1የእስራኤል፡ልጆች፡ከግብጽ፡ምድር፡ከወጡ፡አራት፡መቶ፡ሰማንያ፡ዓመት፡በኾነ፡ጊዜ፥ሰሎሞን፡ በእስራኤል፡ላይ፡በነገሠ፡በአራተኛው፡ዓመት፥ዚፍ፡በሚባለው፡በኹለተኛው፡ወር፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡ መሥራት፡ዠመረ።
2ንጉሡ፡ሰሎሞንም፡ለእግዚአብሔር፡የሠራው፡ቤት፡ርዝመቱ፡ስድሳ፡ክንድ፥ወርዱም፡ኻያ፡ ክንድ፥ቁመቱም፡ሠላሳ፡ክንድ፡ነበረ።
3በመቅደሱም፡ፊት፡ወለል፡ነበረ፤ርዝመቱም፡እንደ፡መቅደሱ፡ወርድ፡ኻያ፡ክንድ፥ወርዱም፡ከቤቱ፡ወደ፡ ፊት፡ዐሥር፡ክንድ፡ነበረ።
4ለቤቱም፡በዐይነ፡ርግብ፡የተዘጉ፡መስኮቶች፡አደረገ።
5በቤቱም፡ግንብ፡ዙሪያ፥በመቅደሱና፡በቅድስተ፡ቅዱሳኑ፡ግንብ፡ዙሪያ፥ደርብ፡ሠራ፥በዙሪያውም፡ ጓዳዎች፡አደረገ።
6የታችኛውም፡ደርብ፡ወርዱ፡ዐምስት፡ክንድ፥የመካከለኛው፡ደርብ፡ወርዱ፡ስድስት፡ክንድ፥የሦስተኛውም፡ ደርብ፡ወርዱ፡ሰባት፡ክንድ፡ነበረ።ሠረገላዎቹ፡በቤቱ፡ግንብ፡ውስጥ፡እንዳይገቡ፡ከቤቱ፡ግንብ፡ውጭ፡ አረፍቶች፡አደረገ።
7ቤቱም፡በተሠራ፡ጊዜ፡ፈጽመው፡በተወቀሩ፡ድንጋዮች፡ተሠራ፤በተሠራም፡ጊዜ፡መራጃና፡መጥረቢያ፡ የብረትም፡ዕቃ፡ዅሉ፡በቤቱ፡ውስጥ፡አልተሰማም።
8የታችኛውም፡ደርብ፡ጓዳዎች፡በር፡በቤቱ፡ቀኝ፡አጠገብ፡ነበረ።ከዚያም፡ወደ፡መካከለኛው፡ ደርብ፥ከመካከለኛውም፡ወደ፡ሦስተኛው፡ደርብ፡በመውጫ፡ያስወጣ፡ነበር።
9ቤቱንም፡ሠርቶ፡ፈጸመው፤በዝግባው፡ሠረገላዎችና፡ሳንቃዎች፡ከደነው።
10በቤቱም፡ዅሉ፡ዙሪያ፡ቁመታቸው፡ዐምስት፡ዐምስት፡ክንድ፡የኾነ፡ደርቦች፡ሠራ፤ከቤቱም፡ጋራ፡ በዝግባ፡ዕንጨት፡አጋጠማቸው።
11የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡ሰሎሞን፡መጣ፡እንዲህ፡ሲል፦
12ስለዚህ፥ስለምትሠራው፡ቤት፡በሥርዐቴ፡ብትኼድ፥ፍርዴንም፡ብታደርግ፥ትመላለስበትም፡ዘንድ፡ ትእዛዜን፡ዅሉ፡ብትጠብቅ፥ለአባትኽ፡ለዳዊት፡የነገርኹትን፡ቃል፡ከአንተ፡ጋራ፡አጸናለኹ።
13በእስራኤልም፡ልጆች፡መካከል፡እኖራለኹ፥ሕዝቤንም፡እስራኤልን፡አልጥልም።
14ሰሎሞንም፡ቤቱን፡ሠራው፥ፈጸመውም።
15የቤቱንም፡ግንብ፡ውስጡን፡በዝግባ፡ሳንቃ፡ለበጠ፤ከቤቱም፡መሠረት፡ዠምሮ፡እስከ፡ጣራው፡ድረስ፡ ውስጡን፡በዕንጨት፡ለበጠው፤ደግሞም፡የቤቱን፡ወለል፡በጥድ፡ዕንጨት፡ከደነው።
16በቤቱ፡ውስጥ፡ቅድስተ፡ቅዱሳን፡ይኾን፡ዘንድ፡ዃለኛውን፡ኻያውን፡ክንድ፡በዝግባ፡ዕንጨት፡ጋረደው።
17በቅድስተ፡ቅዱሳኑ፡ፊት፡ያለውም፡መቅደስ፡ርዝመቱ፡አርባ፡ክንድ፡ነበረ።
18የቤቱንም፡ውስጥ፡በተጐበጐበና፡በፈነዳ፡አበባ፡በተቀረጸ፡ዝግባ፡ለበጠው፤ዅሉም፡ዝግባ፡ http://www.gzamargna.net ነበረ፤ድንጋዩም፡አልታየም፡ነበር።
