Skip to content
← 1 Kings

Chapter 3 · Amharic

1 Kings

1ሰሎሞንም፡ለግብጽ፡ንጉሥ፡ለፈርዖን፡ዐማች፡ኾነ፤የፈርዖንን፡ልጅ፡አገባ፥ቤቱንና፡የእግዚአብሔርንም፡ ቤት፡በኢየሩሳሌምም፡ዙሪያ፡ያለውን፡ቅጥር፡ሠርቶ፡እስኪፈጽም፡ድረስ፡ወደዳዊት፡ከተማ፡አመጣት።

2እስከዚያም፡ቀን፡ድረስ፡ለእግዚአብሔር፡ስም፡መቅደስ፡አልተሠራም፡ነበርና፥ሕዝቡ፡በኰረብታ፡ላይ፡ ባሉት፡መስገጃዎች፡ይሠዋ፡ነበር።

3ሰሎሞንም፡እግዚአብሔርን፡ይወድ፟፡ነበር፥በአባቱም፡በዳዊት፡ሥርዐት፡ይኼድ፡ነበር፤ብቻ፡በኰረብታ፡ መስገጃ፡ይሠዋና፡ያጥን፡ነበር።

4ገባዖን፡ዋና፡የኰረብታ፡መስገጃ፡ነበረችና፡ንጉሡ፡ይሠዋ፡ዘንድ፡ወደዚያ፡ኼደ፤ሰሎሞንም፡በዚያ፡ መሠዊያ፡ላይ፡አንድ፡ሺሕ፡የሚቃጠል፡መሥዋዕት፡አቀረበ።

5እግዚአብሔርም፡በገባዖን፡ለሰሎሞን፡በሌሊት፡በሕልም፡ተገለጠለት፤እግዚአብሔርም፦ምን፡እንድሰጥኽ፡ ለምን፡አለ።

6ሰሎሞንም፡አለ፦ርሱ፡በፊትኽ፡በእውነትና፡በጽድቅ፡በልብም፡ቅንነት፡ከአንተ፡ጋራ፡እንደ፡ ኼደ፥ከባሪያኽ፡ከአባቴ፡ከዳዊት፡ጋራ፡ታላቅ፡ቸርነት፡አድርገኻል፤ዛሬ፡እንደ፡ኾነም፡በዙፋኑ፡ላይ፡ የሚቀመጥ፡ልጅ፡ሰጥተኽ፡ታላቁን፡ቸርነትኽን፡አቈይተኽለታል።

7አኹንም፥አቤቱ፡አምላኬ፡ሆይ፥እኔን፡ባሪያኽን፡በአባቴ፡በዳዊት፡ፋንታ፡አንግሠኸኛል፤እኔም፡ መውጫንና፡መግቢያን፡የማላውቅ፡ታናሽ፡ብላቴና፡ነኝ።

8ባሪያኽም፡ያለው፡አንተ፡በመረጥኸው፡ሕዝብኽ፡ስለ፡ብዛቱም፡ይቈጠርና፡ይመጠን፡ዘንድ፡በማይቻል፡ በታላቅ፡ሕዝብ፡መካከል፡ነው።

9ስለዚህም፡በሕዝብኽ፡ላይ፡መፍረድ፡ይችል፡ዘንድ፥መልካሙንና፡ክፉውንም፡ይለይ፡ዘንድ፡ለባሪያኽ፡ አስተዋይ፡ልቡና፡ስጠው፤አለዚያማ፡በዚህ፡በታላቅ፡ሕዝብኽ፡ላይ፡ይፈርድ፡ዘንድ፡ማን፡ይችላል፧

10ሰሎሞንም፡ይህን፡ነገር፡ስለ፡ለመነ፥ነገሩ፡እግዚአብሔርን፡ደስ፡አሠኘው።

11እግዚአብሔርም፡አለው፦ፍርድን፡ትለይ፡ዘንድ፡ለራስኽ፡ማስተዋልን፡ለመንኽ፡እንጂ፡ለራስኽ፡ብዙ፡ ዘመናትን፡ባለጠግነትንም፡የጠላቶችኽንም፡ነፍስ፡ሳትለምን፡ይህን፡ነገር፡ለምነኻልና፥እንሆ፥

12እኔ፡እንደ፡ቃል፡አድርጌልኻለኹ፤እንሆ፥ማንም፡የሚመስልኽ፡ከአንተ፡በፊት፡እንደሌለ፡ከአንተም፡ በዃላ፡እንዳይነሣ፡አድርጌ፡ጥበበኛና፡አስተዋይ፡ልቡና፡ሰጥቼኻለኹ።

