1ዳዊትም፡በሸመገለ፡ጊዜ፥ዕድሜንም፡በጠገበ፡ጊዜ፡ልጁን፡ሰሎሞንን፡በእስራኤል፡ላይ፡አነገሠው።
2የእስራኤልንም፡አለቃዎች፡ዅሉ፥ካህናቱንም፥ሌዋውያኑንም፡ሰበሰበ።
3ሌዋውያንም፡ከሠላሳ፡ዓመት፡ዕድሜ፡ዠምሮ፡ወደ፡ላይ፡ተቈጠሩ፤ቍጥራቸው፡በያንዳንዱ፡ነፍስ፡ወከፍ፡ ሠላሳ፡ስምንት፡ሺሕ፡ነበረ።
4ከነዚህም፡ውስጥ፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡ሥራ፡የሚያሠሩት፡ኻያ፡አራት፡ሺሕ፡ነበሩ፤ስድስቱ፡ሺሕም፡ አለቃዎችና፡ፈራጆች፡ነበሩ።
5አራቱ፡ሺሕም፡በረኛዎች፡ነበሩ፤አራቱ፡ሺሕም፡ለምስጋና፡በተሠሩት፡በዜማ፡ዕቃዎች፡እግዚአብሔርን፡ ያመሰግኑ፡ነበር።
6ዳዊትም፡እንደ፡ሌዊ፡ልጆች፡እንደ፡ጌድሶንና፡እንደ፡ቀአት፡እንደ፡ሜራሪም፡በየሰሞናቸው፡ከፈላቸው።
7ከጌድሶናውያን፡ለአዳንና፡ሰሜኢ፡ነበሩ።
8የለአዳን፡ልጆች፡አለቃው፡ይሒኤል፥ዜቶም፥ኢዮኤል፡ሦስት፡ነበሩ።
9የሰሜኢ፡ልጆች፡ሰሎሚት፥ሐዝኤል፥ሀራን፡ሦስት፡ነበሩ።እነዚህ፡የለአዳን፡አባቶች፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ ነበሩ።
10የሰሜኢ፡ልጆች፡ኢኢት፥ዚዛ፥የዑስ፥በሪዐ፡ነበሩ።እነዚህ፡አራቱ፡የሰሜኢ፡ልጆች፡ነበሩ።
11አለቃው፡ኢኢት፡ነበረ፤ኹለተኛው፡ዚዛ፡ነበረ፤የዑስና፡በሪዐ፡ግን፡ብዙ፡ልጆች፡ አልነበሯቸውም፤ስለዚህ፥እንደ፡አንድ፡አባት፡ቤት፡ኾነው፡ተቈጠሩ።
12የቀአት፡ልጆች፡ዕምበረም፥ይስዓር፥ኬብሮን፥ዑዝኤል፡አራት፡ነበሩ።
13የዕምበረም፡ልጆች፡አሮንና፡ሙሴ፡ነበሩ፤አሮንም፡ከዅሉ፡በላይ፡የተቀደሰ፡ይኾን፡ዘንድ፡ተለየ፥ርሱና፡ ልጆቹ፥ለዘለዓለም፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ያጥንና፡ያገለግል፡ዘንድ፥በስሙም፡ለዘለዓለም፡ይባርክ፡ዘንድ።
14የእግዚአብሔርም፡ሰው፡የሙሴ፡ልጆች፡በሌዊ፡ነገድ፡ተቈጠሩ።
15የሙሴ፡ልጆች፡ጌርሳምና፡አልዓዛር፡ነበሩ።
16የጌርሳም፡ልጆች፡አለቃ፡ሱባኤል፡ነበረ።
17የአልዓዛርም፡ልጆች፡አለቃ፡ረዓብያ፡ነበረ፤አልዓዛርም፡ሌላዎች፡ልጆች፡አልነበሩትም፤የረዓብያ፡ልጆች፡ እጅግ፡ብዙ፡ነበሩ።
18የይስዓር፡ልጆች፡አለቃው፡ሰሎሚት፡ነበረ።
19የኬብሮን፡ልጆች፡አለቃው፡ይሪያ፥ኹለተኛው፡አማርያ፥ሦስተኛው፡የሕዚኤል፥አራተኛው፡ይቅምዓም፡ ነበሩ።
