1ለደም፡ከተማ፡ወዮላት! በዅለንተናዋ፡ሐሰትና፡ቅሚያ፡ሞልቶባታል፤ንጥቂያ፡ከርሷ፡አያልቅም።
2የዐለንጋ፡ድምፅ፥የመንኰራኵርም፡ድምፅ፥የፈረሶችም፡ኰቴ፥የፈጣን፡ሠረገላም፡ጩኸት፡ተሰምቷል፤
3ፈረሰኛው፡ይጋልባል፥ሰይፍም፡ይንቦገቦጋል፥ጦርም፡ይብለጨለጫል፤የተገደሉትም፡ይበዛሉ፥በድኖችም፡ በክምር፡ይከመራሉ፥ሬሳቸውም፡አይቈጠርም፤በሬሳቸውም፡ይሰናከላሉ።
4ስለተዋበችው፡ጋለሞታ፡ግልሙትና፡ብዛት፡ይህ፡ኾኗል፤ርሷም፡በመተቷ፡እጅግ፡በለጠች፥አሕዛብንም፡ በግልሙትናዋ፥ወገኖችንም፡በመተቷ፡ሸጠች።
5እንሆ፥ባንቺ፡ላይ፡ነኝ፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፥ልብስሽን፡በፊትሽ፡እገልጣለኹ፤ኅፍረተ፡ ሥጋሽንም፡ለአሕዛብ፥ነውርሽንም፡ለመንግሥታት፡አሳያለኹ።
6ርኵሰትንም፡በላይሽ፡እጥላለኹ፥እንቅሽማለኹ፥ማላገጫም፡አደርግሻለኹ።
7የሚያይሽም፡ዅሉ፡ከአንቺ፡ሸሽቶ፦ነነዌ፡ባድማ፡ኾናለች፤የሚያለቅስላትስ፡ማን፡ነው፧የሚያጽናናትንስ፡ ከወዴት፡እፈልጋለኹ፧ይላል።
8አንቺ፡በመስኖች፡መካከል፡ከተቀመጠችው፥ውሃም፡በዙሪያዋ፡ከነበራት፥ምሽጓም፡ባሕር፡ ከነበረ፥ቅጥሯም፡በባሕር፡ውስጥ፡ከነበረ፡ከኖእ፡ዐሞን፡ትበልጫለሽን፧ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
9ኢትዮጵያና፡ግብጽ፡የማይቈጠር፡ኀይሏ፡ነበሩ፤ፉጥና፡ልብያ፡ረዳቶቿ፡ነበሩ።
10ርሷ፡ግን፡ተማርካ፡ፈለሰች፤ሕፃናቷ፡በመንገድ፡ዅሉ፡ራስ፡ላይ፡ተፈጠፈጡ፤በከበርቴዎቿም፡ላይ፡ዕጣ፡ ተጣጣሉ፥ታላላቆቿም፡ዅሉ፡በሰንሰለት፡ታሰሩ።
11አንቺም፡ትሰክሪያለሽ፡ወራዳም፡ትኾኛለሽ፤አንቺ፡ደግሞ፡ከጠላት፡የተነሣ፡መጠጊያን፡ትፈልጊያለሽ።
12ዐምባሽ፡ዅሉ፡የመዠመሪያውን፡የበሰለ፡ፍሬ፡እንደ፡ያዙ፡እንደ፡በለስ፡ዛፎች፡ነው፤ቢወዛወዝ፡ በሚበላው፡አፍ፡ውስጥ፡ይወድቃል።
13እንሆ፥በመካከልሽ፡ያሉ፡ሕዝብሽ፡ሴቶች፡ናቸው፤የአገርሽ፡በሮች፡ለጠላቶችሽ፡ፈጽሞ፡ ተከፍተዋል፥እሳትም፡መወርወሪያዎችኽን፡በልቷል።
14ከበ፟ው፡ያስጨንቁሻልና፥ውሃን፡ቅጂ፤ዐምባሽን፡አጠንክሪ፤ወደ፡ጭቃ፡ገብተሽ፡ርገጪ፤የጡብን፡ መሠሪያ፡ያዢ።
15በዚያ፡እሳት፡ይበላሻል፥ሰይፍ፡ያጠፋሻል፥እንደ፡ደጐብያ፡ይበላሻል፤እንደ፡ደጐብያ፡ብዢ፥እንደ፡ አንበጣም፡ተባዢ።
16ነጋዴዎችሽን፡ከሰማይ፡ከዋክብት፡ይልቅ፡አበዛሽ፤ደጐብያ፡ተዘረጋ፥በረረም።
17ባንቺ፡ዘንድ፡ዘውድ፡የጫኑት፡እንደ፡አንበጣ፥አለቃዎችሽም፡እንደሚንቀሳቀሱ፡ኵብኵባዎች፡ ናቸው፤በብርድ፡ቀን፡በቅጥር፡ውስጥ፡ይቀመጣሉ፥ፀሓይም፡በወጣች፡ጊዜ፡ያኰበኵባሉ፤ስፍራቸው፡በየት፡ እንደ፡ኾነ፡አይታወቅም።
18የአሶር፡ንጉሥ፡ሆይ፥እረኛዎችኽ፡አንቀላፍተዋል፤መኳንንቶችኽም፡ዐርፈዋል፤ሕዝብኽም፡በተራራዎች፡ ላይ፡ተበትኗል፥የሚሰበስበውም፡የለም።
19ስብራትኽ፡አይፈወስም፥ቍስልኽም፡ክፉ፡ነው፤ወሬኽንም፡የሚሰሙ፡ዅሉ፡እጃቸውን፡ባንተ፡ላይ፡ ያጨበጭባሉ፤ክፋትኽ፡ዅልጊዜ፡ያላለፈችበት፡ሰው፡ማን፡ነውና፨ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org