1ፍልስጥኤማውያንም፡ጭፍራዎቻቸውን፡በይሁዳ፡ባለው፡በሰኮት፡አከማቹ፤በሰኮትና፡በዓዜቃ፡መካከል፡ በኤፌስደሚም፡ሰፈሩ።
2ሳኦልና፡የእስራኤል፡ሰዎች፡ተከማቹ፥በዔላ፡ሸለቆም፡ሰፈሩ፥ከፍልስጥኤማውያንም፡ጋራ፡ሊዋጉ፡ተሰለፉ።
3ፍልስጥኤማውያንም፡ባንድ፡ወገን፡በተራራ፡ላይ፡ቆመው፡ነበር፥እስራኤልም፡በሌላው፡ወገን፡በተራራ፡ ላይ፡ቆመው፡ነበር፤በመካከላቸውም፡ሸለቆ፡ነበረ።
4ከፍልስጥኤማውያንም፡ሰፈር፡የጌት፡ሰው፡ጎልያድ፥ቁመቱም፡ስድስት፡ክንድ፡ከስንዝር፡የኾነ፥ዋነኛ፡ ዠግና፡መጣ።
5በራሱም፡የናስ፡ቍር፡ደፍቶ፡ነበር፥ጥሩርም፡ለብሶ፡ነበር፤የጥሩሩም፡ሚዛን፡ዐምስት፡ሺሕ፡ሰቅል፡ናስ፡ ነበረ።
6በእግሮቹም፡ላይ፡የናስ፡ገንባሌ፡ነበረ፥የናስም፡ጭሬ፡በትከሻው፡ላይ፡ነበረ።
7የጦሩም፡የቦ፡እንደ፡ሸማኔ፡መጠቅለያ፡ነበረ፤የጦሩም፡ሚዛን፡ስድስት፡መቶ፡ሰቅል፡ብረት፡ነበረ፤ጋሻ፡ ዣግሬውም፡በፊቱ፡ይኼድ፡ነበር።
8ርሱም፡ቆሞ፡ወደእስራኤል፡ጭፍራዎች፡ጮኸ፦ለሰልፍ፡ትሠሩ፡ዘንድ፡ለምን፡ወጣችኹ፧እኔ፡ ፍልስጥኤማዊ፥እናንተም፡የሳኦል፡ባሪያዎች፡አይደላችኹምን፧ለእናንተ፡አንድ፡ሰው፡ምረጡ፥ወደ፡እኔም፡ ይውረድ፤
9ከእኔም፡ጋራ፡ሊዋጋ፡ቢችል፡ቢገድለኝም፥ባሪያዎች፡እንኾናችዃለን፤እኔ፡ግን፡ባሸንፈው፡ ብገድለውም፥እናንተ፡ባሪያዎች፡ትኾኑናላችኹ፥ለእኛም፡ትገዛላችኹ፡አለ።
10ፍልስጥኤማዊውም፦ዛሬ፡የእስራኤልን፡ጭርራዎች፡ተገዳደርዃቸው፤እንዋጋ፡ዘንድ፡አንድ፡ሰው፡ስጡኝ፡ አለ።
11ሳኦልና፡እስራኤልም፡ዅሉ፡እንዲህ፡የሚላቸውን፡የፍልስጥኤማዊውን፡ቃል፡በሰሙ፡ጊዜ፡እጅግ፡ ፈሩ፥ደነገጡም።
12ዳዊትም፡የዚያ፡የኤፍራታዊው፡ሰው፡ልጅ፡ነበረ፤ያም፡ሰው፡ከቤተ፡ልሔም፡ይሁዳ፡ስሙም፡እሴይ፡ ነበረ፤ስምንትም፡ልጆች፡ነበሩት፤በሳኦልም፡ዘመን፡በዕድሜ፡አርጅቶ፡ሸምግሎም፡ነበር።
13የእሴይም፡ሦስቱ፡ታላላቆች፡ልጆቹ፡ሳኦልን፡ተከትለው፡ወደ፡ሰልፉ፡ኼደው፡ነበር፤ወደ፡ሰልፉም፡ የኼዱት፡የሦስቱ፡ልጆቹ፡ስም፡ይህ፡ነበረ፤ታላቁ፡ኤልያብ፡ኹለተኛውም፡ዐሚናዳብ፡ሦስተኛውም፡ሳማ፡ ነበረ።
14ዳዊት፡የዅሉ፡ታናሽ፡ነበረ፤ሦስቱም፡ታላላቆች፡ሳኦልን፡ተከትለው፡ነበር።
15ዳዊትም፡የአባቱን፡በጎች፡ለመጠበቅ፡ከሳኦል፡ዘንድ፡ወደ፡ቤተ፡ልሔም፡ይመላለስ፡ነበር።
16ፍልስጥኤማዊውም፡ጧትና፡ማታ፡ይቀርብ፥አርባ፡ቀንም፡ይታይ፡ነበር።
