1በዳርዮስ፡በኹለተኛው፡ዓመት፡በስምንተኛው፡ወር፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ወደአዶ፡ልጅ፡ወደበራክዩ፡ልጅ፡ ወደ፡ነቢዩ፡ወደ፡ዘካርያስ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
2እግዚአብሔር፡በአባቶቻችኹ፡ላይ፡እጅግ፡ተቈጥቶ፡ነበር።
3ስለዚህ፥እንዲህ፡በላቸው፦የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ወደ፡እኔ፡ተመለሱ፥ይላል፡ የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፥እኔም፡ወደ፡እናንተ፡እመለሳለኹ፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
4የቀደሙት፡ነቢያት፡ለአባቶቻችኹ፡እንዲህ፡ብለው፡ሰብከዋል፦የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ ይላል፦ከክፉ፡መንገዳችኹና፡ከክፉ፡ሥራችኹ፡ተመለሱ፤እነርሱ፡ግን፡አልሰሙም፥እኔንም፡ አላደመጡም፤እንደ፡እነርሱ፡አትኹኑ፥ይላል፡እግዚአብሔር።
5አባቶቻችኹ፡ወዴት፡ናቸው፧ነቢያትስ፡ለዘለዓለም፡በሕይወት፡ይኖራሉን፧
6ለባሪያዎቼስ፡ለነቢያት፡ያዘዝዃቸው፡ቃሎቼና፡ሥርዐቴ፡በአባቶቻችኹ፡ላይ፡አልደረሱምን፧እነርሱም፡ ተመልሰው፦የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡በመንገዳችንና፡በሥራችን፡መጠን፡ያደርግብን፡ዘንድ፡እንዳሰበ፡ እንዲሁ፡አድርጎብናል፡አሉ።
7በዳርዮስ፡በኹለተኛው፡ዓመት፡ሳባጥ፡በሚባል፡በዐሥራ፡አንደኛው፡ወር፡በኻያ፡አራተኛው፡ቀን፡ የእግዚአብሔር፡ቃል፡ወደአዶ፡ልጅ፡ወደበራክዩ፡ልጅ፡ወደ፡ነቢዩ፡ወደ፡ዘካርያስ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
8እንሆም፥አንድ፡ሰው፡በመጋላ፡ፈረስ፡ተቀምጦ፡በሌሊት፡አየኹ፥ርሱም፡በሸለቆው፡ውስጥ፡ባሉ፡ በባርሰነት፡ዛፎች፡መካከል፡ቆሞ፡ነበር፤በስተዃላውም፡መጋላና፡ሐመር፡ዐምባላይም፡ፈረሶች፡ነበሩ።
9እኔም፦ጌታዬ፡ሆይ፥እነዚህ፡ምንድር፡ናቸው፧አልኹ።ከእኔም፡ጋራ፡ይነጋገር፡የነበረው፡ መልአክ፦እነዚህ፡ምን፡እንደ፡ኾኑ፡አሳይኻለኹ፡አለኝ።
10በባርሰነት፡ዛፎች፡መካከልም፡ቆሞ፡የነበረው፡ሰው፦እነዚህ፡በምድር፡ላይ፡ይመላለሱ፡ዘንድ፡ እግዚአብሔር፡የላካቸው፡ናቸው፡ብሎ፡መለሰ።
11በባርሰነት፡ዛፎች፡መካከልም፡ቆሞ፡የነበረውን፡የእግዚአብሔርን፡መልአክ፦በምድር፡ላይ፡ ተመላለስን፥እንሆም፥ምድር፡ዅሉ፡ዝም፡ብላ፡ዐርፋ፡ተቀምጣለች፡ብለው፡መለሱለት።
12የእግዚአብሔርም፡መልአክ፡መልሶ፦አቤቱ፥የሰራዊት፡ጌታ፡ሆይ፥እነዚህ፡ሰባ፡ዓመት፡የተቈጣኻቸውን፡ ኢየሩሳሌምንና፡የይሁዳን፡ከተማዎች፡የማትምራቸው፡እስከ፡መቼ፡ነው፧አለ።
13እግዚአብሔርም፡መልሶ፡ከእኔ፡ጋራ፡ይነጋገር፡ለነበረው፡መልአክ፡በመልካምና፡በሚያጽናና፡ቃል፡ ተናገረው።
14ስለዚህም፡ከእኔ፡ጋራ፡ይነጋገር፡የነበረው፡መልአክ፡እንዲህ፡አለኝ፦ስበክ፡እንዲህም፡በል፦የሰራዊት፡ ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እኔ፡በታላቅ፡ቅንአት፡በኢየሩሳሌምና፡በጽዮን፡ቀንቻለኹ።
15እኔ፡ጥቂት፡ብቻ፡ተቈጥቼ፡ሳለኹ፡እነርሱ፡ክፋትን፡ስላገዙት፥ባልተቸገሩት፡አሕዛብ፡ላይ፡እጅግ፡ ተቈጥቻለኹ።
16ስለዚህ፥እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ወደ፡ኢየሩሳሌም፡በምሕረት፡ተመልሻለኹ፤ቤቴ፡ ይሠራባታል፤በኢየሩሳሌምም፡ላይ፡ገመድ፡ይዘረጋበታል፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
17ደግሞም፡እንዲህ፡ስትል፡ስበክ፦የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ከተማዎቼ፡ደግሞ፡ በበጎ፡ነገር፡ይረካሉ፤እግዚአብሔርም፡ደግሞ፡ጽዮንን፡ያጽናናል፥ኢየሩሳሌምንም፡ደግሞ፡ይመርጣል።
18ዐይኖቼንም፡አንሥቼ፥እንሆ፥አራት፡ቀንዶች፡አየኹ።
19ከእኔም፡ጋራ፡ይነጋገር፡የነበረውን፡መልአክ፦እነዚህ፡ምንድር፡ናቸው፧አልኹት።ርሱም፦እነዚህ፡ ይሁዳንና፡እስራኤልን፡ኢየሩሳሌምንም፡የበተኑ፡ቀንዶች፡ናቸው፡ብሎ፡መለሰልኝ።
20እግዚአብሔርም፡አራት፡ጠራቢዎች፡አሳየኝ።
21እኔም፦እነዚህ፡የመጡት፡ምን፡ሊሠሩ፡ነው፧አልኹ።ርሱም፦አንድ፡ሰው፡ራሱን፡እስከማያነሣ፡ ድረስ፡እነዚህ፡ቀንዶች፡ይሁዳን፡የበተኑ፡ናቸው፤እነዚህ፡ግን፡ሊያስፈራሯቸው፥የይሁዳንም፡አገር፡ይበትኑ፡ ዘንድ፡ቀንዳቸውን፡ያነሡትን፡የአሕዛብን፡ቀንዶች፡ሊጥሉ፡መጥተዋል፡ብሎ፡ተናገረ።