20የዑዝኤል፡ልጆች፡አለቃው፡ሚካ፥ኹለተኛው፡ይሺያ፡ነበሩ።
21የሜራሪ፡ልጆች፡ሞሖሊና፡ሙሲ፡ነበሩ።የሞሖሊ፡ልጆች፡አልዓዛርና፡ቂስ፡ነበሩ።
22አልዓዛርም፡ሴቶች፡ልጆች፡ብቻ፡እንጂ፡ወንዶች፡ልጆች፡ሳይወልድ፡ሞተ፤ወንድሞቻቸውም፡የቂስ፡ ልጆች፡አገቧቸው።
23የሙሲ፡ልጆች፡ሞሖሊ፥ዔደር፥ኢያሪሙት፡ሦስት፡ነበሩ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
24የእግዚአብሔርን፡ቤት፡አገልግሎት፡በሠሩ፡ከኻያ፡ዓመት፡ዕድሜ፡ዠምሮ፡ወደ፡ላይ፡በነበሩ፡ በያንዳንዳቸው፡በስማቸው፡በተቈጠሩት፡ላይ፡የአባቶች፡ቤት፡አለቃዎች፡የኾኑት፡በያባቶቻቸው፡ቤት፡የሌዊ፡ ልጆች፡እነዚህ፡ነበሩ።
25ዳዊትም፦የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ለሕዝቡ፡ዕረፍት፡ሰጥቷል፥በኢየሩሳሌምም፡ለዘለዓለም፡ ይቀመጣል።
26ሌዋውያንም፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ማደሪያውንና፡የማገልገያውን፡ዕቃ፡ዅሉ፡አይሸከሙም፡አለ።
27በመጨረሻውም፡በዳዊት፡ትእዛዝ፡ከኻያ፡ዓመት፡ዕድሜ፡ዠምሮ፡ከዚያም፡በላይ፡ያሉት፡የሌዊ፡ልጆች፡ ተቈጠሩ።
28ሥራቸውም፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡በያደባባዩና፡በየጓዳው፡ውስጥ፡ለማገልገል፥ቅዱሱንም፡ዕቃ፡ዅሉ፡ ለማንጻት፥የእግዚአብሔርንም፡ቤት፡አገልግሎት፡ለመሥራት፡ከአሮን፡ልጆች፡እጅ፡በታች፡ነበረ።
29ደግሞም፡ገጸ፡ኅብስት፥ሥሥ፡ቂጣም፡ቢኾን፥በምጣድም፡ቢጋገር፥ቢለወስም፥ለእኽል፡ቍርባን፡ በኾነው፡በመልካሙ፡ዱቄት፡በመስፈሪያና፡በልክ፡ዅሉ፡ያገለግሉ፡ነበር።
30ሥራቸውም፡በየጧቱና፡በየማታው፡ቆመው፡እግዚአብሔርን፡ለማመስገንና፡ለማክበር፥
31በየሰንበታቱም፡በየመባቻዎቹም፡በየበዓላቱም፡እንደ፡ሥርዐቱ፡ቍጥር፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ዘወትር፡ ለእግዚአብሔር፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡ዅሉ፡ለማቅረብ፥
32ለእግዚአብሔርም፡ቤት፡አገልግሎት፡የመገናኛውን፡ድንኳን፡ሥርዐት፡የመቅደሱንም፡ሥርዐት፡ የወንድሞቻቸውንም፡የአሮንን፡ልጆች፡ሥርዐት፡ለመጠበቅ፡ነበረ።