1እግዚአብሔርም፡ሳሙኤልን፦በእስራኤል፡ላይ፡እንዳይነግሥ፡ለናቅኹት፡ለሳኦል፡የምታለቅስለት፡እስከ፡ መቼ፡ነው፧በቀንድኽ፡ዘይቱን፡ሞልተኽ፡ኺድ፤በልጆቹ፡መካከል፡ንጉሥ፡አዘጋጅቻለኹና፡ወደ፡እሴይ፡ ወደ፡ቤተ፡ልሔም፡እልክኻለኹ፡አለው። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
2ሳሙኤልም፦እንዴት፡እኼዳለኹ፧ሳኦል፡ቢሰማ፡ይገድለኛል፡አለ።እግዚአብሔርም፦አንዲት፡ጊደር፡ ይዘኽ፡ኺድና፥ለእግዚአብሔር፡እሠዋ፡ዘንድ፡መጣኹ፡በል።
3እሴይንም፡ወደ፡መሥዋዕቱ፡ጥራው፥የምታደርገውንም፡አስታውቅኻለኹ፤የምነግርኽንም፡ቅባልኝ፡አለው።
4ሳሙኤልም፡እግዚአብሔር፡የተናገረውን፡አደረገ፥ወደ፡ቤተ፡ልሔምም፡መጣ።የአገሩም፡ሽማግሌዎች፡ እየተንቀጠቀጡ፡ሊገናኙት፡መጡና።የመጣኸው፡ለደኅንነት፡ነውን፧አሉት።
5ርሱም፦ለደኅንነት፡ነው፤ለእግዚአብሔር፡እሠዋ፡ዘንድ፡መጣኹ፤ቅዱሳን፡ኹኑ፥ከእኔም፡ጋራ፡ወደ፡ መሥዋዕቱ፡ኑ፡አለ።እሴይንና፡ልጆቹንም፡ቀደሳቸው፥ወደ፡መሥዋዕቱም፡ጠራቸው።
6እንዲህም፡ኾነ፤በመጡ፡ጊዜ፡ወደ፡ኤልያብ፡ተመልክቶ፦በእውነት፡እግዚአብሔር፡የሚቀባው፡በፊቱ፡ ነው፡አለ።
7እግዚአብሔር፡ግን፡ሳሙኤልን፦ፊቱን፡የቁመቱንም፡ዘለግታ፡አትይ፤ሰው፡እንዲያይ፡እግዚአብሔር፡ አያይምና፡ናቅኹት፤ሰው፡ፊትን፡ያያል፥እግዚአብሔር፡ግን፡ልብን፡ያያል፡አለው።
8እሴይም፡ዐሚናዳብን፡ጠርቶ፡በሳሙኤል፡ፊት፡አሳለፈው፤ርሱም፦ይህን፡ደግሞ፡እግዚአብሔር፡ አልመረጠውም፡አለ።
9እሴይም፡ሳማን፡አሳለፈው፤ርሱም፦ይህን፡ደግሞ፡እግዚአብሔር፡አልመረጠውም፡አለ።
10እሴይም፡ከልጆቹ፡ሰባቱን፡በሳሙኤል፡ፊት፡አሳለፋቸው።ሳሙኤልም፡እሴይን፦እግዚአብሔር፡እነዚህን፡ አልመረጠም፡አለው።
11ሳሙኤልም፡እሴይን፦የቀረ፡ሌላ፡ልጅ፡አለኽን፧አለው።ርሱም፦ታናሹ፡ገና፡ ቀርቷል፤እንሆም፥በጎችን፡ይጠብቃል፡አለ።ሳሙኤልም፡እሴይን፦ርሱ፡እስኪመጣ፡ድረስ፡አንረፍቅምና፡ ልከኽ፡አስመጣው፡አለው።
12ልኮም፡አስመጣው፤ርሱም፡ቀይ፥ዐይኑም፡የተዋበ፥መልኩም፡ያማረ፡ነበረ።እግዚአብሔርም፦ይህ፡ ነውና፥ተነሥተኽ፡ቅባው፡አለ።
13ሳሙኤልም፡የዘይቱን፡ቀንድ፡ወስዶ፡በወንድሞቹ፡መካከል፡ቀባው።የእግዚአብሔርም፡መንፈስ፡ከዚያ፡ ቀን፡ዠምሮ፡በዳዊት፡ላይ፡በኀይል፡መጣ።ሳሙኤልም፡ተነሥቶ፡ወደ፡አርማቴም፡ኼደ።
14የእግዚአብሔርም፡መንፈስ፡ከሳኦል፡ራቀ፥ክፉም፡መንፈስ፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡አሠቃየው።
15የሳኦልም፡ባሪያዎች፦እንሆ፥ክፉ፡መንፈስ፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ያሠቃይኻል፤
16በገና፡መልካም፡አድርጎ፡የሚመታ፡ሰው፡ይሹ፡ዘንድ፡ጌታችን፡በፊቱ፡የሚቆሙትን፡ባሪያዎቹን፡ ይዘዝ፤ከእግዚአብሔርም፡ዘንድ፡ክፉ፡መንፈስ፡በኾነብኽ፡ጊዜ፡በእጁ፡ሲመታ፡አንተ፡ደኅና፡ትኾናለኽ፡ አሉት።
17ሳኦልም፡ባሪያዎቹን፦መልካም፡አድርጎ፡በገና፡መምታት፡የሚችል፡ሰው፡ፈልጋችኹ፡አምጡልኝ፡ አላቸው።
18ከብላቴናዎቹም፡አንዱ፡መልሶ፦እንሆ፥መልካም፡አድርጎ፡በገና፡የሚመታ፡የቤተ፡ልሔማዊውን፡ የእሴይን፡ልጅ፡አይቻለኹ፤ርሱም፡ጽኑዕ፡ኀያል፡ነው፥በነገርም፡ብልኅ፥መልኩም፡ያማረ፡ ነው፥እግዚአብሔርም፡ከርሱ፡ጋራ፡ነው፡አለ።
19ሳኦልም፡ወደእሴይ፡መልክተኛዎች፡ልኮ፦ከበጎች፡ጋራ፡ያለውን፡ልጅኽን፡ዳዊትን፡ላክልኝ፡አለ።
20እሴይም፡እንጀራና፡የወይን፡ጠጅ፡አቍማዳ፡የተጫነ፡አህያ፡የፍየልም፡ጠቦት፡ወስዶ፡በልጁ፡በዳዋት፡ እጅ፡ወደ፡ሳኦል፡ላከ።
21ዳዊትም፡ወደ፡ሳኦል፡መጣ፥በፊቱም፡ቆመ፤እጅግም፡ወደደው፥ለርሱም፡ጋሻ፡ዣግሬው፡ኾነ።
22ሳኦልም፡ወደ፡እሴይ፦በዐይኔ፡ሞገስ፡አግኝቷልና፥ዳዊት፡በፊቴ፥እባክኽ፥ይቁም፡ብሎ፡ላከ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
23እንዲህም፡ኾነ፤ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ክፉ፡መንፈስ፡በሳኦል፡ላይ፡በኾነ፡ጊዜ፡ዳዊት፡በገና፡ይዞ፡ በእጁ፡ይመታ፡ነበር፤ሳኦልንም፡ደስ፡ያሠኘው፡ያሳርፈውም፡ነበር፥ክፉ፡መንፈስም፡ከርሱ፡ይርቅ፡ነበር።