13ደግሞም፡ከነገሥታት፡የሚመስልኽ፡ማንም፡እንዳይኖር፡ያልለመንኸውን፡ባለጠግነትና፡ክብር፡ሰጥቼኻለኹ።

14አባትኽም፡ዳዊት፡እንደ፡ኼደ፥ሥርዐቴንና፡ትእዛዜን፡ትጠብቅ፡ዘንድ፡በመንገዴ፡የኼድኽ፡እንደ፡ ኾነ፥ዕድሜኽን፡አረዝመዋለኹ።

15ሰሎሞንም፡ነቃ፥እንሆም፥ሕልም፡ነበረ፤ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡መጥቶ፡በእግዚአብሔር፡ቃል፡ኪዳን፡ ታቦት፡ፊት፡ቆመ፥የሚቃጠለውንም፡መሥዋዕት፡አሳረገ፥የደኅንነትንም፡መሥዋዕት፡አቀረበ፥ለባሪያዎቹም፡ ዅሉ፡ግብዣ፡አደረገ።

16በዚያን፡ጊዜም፡ኹለት፡ጋለሞታዎች፡ሴቶች፡ወደ፡ንጉሡ፡መጥተው፡በፊቱ፡ቆሙ። http://www.gzamargna.net

17አንደኛዪቱም፡ሴት፡አለች፦ጌታዬ፡ሆይ፥እኔና፡ይህች፡ሴት፡ባንድ፡ቤት፡እንኖራለን፤እኔም፡ከርሷ፡ ጋራ፡በቤት፡ሳለኹ፡ወለድኹ።

18እኔ፡ከወለድኹ፡ከሦስት፡ቀን፡በዃላ፡ይህች፡ሴት፡ደግሞ፡ወለደች፤እኛ፡በቤት፡ውስጥ፡ዐብረን፡ ነበርን፥ከኹለታችንም፡በቀር፡ማንም፡በቤት፡ውስጥ፡አልነበረም።

19ርሷም፡በላዩ፡ስለ፡ተኛችበት፡የዚች፡ሴት፡ልጅ፡በሌሊት፡ሞተ።

20ርሷም፡በእኩለ፡ሌሊት፡ተነሥታ፥እኔ፡ባሪያኽ፡ተኝቼ፡ሳለኹ፥ልጄን፡ከአጠገቤ፡ወሰደች፥በብብቷም፡ አደረገችው፥የሞተውንም፡ልጇን፡በእኔ፡ብብት፡አደረገች።

21ልጄንም፡አጠባ፡ዘንድ፡በማለዳ፡ብነሣ፥እንሆ፥ሞቶ፡ነበር፤ነገር፡ግን፥ብርሃን፡በኾነ፡ጊዜ፡ ተመለከትኹት፥እንሆም፥የወለድኹት፡ልጄ፡አልነበረም።

22ኹለተኛዪቱም፡ሴት፦ደኅነኛው፡የኔ፡ልጅ፡ነው፥የሞተውም፡የአንቺ፡ልጅ፡ነው፡እንጂ፡አንቺ፡ እንደምትዪው፡አይደለም፡አለች።ይህችም፦የሞተው፡የአንቺ፡ልጅ፡ነው፥ደኅነኛውም፡የእኔ፡ልጅ፡ነው፡ አለች፤እንዲሁም፡በንጉሡ፡ፊት፡ይነጋገሩ፡ነበር።

23በዚያን፡ጊዜም፡ንጉሡ፦ይህች፦ደኅነኛው፡የእኔ፡ልጅ፡ነው፥የሞተውም፡የአንቺ፡ልጅ፡ነው፡ ትላለች፤ያችኛዪቱም፦አይደለም፥የሞተው፡የአንቺ፡ልጅ፡ነው፡ደኅነኛውም፡የእኔ፡ልጅ፡ነው፡ትላለች፡አለ።

24ንጉሡም፦ሰይፍ፡አምጡልኝ፡አለ፤ሰይፍም፡ይዘው፡ወደ፡ንጉሡ፡ፊት፡መጡ።

25ንጉሡም፦ደኅነኛውን፡ሕፃን፡ለኹለት፡ከፍላችኹ፡ለአንዲቱ፡አንዱን፡ክፍል፥ለኹለተኛዪቱም፡ ኹለተኛውን፡ክፍል፡ስጡ፡አለ።

26ደኅነኛውም፡የነበራት፡ሴት፡አንዠቷ፡ስለ፡ልጇ፡ናፍቋልና፦ጌታዬ፡ሆይ፥ደኅነኛውን፡ለርሷ፡ስጣት፡ እንጂ፡አትግደል፡ብላ፡ለንጉሡ፡ተናገረች።ያችኛዪቱ፡ግን፦ይከፈል፡እንጂ፡ለኔም፡ለአንቺም፡አይኹን፡ አለች።

27ንጉሡም፡መልሶ፦ይህችኛዪቱ፡እናቱ፡ናትና፥ደኅነኛውን፡ሕፃን፡ለርሷ፡ስጧት፡እንጂ፡አትግደሉት፡አለ።

28ንጉሡም፡የፈረደውን፡ፍርድ፡እስራኤል፡ዅሉ፡ሰሙ፤ፍርድን፡ለማድረግ፡የእግዚአብሔር፡ጥበብ፡እንደ፡ ነበረበት፡አይተዋልና፥ንጉሡን፡ፈሩ።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source