1ስለ፡ነነዌ፡የተነገረ፡ሸክም፤የኤልቆሻዊው፡የናሖም፡የራእዩ፡መጽሐፍ፡ይህ፡ነው።
2እግዚአብሔር፡ቀናተኛና፡ተበቃይ፡አምላክ፡ነው፤እግዚአብሔር፡ተበቃይና፡መዓትን፡የተሞላ፡ ነው፤እግዚአብሔር፡ተቃዋሚዎቹን፡ይበቀላል፥ለጠላቶቹም፡ቍጣውን፡ይጠብቃል።
3እግዚአብሔር፡ትዕግሥተኛ፥ኀይሉም፡ታላቅ፡ነው፥በደለኛውንም፦ንጹሕ፡ነኽ፡አይልም፤እግዚአብሔር፡ በወጀብና፡በዐውሎ፡ነፋስ፡ውስጥ፡መንገድ፡አለው፥ደመናም፡የእግሩ፡ትቢያ፡ነው።
4ባሕሩንም፡ይገሥጻታል፥ያደርቃትማል፥ወንዞችንም፡ዅሉ፡ያደርቃል፤ባሳንና፡ቀርሜሎስም፡ ላልተዋል፥የሊባኖስም፡አበባ፡ጠውልጓል።
5ተራራዎችም፡ከርሱ፡የተነሣ፡ታወኩ፥ኰረብታዎችም፡ቀለጡ፤ምድርና፡ዓለም፡የሚኖሩበትም፡ዅሉ፡ከፊቱ፡ ተናወጡ።
6በቍጣው፡ፊት፡የሚቆም፡ማን፡ነው፧የቍጣውንም፡ትኵሳት፡ማን፡ይታገሣል፧መዓቱ፡እንደ፡እሳት፡ ይፈሳ፟ል፥ከርሱም፡የተነሣ፡አለቶች፡ተሰነጠቁ።
7እግዚአብሔር፡መልካም፡ነው፥በመከራ፡ቀንም፡መሸሸጊያ፡ነው፤በርሱ፡የሚታመኑትንም፡ያውቃል።
8ስፍራዋን፡ግን፡በሚያጥለቀልቅ፡ጐርፍ፡ፈጽሞ፡ያጠፋታል፥ጠላቶቹንም፡ወደ፡ጨለማ፡ያሳድዳቸዋል።
9በእግዚአብሔር፡ላይ፡የምታስቡት፡ምንድር፡ነው፧ርሱ፡ፈጽሞ፡ያጠፋል፥መከራም፡ኹለተኛ፡አይነሣም።
10ርስ፡በርሳቸው፡እንደ፡ተመሰቃቀለ፡ሾኽ፡ቢኾኑ፥በመጠጣቸውም፡ቢሰክሩ፡እንደ፡ደረቅ፡ገለባ፡ ፈጽመው፡ይጠፋሉ።
11በእግዚአብሔር፡ላይ፡በክፉ፡የሚያስብ፥ክፋትን፡የሚመክር፥ከአንተ፡ዘንድ፡ወጥቷል።
12እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ኀይለኛዎችና፡ብዙዎች፡ቢኾኑ፡እንዲሁ፡ይቈረጣሉ፥ርሱም፡ ያልቃል።እኔም፡አስጨንቄኻለኹ፥ነገር፡ግን፥ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አላስጨንቅኽም።
13አኹንም፡ቀንበሩን፡ከአንተ፡እሰብራለኹ፥እስራትኽንም፡እበጥሳለኹ።
14እግዚአብሔርም፡ከስምኽ፡ማንም፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡እንዳይዘራ፡ስለ፡አንተ፡አዟ፟ል፤ከአምላኮችኽ፡ቤት፡ የተቀረጸውንና፡ቀልጦ፡የተሠራውን፡ምስል፡አጠፋለኹ፤አንተም፡የተጠቃኽ፡ነኽና፥መቃብርኽን፡እምሳለኹ።
15እንሆ፥የምሥራችን፡የሚያመጣ፡ሰላምንም፡የሚያወራ፡ሰው፡እግር፡በተራራዎች፡ላይ፡ነው! ይሁዳ፡ ሆይ፥አጥፊው፡ፈጽሞ፡ጠፍቷልና፥ከእንግዲህም፡ወዲህ፡ባንተ፡ዘንድ፡አያልፍምና፡ዓመት፡በዓሎችኽን፡ አድርግ፥ስእለቶችኽን፡ክፈል።