1እንሆ፥የእግዚአብሔር፡ቀን፡ይመጣል፥ብዝበዛሽንም፡በውስጥሽ፡ይካፈላሉ።
2አሕዛብንም፡ዅሉ፡በኢየሩሳሌም፡ላይ፡ለሰልፍ፡እሰበስባለኹ፤ከተማዪቱም፡ትያዛለች፥ቤቶችም፡ ይበዘበዛሉ፥ሴቶችም፡ይነወራሉ፤የከተማዪቱም፡እኩሌታ፡ለምርኮ፡ይወጣል፥የቀረው፡ሕዝብ፡ግን፡ከከተማ፡ አይጠፋም።
3እግዚአብሔርም፡ይወጣል፥በሰልፍም፡ቀን፡እንደ፡ተዋጋ፡ከነዚያ፡አሕዛብ፡ጋራ፡ይዋጋል።
4በዚያም፡ቀን፡እግሮቹ፡በኢየሩሳሌም፡ትይዩ፡በምሥራቅ፡በኩል፡ባለው፡በደብረ፡ዘይት፡ላይ፡ ይቆማሉ፤ደብረ፡ዘይትም፡በመካከል፡ወደ፡ምሥራቅና፡ወደ፡ምዕራብ፡ይሰነጠቃል፥እጅግም፡ታላቅ፡ሸለቆ፡ ይኾናል፤የተራራውም፡እኩሌታ፡ወደ፡ሰሜን፥እኩሌታውም፡ወደ፡ደቡብ፡ይርቃል።
5የተራራዎችም፡ሸለቆ፡እስከ፡አጸል፡ይደርሳልና፥በተራራዎች፡ሸለቆ፡ትሸሻላችኹ፤በይሁዳም፡ንጉሥ፡ በዖዝያን፡ዘመን፡ከኾነው፡ከምድር፡መናወጥ፡ፊት፡እንደ፡ሸሻችኹ፡ትሸሻላችኹ፤አምላኬ፡እግዚአብሔርም፡ ከቅዱሳኑ፡ዅሉ፡ጋራ፡ይመጣል።
6በዚያም፡ቀን፡በረዶና፡ውርጭ፡እንጂ፡ብርሃን፡አይኾንም።
7አንድ፡ቀንም፡ይኾናል፥ርሱም፡በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡የታወቀ፡ይኾናል፤ቀንም፡አይኾንም፥ሌሊትም፡ አይኾንም፤ሲመሽም፡ብርሃን፡ይኾናል።
8በዚያም፡ቀን፡የሕይወት፡ውሃ፡ከኢየሩሳሌም፡ይወጣል፤እኩሌታው፡ወደምሥራቁ፡ባሕር፥እኩሌታውም፡ ወደምዕራቡ፡ባሕር፡ይኼዳል፤ይህ፡በበጋና፡በክረምት፡ይኾናል።
9እግዚአብሔርም፡በምድር፡ዅሉ፡ላይ፡ይነግሣል፤በዚያ፡ቀን፡እግዚአብሔር፡አንድ፥ስሙም፡አንድ፡ ይኾናል።
10ምድር፡ዅሉ፡ከጌባ፡ዠምሮ፡በኢየሩሳሌምም፡ደቡብ፡በኩል፡እስካለችው፡እስከ፡ሬሞን፡ድረስ፡ተለውጣ፡ እንደ፡ዐረባ፡ትኾናለች፤ርሷም፡ከፍ፡ከፍ፡ትላለች፥ከብንያምም፡በር፡ዠምሮ፡እስከፊተኛው፡በር፡ስፍራ፡ እስከማእዘኑ፡በር፡ድረስ፥ከሐናንኤልም፡ግንብ፡ዠምሮ፡እስከንጉሡ፡መጥመቂያ፡ድረስ፡በስፍራዋ፡ትኖራለች። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
11ሰዎችም፡ይኖሩባታል፥ከዚያም፡ወዲያ፡ርግማን፡አይኾንም፤ኢየሩሳሌምም፡ተዘልላ፡ትኖራለች።
