Skip to content
← 1 Samuel

Chapter 12 · Amharic

1 Samuel

1ሳሙኤልም፡እስራኤልን፡ዅሉ፡አለ፦የነገራችኹኝን፡ዅሉ፡ሰምቼ፡አንግሼላችዃለኹ።

2አኹንም፥እንሆ፥ንጉሡ፡በፊታችኹ፡ይኼዳል፤እኔም፡አርጅቻለኹ፡ሸምግያለኹም፤እንሆም፥ልጆቼ፡ ከእናንተ፡ጋራ፡ናቸው፤እኔም፡ከሕፃንነቴ፡ዠምሬ፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡በፊታችኹ፡ኼድኹ።

3እንሆኝ፤በእግዚአብሔርና፡ርሱ፡በቀባው፡ፊት፡መስክሩብኝ፤የማንን፡በሬ፡ወሰድኹ፧የማንንስ፡አህያ፡ ወሰድኹ፧ማንንስ፡ሸነገልኹ፧በማንስ፡ላይ፡ግፍ፡አደረግኹ፧ዐይኖቼንስ፡ለማሳወር፡ከማን፡ጋራ፡እጅ፡ጕቦ፡ ተቀበልኹ፧እኔም፡እመልስላችዃለኹ።

4እነርሱም፦አልሸነገልኸንም፥ግፍም፡አላደረግኽብንም፥ከሰውም፡እጅ፡ምንም፡አልወሰድኽም፡አሉ።

5ርሱም፦በእጄ፡ምንም፡እንዳላገኛችኹ፡እግዚአብሔርና፡ርሱ፡የቀባው፡ዛሬ፡በእናንተ፡ላይ፡ምስክሮች፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ናቸው፡አላቸው፤እነርሱም፦ምስክር፡ነው፡አሉ።

6ሳሙኤልም፡ሕዝቡን፡አለ፦ሙሴንና፡አሮንን፡ያላቀ፥አባቶቻችኹንም፡ከግብጽ፡ምድር፡ያወጣ፡ እግዚአብሔር፡ነው።

7አኹንም፡እግዚአብሔር፡ለእናንተና፡ለአባቶቻችኹ፡ስላደረገው፡ጽድቅ፡ዅሉ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ እሟገታችኹ፡ዘንድ፡በዚህ፡ቁሙ።

8ያዕቆብና፡ልጆቹ፡ወደ፡ግብጽ፡በገቡ፡ጊዜ፡ግብጻውያን፡አስጨነቋቸው፤አባቶቻችኹም፡ወደ፡ እግዚአብሔር፡ጮኹ፥እግዚአብሔርም፡ሙሴንና፡አሮንን፡ላከ፥አባቶቻችኹንም፡ከግብጽ፡አውጥተው፡በዚህ፡ ቦታ፡አኖሯቸው።

9አምላካቸውንም፡እግዚአብሔርን፡ረሱ፥ለአሶር፡ሰራዊትም፡አለቃ፡ለሢሣራ፡እጅ፥ለፍልስጥኤማውያንም፡ እጅ፥ለሞዐብም፡ንጉሥ፡እጅ፡አሳልፎ፡ሰጣቸው፥ከነርሱም፡ጋራ፡ተዋጉ።

10እነርሱም፦እግዚአብሔርን፡ትተን፡በዓሊምንና፡ዐስታሮትን፡በማምለካችን፡በድለናል፤አኹንም፡ ከጠላቶቻችን፡እጅ፡አድነን፥እናመልክኽማለን፡ብለው፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ጮኹ።

11እግዚአብሔርም፡ይሩበአልም፥ባርቅንም፥ዮፍታሔንም፥ሳሙኤልንም፡ላከ፥በዙሪያችኹም፡ካሉት፡ ከጠላቶቻችኹ፡እጅ፡አዳናችኹ፤ተዘልላችኹም፡ተቀመጣችኹ።

12የዐሞንም፡ልጆች፡ንጉሥ፡ናዖስ፡እንደ፡መጣባችኹ፡ባያችኹ፡ጊዜ፥አምላካችኹ፡እግዚአብሔር፡ ንጉሣችኹ፡ሳለ።እንዲህ፡አይኹን፥ነገር፡ግን፥ንጉሥ፡ይንገሥልን፡አላችኹኝ።

