፧ሰማርያ፡አይደለችምን፧የይሁዳስ፡የኰረብታው፡መስገጃ፡ምንድር፡ነው፧ኢየሩሳሌም፡አይደለችምን፧
6ስለዚህ፥ሰማርያን፡በሜዳ፡እንደሚገኝ፡የድንጋይ፡ክምር፥ወይን፡እንደሚተከልበትም፡ስፍራ፡ አደርጋታለኹ፤ድንጋዮቿንም፡ወደ፡ሸለቆ፡እወረውራለኹ፥መሠረቶቿንም፡እገልጣለኹ።
7የተቀረጹትም፡ምስሎቿ፡ይደቃ፟ሉ፥በግልሙትና፡ያገኘችው፡ዋጋ፡ዅሉ፡በእሳት፡ይቃጠላል፥ጣዖታቷንም፡ ዅሉ፡አጠፋለኹ፤በግልሙትና፡ዋጋ፡ሰበሰበቻቸው፥ወደ፡ግልሙትናም፡ዋጋ፡ይመለሳሉና።
8ስለዚህ፡ነገር፡ዋይ፡ብላ፡ታለቅሳለች፥ባዶ፡እግሯንና፡ዕራቍቷን፡ኾና፡ትኼዳለች፤እንደ፡ቀበሮ፡ ታለቅሳለች፥እንደ፡ሰጐንም፡ዋይ፡ትላለች፤
9ቍስሏ፡የማይፈወስ፡ነውና፤እስከ፡ይሁዳም፡ደርሷልና፥ወደሕዝቤም፡በር፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ቀርቧልና።
10በጌት፡ላይ፡አታውሩ፤በአኮ፡ላይ፡እንባን፡አታድርጉ፤በቤትዓፍራ፡በትቢያ፡ላይ፡ተንከባለሉ።
11በሻፊር፡የምትቀመጪ፡ሆይ፥በዕራቍትነትሽና፡በዕፍረት፡ዕለፊ፤በጸዓናን፡የምትቀመጠው፡ አልወጣችም፤የቤትኤጼል፡ልቅሶ፡ከእናንተ፡ዘንድ፡መኖሪያውን፡ይወስዳል።
12ክፉ፡ነገር፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡እስከኢየሩሳሌም፡በር፡ድረስ፡ወርዷልና፥በማሮት፡የምትቀመጠው፡ በጎነትን፡ትጠባበቃለች።
13በለኪሶ፡የምትቀመጪ፡ሆይ፥ሠረገላውን፡ለፈረስ፡እሰሪ፤ርሷ፡ለጽዮን፡ሴት፡ልጅ፡የኀጢአት፡ መዠመሪያ፡ነበረች፤የእስራኤል፡በደል፡ባንቺ፡ዘንድ፡ተገኝቷልና።
14ስለዚህ፥ትሎት፡ለሞሬሼትጌት፡ትሰጪያለሽ፤የአክዚብ፡ቤቶች፡ለእስራኤል፡ነገሥታት፡አታላይ፡ይኾናሉ።
15በመሪሳ፡የምትቀመጪ፡ሆይ፥ወራሽ፡አመጣብሻለኹ፤የእስራኤል፡ክብር፡ወደ፡ዓዶላም፡ይመጣል።
16ተማርከው፡ከአንቺ፡ዘንድ፡ወጥተዋልና፥ስለተድላሽ፡ልጆች፡ራስሽን፡ንጪ፥ጠጕርሽንም፡ ተቈረጪ፤ቡሓነትሽንም፡እንደ፡ንስር፡አስፊ።