Skip to content
← Nehemiah

Chapter 13 · Amharic

Nehemiah

1በዚያም፡ቀን፡የሙሴን፡መጽሐፍ፡በሕዝቡ፡ዦሮ፡አነበቡ፤አሞናውያንና፡ሞዐባውያንም፡ወደእግዚአብሔር፡ ጉባኤ፡ለዘለዓለም፡እንዳይገቡ፡የሚል፡በዚያ፡ተገኘ።

2የእስራኤልን፡ልጆች፡በእንጀራና፡በውሃ፡ስላልተቀበሏቸውና፡ይረግማቸው፡ዘንድ፡በለዓምን፡ስለ፡ገዙባቸው፡ ነው፤ነገር፡ግን፥አምላካችን፡ርግማኑን፡ወደ፡በረከት፡መለሰው።

3ሕጉንም፡በሰሙ፡ጊዜ፡ድብልቁን፡ሕዝብ፡ዅሉ፡ከእስራኤል፡ለዩ።

4ከዚህም፡አስቀድሞ፡በአምላካችን፡ቤት፡ጓዳዎች፡ላይ፡ተሾሞ፡የነበረው፡ካህኑ፡ኤልያሴብ፡ከጦብያ፡ጋራ፡ ተወዳጅቶ፥

5ለሌዋውያን፥ለመዘምራን፥ለበረኛዎቹ፡እንደ፡ሕጉ፡የተሰጣቸውን፡የእኽሉን፡ቍርባንና፡ ዕጣኑን፥ዕቃዎቹንም፥የእኽሉንና፡የወይኑን፡የዘይቱንም፡ዓሥራት፥ለካህናቱም፡የኾነውን፡የማንሣት፡ቍርባን፡ አስቀድሞ፡ያስቀመጡበትን፡ታላቁን፡ጓዳ፡አዘጋጅቶለት፡ነበር።

6እኔ፡ግን፡በባቢሎን፡ንጉሥ፡በአርጤክስስ፡በሠላሳ፡ኹለተኛው፡ዓመት፡ወደ፡ንጉሡ፡ኼጄ፡ነበርና፥በዚህ፡ ጊዜ፡በኢየሩሳሌም፡አልነበርኹም።ከጥቂት፡ዘመንም፡በዃላ፡የንጉሡን፡ፈቃድ፡ለመንኹ፤

7ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡መጣኹ፤ኤልያሴብም፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡አደባባይ፡ለጦብያ፡ጓዳውን፡በማዘጋጀት፡ ያደረገውን፡ክፉ፡ነገር፡አስተዋልኹ።

8እጅግም፡አስከፋኝ፤የጦብያንም፡የቤቱን፡ዕቃ፡ዅሉ፡ከጓዳ፡ወደ፡ውጪ፡ጣልኹ።

9ጓዳዎቹንም፡እንዲያነጹ፡አዘዝኹ፤የእግዚአብሔርንም፡ቤት፡ዕቃዎች፡የእኽሉንም፡ቍርባን፡ዕጣኑንም፡ መልሼ፡በዚያ፡አገባኹ።

10ለሌዋውያንም፡ዕድል፡ፈንታቸው፡እንዳልተሰጠ፥የሚያገለግሉትም፡ሌዋውያንና፡መዘምራን፡እያንዳንዱ፡ ወደ፡ዕርሻው፡እንደ፡ኼዱ፡ተመለከትኹ።

11እኔም፦የእግዚአብሔር፡ቤት፡ስለ፡ምን፡ተተወ፧ብዬ፡ከአለቃዎቹ፡ጋራ፡ ተከራከርኹ።ሰበሰብዃቸውም፥በየስፍራቸውም፡አቆምዃቸው።

12ይሁዳም፡ዅሉ፡የእኽሉንና፡የወይኑን፡የዘይቱንም፡ዓሥራት፡ወደዕቃ፡ቤቶች፡አመጡ።

13በዕቃ፡ቤቶችም፡ላይ፡ካህኑን፡ሰሌምያን፥ጸሓፊውንም፡ሳዶቅን፥ከሌዋውያኑም፡ፈዳያን፡ሾምኹ፤ከነርሱም፡ ጋራ፡የመታንያ፡ልጅ፡የዘኩር፡ልጅ፡ሐናን፡ነበረ፤እነርሱም፡የታመኑ፡ኾነው፡ተገኙ፥ሥራቸውም፡ ለወንድሞቻቸው፡ማከፋፈል፡ነበረ።

14አምላኬ፡ሆይ፥ስለዚህ፡ዐስበኝ፤ለአምላኬም፡ቤት፡ያደረግኹትን፡ወረታዬን፡አታጥፋ።

15በዚያም፡ወራት፡በይሁዳ፡በሰንበት፡ቀን፡የወይን፡መጥመቂያን፡የሚረግጡትን፥ነዶም፡ የሚከመሩትን፥የወይኑን፡ጠጅና፡የወይኑን፡ዘለላ፡በለሱንም፡ልዩ፡ልዩም፡ዐይነት፡ሸክም፡በአህያዎች፡ላይ፡ የሚጭኑትን፥በሰንበትም፡ቀን፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡የሚያስገቡትን፡አየኹ፤ገበያ፡ባደረጉበትም፡ቀን፡ አስመሰከርኹባቸው።