13አኹንም፡የመረጣችኹትንና፡የፈለጋችኹትን፡ንጉሥ፡እዩ፤እንሆም፥እግዚአብሔር፡ንጉሥ፡አደረገላችኹ።

14እግዚአብሔርን፡ብትፈሩ፡ብታመልኩትም፥ቃሉንም፡ብትሰሙ፥በእግዚአብሔርም፡ትእዛዝ፡ላይ፡ ባታምፁ፥እናንተና፡በእናንተ፡ላይ፡የነገሠው፡ንጉሥ፡አምላካችኹን፡እግዚአብሔርን፡ብትከተሉ፥መልካም፡ ይኾንላችዃል።

15ነገር፡ግን፥የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ባትሰሙ፥በእግዚአብሔርም፡ትእዛዝ፡ላይ፡ብታምፁ፥በእናንተና፡ በንጉሣችኹ፡ላይ፡የእግዚአብሔር፡እጅ፡ትኾናለች።

16አኹንም፡ቁሙ፥እግዚአብሔርም፡በዐይናችኹ፡ፊት፡ወደሚያደርገው፡ወደዚህ፡ታላቅ፡ነገር፡ተመልከቱ።

17የስንዴ፡መከር፡ዛሬ፡አይደለምን፧ወደ፡እግዚአብሔር፡እጮኻለኹ፥ርሱም፡ነጐድጓድና፡ዝናብ፡ ይልካል፤እናንተም፡ንጉሥ፡በመለመናችኹ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ያደረጋችኹት፡ክፋት፡ታላቅ፡እንደ፡ኾነ፡ ታውቃላችኹ፡ታያላችኹም።

18ሳሙኤልም፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ጮኸ፥እግዚአብሔርም፡በዚያን፡ቀን፡ነጐድጓድና፡ዝናብ፡ ላከ፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡እግዚአብሔርንና፡ሳሙኤልን፡እጅግ፡ፈሯቸው።

19ሕዝቡም፡ዅሉ፡ሳሙኤልን፦ንጉሥ፡በመለመናችን፡በኀጢአታችን፡ዅሉ፡ላይ፡ይህን፡ክፋት፡ ጨምረናልና፥እንዳንሞት፡ስለ፡ባሪያዎችኽ፡ወደ፡አምላክኽ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ጸልይ፡አሉት።

20ሳሙኤልም፡ሕዝቡን፡አለ፦አትፍሩ፤በእውነት፡ይህን፡ክፋት፡ዅሉ፡አደረጋችኹ፤ነገር፡ ግን፥እግዚአብሔርን፡በፍጹም፡ልባችኹ፡አምልኩት፡እንጂ፡እግዚአብሔርን፡ከመከተል፡ፈቀቅ፡አትበሉ።

21ምናምንቴ፡ነውና፥የማይረባንና፡የማያድን፡ከንቱን፡ነገር፡ለመከተል፡ፈቀቅ፡አትበሉ።

22እግዚአብሔር፡ለርሱ፡ሕዝብ፡ያደርጋችኹ፡ዘንድ፡ወዷ፟ልና፥እግዚአብሔር፡ስለ፡ታላቅ፡ስሙ፡ሕዝቡን፡ አይተውም።

23ደግሞ፡መልካሙንና፡ቅኑን፡መንገድ፡አስተምራችዃለኹ፡እንጂ፡ስለ፡እናንተ፡መጸለይን፡በመተው፡ እግዚአብሔርን፡እበድል፡ዘንድ፡ይህ፡ከእኔ፡ይራቅ።

24ብቻ፡እግዚአብሔርን፡ፍሩ፥ያደረገላችኹንም፡ታላቅ፡ነገር፡አይታችዃልና፥በፍጹም፡ልባችኹ፡በእውነት፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org አምልኩት።

25ነገር፡ግን፥ክፉ፡ብትሠሩ፡እናንተም፡ንጉሣችኹም፡ትጠፋላችኹ።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source