1ከዚህም፡በዃላ፡ዳዊት፡ፍልስጥኤማውያንን፡መታ፥አዋረዳቸውም፥ከፍልስጥኤማውያንም፡እጅ፡ጌትንና፡ መንደሮቿን፡ወሰደ።
2ሞዐብን፡መታ፤ሞዐባውያንም፡ለዳዊት፡ገባሮች፡ኾኑ፤ግብርም፡አመጡለት።
3ዳዊትም፡በኤፍራጥስ፡ወንዝ፡አጠገብ፡የነበረውን፡ግዛት፡ለመያዝ፡በኼደ፡ጊዜ፡የሱባን፡ንጉሥ፡ አድርዐዛርን፡እስከ፡ሃማት፡ድረስ፡መታ።
4ዳዊትም፡ከርሱ፡አንድ፡ሺሕ፡ሠረገላዎች፥ሰባት፡ሺሕም፡ፈረሰኛዎች፥ኻያ፡ሺሕም፡እግረኛዎች፡ ወሰደ፤ዳዊት፡ለመቶ፡ሠረገላዎች፡የሚኾኑትን፡ብቻ፡አስቀርቶ፡የሠረገላዎቹን፡ፈረሶች፡ቋንዣ፡ቈረጠ።
5ከደማስቆም፡ሶርያውያን፡የሱባን፡ንጉሥ፡አድርዐዛርን፡ሊረዱ፡በመጡ፡ጊዜ፡ዳዊት፡ከሶርያውያን፡ኻያ፡ ኹለት፡ሺሕ፡ሰዎችን፡ገደለ።
6ዳዊትም፡በደማስቆ፡ሶርያ፡ጭፍራዎች፡አኖረ፤ሶርያውያንም፡ለዳዊት፡ገባሮች፡ኾኑ፥ግብርም፡ አመጡለት።እግዚአብሔርም፡ዳዊት፡በኼደበት፡ዅሉ፡ድል፡ይሰጠው፡ነበር።
7ዳዊትም፡ለአድርዐዛር፡ባሪያዎች፡የነበሩትን፡የወርቅ፡ጋሻዎች፡ወሰደ፥ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡ይዟቸው፡መጣ።
8ከአድርዐዛርም፡ከተማዎች፡ከጢብሐትና፡ከኩን፡ዳዊት፡እጅግ፡ብዙ፡ናስ፡ወሰደ፤ከዚህም፡ሰሎሞን፡ የናሱን፡ኵሬና፡ዐምዶች፡የናሱንም፡ዕቃ፡ሠራ።
9የሐማትም፡ንጉሥ፡ቶዑ፡ዳዊት፡የሱባን፡ንጉሥ፡የአድርዐዛርን፡ጭፍራ፡ዅሉ፡እንደ፡መታ፡ሰማ።
10ቶዑም፡ከአድርዐዛር፡ጋራ፡ዅል፡ጊዜ፡ይዋጋ፡ነበርና፥ዳዊት፡አድርዐዛርን፡ወግቶ፡ስለ፡መታው፡ ደኅንነቱን፡ይጠይቅ፡ዘንድ፡ይመርቀውም፡ዘንድ፡ልጁን፡አዶራምን፡ወደ፡ዳዊት፡ላከው፤ርሱም፡የወርቅና፡ የብር፡የናስም፡ዕቃ፡ይዞ፡መጣ።
11ንጉሡም፡ዳዊት፡ከአሕዛብ፡ዅሉ፡ከኤዶምና፡ከሞዐብ፡ከዐሞንም፡ልጆች፡ከፍልስጥኤማውያንም፡ ከዐማሌቅም፡ከማረከው፡ብርና፡ወርቅ፡ጋራ፡እነዚህን፡ደግሞ፡ለእግዚአብሔር፡ቀደሰ።
12ደግሞ፡የጽሩያ፡ልጅ፡አቢሳ፡ከኤዶማውያን፡በጨው፡ሸለቆ፡ውስጥ፡ዐሥራ፡ስምንት፡ሺሕ፡ሰዎች፡ገደለ።
13በኤዶምያስም፡ጭፍራዎች፡አኖረ፥ኤዶማውያንም፡ዅሉ፡ለዳዊት፡ገባሮች፡ኾኑ።እግዚአብሔርም፡ዳዊት፡ በኼደበት፡ዅሉ፡ድል፡ይሰጠው፡ነበር።
14ዳዊትም፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ላይ፡ነገሠ፤ለሕዝቡም፡ዅሉ፡ፍርድንና፡ጽድቅም፡አደረገላቸው።
15የጽሩያ፡ልጅ፡ኢዮአብም፡የሰራዊት፡አለቃ፡ነበረ፤የአኂሉድም፡ልጅ፡ኢዮሳፍጥ፡ታሪክ፡ጸሓፊ፡ነበረ።
16የአኪጦብም፡ልጅ፡ሳዶቅ፥የአቢሜሌክም፡ልጅ፡አብያታር፡ካህናት፡ነበሩ፤ሱሳ፡ጸሓፊ፡ነበረ።
17የዮዳዔ፡ልጅ፡በናያስ፡በከሊታውያንና፡በፈሊታውያን፡ላይ፡ነበረ፤የዳዊትም፡ልጆች፡በንጉሡ፡አጠገብ፡ አለቃዎች፡ነበሩ።