12እግዚአብሔርም፡ከኢየሩሳሌም፡ጋራ፡የተዋጉትን፡አሕዛብ፡ዅሉ፡የሚቀሥፍበት፡ቸነፈር፡ይህ፡ ነው፤በእግራቸው፡ሲቆሙ፡ሥጋቸው፡ይበሰብሳል፥ዐይኖቻቸውም፡በዐይነ፡ሥባቸው፡ውስጥ፡ ይበሰብሳሉ፥ምላሳቸውም፡በአፋቸው፡ውስጥ፡ይበሰብሳል።
13በዚያም፡ቀን፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ታላቅ፡ሽብር፡በእነርሱ፡ላይ፡ይኾናል፤እያንዳንዱም፡የባልንጀራውን፡ እጅ፡ይይዛል፥እጁም፡በባልንጀራው፡እጅ፡ላይ፡ይነሣል።
14ይሁዳም፡ደግሞ፡በኢየሩሳሌም፡ውስጥ፡ኾኖ፡ይዋጋል፤በዙሪያም፡ያሉት፡የአሕዛብ፡ዅሉ፡ሀብት፡እጅግ፡ ብዙ፡ወርቅና፡ብር፡ልብስም፡ይሰበሰባል።
15በፈረስና፡በበቅሎ፥በግመልና፡በአህያ፥በዚያም፡ሰፈር፡ባለ፡እንስሳ፡ዅሉ፡ላይ፡የኾነ፡ቸነፈር፡እንደዚያ፡ ያለ፡ቸነፈር፡ይኾናል።
16በኢየሩሳሌም፡ላይ፡ከመጡት፡ከአሕዛብ፡ዅሉ፡የቀሩት፡ዅሉ፡ለንጉሡ፡ለሰራዊት፡ጌታ፡ለእግዚአብሔር፡ ይሰግዱ፡ዘንድ፥የዳስ፡በዓልንም፡ያከብሩ፡ዘንድ፡በየዓመቱ፡ይወጣሉ።
17ከምድርም፡ወገኖች፡ዅሉ፡ለንጉሡ፡ለሰራዊት፡ጌታ፡ለእግዚአብሔር፡ይሰግዱ፡ዘንድ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ ለማይወጡ፡ለእነርሱ፡ዝናብ፡አይዘንብላቸውም።
18የግብጽም፡ወገን፡ባይወጣ፡ወደዚያም፡ባይመጣ፥እግዚአብሔር፡የዳስ፡በዓልን፡ያከብሩ፡ዘንድ፡ የማይወጡትን፡አሕዛብ፡የሚቀሥፍበት፡ቸነፈር፡በርሱ፡ላይ፡ይኾናል።
19የግብጽ፡ቅጣት፥የዳስ፡በዓልንም፡ያከብሩ፡ዘንድ፡የማይወጡት፡የአሕዛብ፡ዅሉ፡ቅጣት፡እንደዚህ፡ ይኾናል።
20በዚያ፡ቀን፡በፈረሶች፡ሻኵራ፡ላይ፦ለእግዚአብሔር፡የተቀደሰ፡ተብሎ፡ይጻፋል፤በእግዚአብሔርም፡ቤት፡ ያሉ፡ምንቸቶች፡በመሠዊያው፡ፊት፡እንዳሉ፡ዳካዎች፡ይኾናሉ።
21በኢየሩሳሌምና፡በይሁዳ፡ያሉ፡ምንቸቶችም፡ዅሉ፡ለሰራዊት፡ጌታ፡ለእግዚአብሔር፡የተቀደሱ፡ ይኾናሉ፤የሚሠዉትም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ይመጣሉ፡ከነዚያም፡ወስደው፡ይቀቅሉባቸዋል፤በዚያም፡ቀን፡በሰራዊት፡ ጌታ፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡ከነዓናዊው፡ከእንግዲህ፡ወዲያ፡አይገኝም፨ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org