19በዚያም፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡ያኖር፡ዘንድ፡በቤቱ፡ውስጥ፡ቅድስተ፡ቅዱሳኑን፡አበጀ።
20የቅድስተ፡ቅዱሳንም፡ርዝመት፡ኻያ፡ክንድ፥ስፋቱም፡ኻያ፡ክንድ፥ቁመቱም፡ኻያ፡ክንድ፡ነበረ፤በጥሩ፡ ወርቅም፡ለበጠው።
21በቅድስተ፡ቅዱሳኑም፡ፊት፡ከዝግባ፡የተሠራ፡መሠዊያ፡አደረገ፤በጥሩ፡ወርቅም፡ለበጠው።
22ቤቱንም፡ዅሉ፡ፈጽሞ፡በወርቅ፡ለበጠው፤በቅድስተ፡ቅዱሳኑም፡ፊት፡የነበረውን፡መሠዊያ፡ዅሉ፡ በወርቅ፡ለበጠው።
23በቅድስተ፡ቅዱሳኑም፡ውስጥ፡ቁመታቸው፡ዐሥር፡ክንድ፡የኾነ፡ከወይራ፡ዕንጨት፡ኹለት፡ኪሩቤል፡ ሠራ።
24የኪሩብም፡አንደኛው፡ክንፍ፡ዐምስት፡ክንድ፥የኪሩብም፡ኹለተኛው፡ክንፍ፡ዐምስት፡ክንድ፡ ነበረ፤ከአንደኛው፡ክንፍ፡ጫፍ፡ዠምሮ፡እስክ፡ኹለተኛው፡ክንፍ፡ጫፍ፡ድረስ፡ዐሥር፡ክንድ፡ነበረ።
25ኹለተኛውም፡ኪሩብ፡ዐሥር፡ክንድ፡ነበረ፤ኹለቱም፡ኪሩቤል፡አንድ፡ልክና፡አንድ፡መልክ፡ነበረ።
26የአንዱ፡ኪሩብ፡ቁመት፡ዐሥር፡ክንድ፡ነበረ፥የኹለተኛውም፡ኪሩብ፡እንዲሁ፡ነበረ።
27ኪሩቤልንም፡በውስጠኛው፡ቤት፡አኖራቸው፤የኪሩቤልም፡ክንፎቻቸው፡ተዘርግተው፡ነበር፤የአንዱም፡ ኪሩብ፡ክንፍ፡አንደኛውን፡ግንብ፡ይነካ፡ነበር፥የኹለተኛውም፡ኪሩብ፡ክንፍ፡ኹለተኛውን፡ግንብ፡ይነካ፡ ነበር፤የኹለቱም፡ክንፎች፡በቤቱ፡መካከል፡ርስ፡በርሳቸው፡ይነካኩ፡ነበር።
28ኪሩቤልንም፡በወርቅ፡ለበጣቸው።
29በቤቱም፡ግንብ፡ዅሉ፡ዙሪያ፡በውስጥና፡በውጭ፡የኪሩቤልና፡የዘንባባ፡ዛፍ፡የፈነዳም፡አበባ፡ምስል፡ ቀረጸ።
30የቤቱንም፡ወለል፡በውስጥና፡በውጭ፡በወርቅ፡ለበጠ።
31ለቅድስተ፡ቅዱሳኑም፡መግቢያ፡ከወይራ፡ዕንጨት፡ደጆች፡ሠራ፤መድረኩንና፡መቃኖቹን፡ደፉንም፡ ዐምስት፡ማእዘን፡አደረገ።
32ኹለቱንም፡ደጆች፡ከወይራ፡ዕንጨት፡ሠራ፤የኪሩቤልንና፡የዘንባባ፡ዛፍ፡የፈነዳም፡አበባ፡ምስል፡ ቀረጸባቸው፥በወርቅም፡ለበጣቸው፤ኪሩቤልናና፡የዘንባባውን፡ዛፍ፡በወርቅ፡ለበጣቸው።
33እንዲሁም፡ለመቅደሱ፡መግቢያ፡ከወይራ፡ዕንጨት፡አራት፡ማእዘን፡መቃን፡አደረገ።
34ኹለቱንም፡ደጆች፡ከጥድ፡ዕንጨት፡ሠራ፤አንዱ፡ደጅ፡በማጠፊያ፡ከተያያዘ፡ከኹለት፡ሳንቃ፡ ተደረገ፥ኹለተኛውም፡ደጅ፡በማጠፊያ፡ከተያያዘ፡ከኹለት፡ሳንቃ፡ተደረገ።
35የኪሩቤልንና፡የዘንባባ፡ዛፍ፡የፈነዳም፡አበባ፡ምስል፡ቀረጸባቸው፤በተቀረጸውም፡ሥራ፡ላይ፡በወርቅ፡ ለበጣቸው።
36የውስጠኛውንም፡አደባባይ፡ቅጥር፡ሦስቱን፡ተራ፡በተጠረበ፡ድንጋይ፥አንዱንም፡ተራ፡በዝግባ፡ሳንቃ፡ ሠራው።
37በአራተኛው፡ዓመት፡ዚፍ፡በሚባል፡ወር፡የእግዚአብሔር፡ቤት፡ተመሠረተ።
38በዐሥራ፡አንደኛውም፡ዓመት፡ቡል፡በሚባል፡በስምንተኛው፡ወር፡ቤቱ፡እንደ፡ክፍሎቹና፡እንደ፡ሥርዐቱ፡ ዅሉ፡ተጨረሰ።በሰባትም፡ዓመት፡ውስጥ፡ሠራው።