16ደግሞም፡በርሷ፡የተቀመጡ፡የጢሮስ፡ሰዎች፡ነበሩ፤እነርሱም፡ዓሣዎችን፡ልዩ፡ልዩም፡ዐይነት፡ሸቀጥ፡ አምጥተው፡በሰንበት፡ቀን፡በኢየሩሳሌም፡ለይሁዳ፡ልጆች፡ይሸጡ፡ነበር።

17ከይሁዳም፡ታላላቆች፡ጋራ፡ተከራከርኹና፦ይህ፡የምታደርጉት፡ክፉ፡ነገር፡ምንድር፡ነው፧የሰንበትንስ፡ ቀን፡ታረክሳላችኹን፧

18አባቶቻችኹ፡እንደዚህ፡አድርገው፡አልነበረምን፧አምላካችንስ፡ይህን፡ክፉ፡ነገር፡ዅሉ፡በእኛና፡በዚህ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ከተማ፡ላይ፡አምጥቶ፡አልነበረምን፧እናንተም፡ሰንበትን፡በማርከሳችኹ፡በእስራኤል፡ላይ፡መዓትን፡ ትጨምራላችኹ፡አልዃቸው።

19ከዚህ፡በዃላ፡ከሰንበት፡በፊት፡በኢየሩሳሌም፡በሮች፡ድንግዝግዝታ፡በኾነ፡ጊዜ፡በሮቿ፡ እንዲዘጉ፥ሰንበትም፡እስኪያልፍ፡ድረስ፡እንዳይከፈቱ፡አዘዝኹ።በሰንበትም፡ቀን፡ሸክም፡እንዳይገባ፡ ከብላቴናዎቼ፡በዐያሌዎቹ፡በሮቿን፡አስጠበቅኹ።

20ዅሉም፡አንድ፡ወይም፡ኹለት፡ጊዜ፡በኢየሩሳሌም፡ውጭ፡ዐድረው፥ገበያ፡አድርገው፡ነበር።

21እኔም፡አስመሰከርኹባቸውና፦በቅጥሩ፡ውጭ፡ለምን፡ታድራላችኹ፧እንደ፡ገና፡ብታደርጉት፡እጆቼን፡ አነሣባችዃለኹ፡አልዃቸው።ከዚያም፡ወዲያ፡በሰንበት፡ቀን፡እንደ፡ገና፡አልመጡም።

22ሌዋውያኑንም፡ራሳቸውን፡እንዲያነጹ፥መጥተውም፡በሮቹን፡እንዲጠብቁ፥የሰንበትንም፡ቀን፡እንዲቀድሱ፡ ነገርዃቸው።አምላኬ፡ሆይ፥ስለዚህ፡ደግሞ፡ዐስበኝ፥እንደ፡ምሕረትኽም፡ብዛት፡ራራልኝ።

23ደግሞም፡በዚያ፡ወራት፡የአዛጦንና፡የዐሞንን፡የሞዐብንም፡ሴቶች፡ያገቡትን፡አይሁድ፡አየኹ።

24ከልጆቻቸውም፡እኩሌቶቹ፡በአዛጦን፡ቋንቋ፡ይናገሩ፡ነበር፥በአይሁድም፡ቋንቋ፡መናገር፡አያውቁም፡ ነበር።

25ከነርሱም፡ጋራ፡ተከራከርኹ፥ረገምዃቸውም፤ከነርሱም፡ዐያሌዎቹን፡መታኹ፥ጠጕራቸውንም፡ ነጨኹ፥እንዲህም፡ብዬ፡በእግዚአብሔር፡አማልዃቸው።ሴቶች፡ልጆቻችኹን፡ለወንዶች፡ልጆቻቸው፡ አትስጡ፥ሴቶች፡ልጆቻቸውንም፡ለእናንተና፡ለልጆቻችኹ፡አትውሰዱ።

26የእስራኤል፡ንጉሥ፡ሰሎሞን፡በዚህ፡ነገር፡ኀጢአት፡አድርጎ፡የለምን፧በብዙ፡አሕዛብም፡መካከል፡እንደ፡ ርሱ፡ያለ፡ንጉሥ፡አልነበረም፥በአምላኩም፡ዘንድ፡የተወደደ፡ነበረ፥እግዚአብሔርም፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ላይ፡ አንግሦት፡ነበር፤ርሱንም፡እንኳ፡እንግዳዎች፡ሴቶች፡አሳ፟ቱት።

27በእውኑ፡ይህን፡ዅሉ፡ታላቅ፡ክፋት፡እንሠራ፥እንግዳዎችንም፡ሴቶች፡በማግባት፡አምላካችን፡እንበድል፡ ዘንድ፡እናንተን፡እንስማ፧

28ከዋነኛውም፡ካህን፡ከኤልያሴብ፡ልጅ፡ከዮአዳ፡ልጆች፡አንዱ፡ለሖሮናዊው፡ለሰንባላጥ፡ዐማች፡ ነበረ፤ከእኔም፡ዘንድ፡አባረርኹት።

29አምላኬ፡ሆይ፥ክህነትን፡የክህነትንና፡የሌዋውያንንም፡ቃል፡ኪዳን፡ስላፈረሱ፡ዐስባቸው።

30ከእንግዳ፡ነገርም፡ዅሉ፡አነጻዃቸው፤ለካህናቱና፡ለሌዋውያኑም፡እያንዳንዳቸው፡በየሰሞናቸው፥

31በየጊዜያቸውም፡ለዕንጨት፡ቍርባን፡ለበኵራቱም፡ሥርዐት፡አደረግኹ።አምላኬ፡ሆይ፥በመልካም፡ዐስበኝ፨ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source