1እንዲህም፡ኾነ፤ካንድ፡ወር፡በዃላ፡አሞናዊው፡ናዖስ፡ወጣ፥በኢያቢስ፡ገለዓድም፡ሰፈረ፤የኢያቢስም፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ሰዎች፡ዅሉ፦ቃል፡ኪዳን፡አድርግልን፥እኛም፡እንገዛልኻለን፡አሉት።
2አሞናዊውም፡ናዖስ፦ቀኝ፡ዐይናችኹን፡ዅሉ፡በማውጣት፡ቃል፡ኪዳን፡አደርግላችዃለኹ፤በእስራኤልም፡ ዅሉ፡ላይ፡ስድብ፡አደርጋለኹ፡አላቸው።
3የኢያቢስም፡ሽማግሌዎች፦ወደእስራኤል፡አገር፡ዅሉ፡መልክተኛዎችን፡እንድንልክ፡ሰባት፡ቀን፡ ቈይልን፤ከዚያም፡በዃላ፡የሚያድነን፡ባይኖር፡ወዳንተ፡እንመጣለን፡አሉት።
4መልክተኛዎቹም፡ሳኦል፡ወዳለበት፡ወደ፡ጊብዓ፡መጥተው፡ይህን፡ነገር፡በሕዝቡ፡ዦሮ፡ተናገሩ፤ሕዝቡም፡ ዅሉ፡ድምፃቸውን፡ከፍ፡አድርገው፡አለቀሱ።
5እንሆም፥ሳኦል፡በሬዎቹን፡ተከትሎ፡ከዕርሻው፡መጣ፤ሳኦልም፦ሕዝቡ፡የሚያለቅስ፡ምን፡ኾኖ፡ ነው፧አለ።የኢያቢስንም፡ሰዎች፡ነገር፡ነገሩት።
6ይህንም፡ነገር፡በሰማው፡ጊዜ፡በሳኦል፡ላይ፡የእግዚአብሔር፡መንፈስ፡በኀይል፡ወረደ፥ቍጣውም፡እጅግ፡ ነደደ።
7ጥምዱንም፡በሬዎች፡ወስዶ፡ቈራረጣቸው፥ወደእስራኤልም፡ዳርቻ፡ዅሉ፡በመልክተኛዎቹ፡እጅ፡ ሰደደና፦ሳኦልንና፡ሳሙኤልን፡ተከትሎ፡የማይወጣ፡ዅሉ፥በበሬዎቹ፡እንዲሁ፡ይደረግ፡አለ።ድንጋጤም፡ በሕዝቡ፡ላይ፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ወደቀ፥እንደ፡አንድ፡ሰውም፡ኾነው፡ወጡ።
8በቤዜቅም፡ቈጠራቸው፤የእስራኤልም፡ልጆች፡ሦስት፡መቶ፡ሺሕ፥የይሁዳም፡ሰዎች፡ሠላሳ፡ሺሕ፡ነበሩ።
9የመጡትንም፡መልክተኛዎች፦የኢያቢስ፡ገለዓድን፡ሰዎች፦ነገ፡ፀሓይ፡በተኰሰ፡ጊዜ፡ማዳን፡ ይኾንላችዃል፡በሏቸው፡አሏቸው።መልክተኛዎችም፡መጥተው፡ለኢያቢስ፡ሰዎች፡ነገሩ፤ደስም፡አላቸው።
10የአያቢስም፡ሰዎች፦ነገ፡እንወጣላችዃለን፥ደስ፡የሚያሠኛችኹንም፡አድርጉብን፡አሉ።
11በነጋውም፡ሳኦል፡ሕዝቡን፡በሦስት፡ወገን፡አደረጋቸው፤ወገግም፡ባለ፡ጊዜ፡ወደሰፈሩ፡መካከል፡ ገቡ፥ቀትርም፡እስኪኾን፡ድረስ፡አሞናውያንን፡መቱ፤የቀሩትም፡ተበተኑ፥ኹለትም፡ባንድ፡ላይ፡ኾነው፡ አልቀሩላቸውም።
12ሕዝቡም፡ሳሙኤልን፦ሳኦል፡አይንገሥብን፡ያሉ፡እነማናቸው፧አውጧቸውና፡እንግደላቸው፡አሉት።
13ሳኦልም፦ዛሬ፡እግዚአብሔር፡ለእስራኤል፡ማዳን፡አድርጓልና፥ዛሬ፡አንድ፡ሰው፡አይሞትም፡አለ።
14ሳሙኤልም፡ሕዝቡን፦ኑ፥ወደ፡ገልገላ፡እንኺድ፥በዚያም፡መንግሥቱን፡እናድስ፡አላቸው።
15ሕዝቡም፡ዅሉ፡ወደ፡ገልገላ፡ኼዱ፥በዚያም፡ሳኦልን፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡በገልገላ፡ አነገሡት፤በዚያም፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡የደኅንነት፡መሥዋዕት፡አቀረቡ፤በዚያም፡ሳኦልና፡የእስራኤል፡ሰዎች፡ ዅሉ፡ታላቅ፡ደስታ፡አደረጉ።