17እሴይም፡ልጁን፡ዳዊትን፡እንዲህ፡አለው፦ከዚህ፡ከተጠበሰው፡እሸት፡አንድ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡ እነዚህንም፡ዐሥር፡እንጀራዎች፡ለወንድሞችኽ፡ውሰድ፥ወደ፡ሰፈሩም፡ወደ፡ወንድሞችኽ፡ፈጥነኽ፡ አድርሳቸው፤
18ይህንም፡ዐሥሩን፡አይብ፡ወደ፡ሻለቃው፡ውሰደው፤የወንድሞችኽንም፡ደኅንነት፡ጠይቅ፥ወሬያቸውንም፡ አምጣልኝ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
19ሳኦልና፡እነርሱ፡የእስራኤልም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ከፍልስጥኤማውያን፡ጋራ፡እየተዋጉ፡በዔላ፡ሸለቆ፡ነበሩ።
20ዳዊትም፡ማልዶ፡ተነሣ፥በጎቹንም፡ለጠባቂ፡ተወ፥እሴይም፡ያዘዘውን፡ይዞ፡ኼደ፤ጭፍራውም፡ተሰልፎ፡ ሲወጣ፡ለሰልፍም፡ሲጮኽ፡በሠረገላዎች፡ወደተከበበው፡ሰፈር፡መጣ።
21እስራኤልና፡ፍልስጥኤማውያን፡ፊት፡ለፊት፡ተሰላልፈው፡ነበር።
22ዳዊትም፡ዕቃውን፡በዕቃ፡ጠባቂው፡እጅ፡አኖረው፥ወደ፡ሰራዊቱም፡ሮጠ፥የወንድሞቹንም፡ደኅንነት፡ ጠየቀ።
23ርሱም፡ሲነጋገራቸው፥እንሆ፥ጎልያድ፡የተባለው፡ያ፡ዋነኛ፡ዠግና፡ፍልስጥኤማዊ፡የጌት፡ሰው፡ ከፍልስጥኤማውያን፡ጭፍራ፡መካከል፡ወጣ፥የተናገረውንም፡ቃል፡ተናገረ፤ዳዊትም፡ሰማ።
24የእስራኤልም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ሰውዮውን፡ባዩ፡ጊዜ፡እጅግ፡ፈርተው፡ከርሱ፡ሸሹ።
25የእስራኤልም፡ሰዎች፦ይህን፡የወጣውን፡ሰው፡አያችኹትን፧በእውነት፡እስራኤልን፡ሊገዳደር፡ ወጣ፤የሚገድለውንም፡ሰው፡ንጉሡ፡እጅግ፡ባለጠጋ፡ያደርገዋል፥ልጁንም፡ይድርለታል፤ያባቱንም፡ቤተ፡ሰብ፡ በእስራኤል፡ዘንድ፡ከግብር፡ነጻ፡ያወጣቸዋል፡አሉ።
26ዳዊትም፡በአጠገቡ፡ለቆሙት፡ሰዎች፦ይህን፡ፍልስጥኤማዊ፡ለሚገድል፥ከእስራኤልም፡ተግዳሮትን፡ ለሚያርቅ፡ሰው፡ምን፡ይደረግለታል፧የሕያውን፡አምላክ፡ጭፍራዎች፡የሚገዳደር፡ይህ፡ያልተገረዘ፡ ፍልስጥኤማዊ፡ማን፡ነው፧ብሎ፡ተናገራቸው።
27ሕዝቡም፦ለሚገድለው፡ሰው፡እንዲህ፡ይደረግለታል፡ብለው፡እንደ፡ቀድሞው፡መለሱለት።
28ታላቅ፡ወንድሙም፡ኤልያብ፡ከሰዎች፡ጋራ፡ሲነጋገር፡ሰማ፤የኤልያብም፡ቍጣ፡በዳዊት፡ላይ፡ ነዶ፟፦ለምን፡ወደዚህ፡ወረድኽ፧እነዚያንስ፡ጥቂቶች፡በጎች፡በምድረ፡በዳ፡ለማን፡ተውኻቸው፧እኔ፡ ኵራትኽንና፡የልብኽን፡ክፋት፡ዐውቃለኹና፡ሰልፉን፡ለማየት፡መጥተኻል፡አለው።
29ዳዊትም፦እኔ፡ምን፡አደረግኹ፧ይህ፡ታላቅ፡ነገር፡አይደለምን፧አለ።
30ዳዊትም፡ከርሱ፡ወደ፡ሌላ፡ሰው፡ዘወር፡አለ፥እንደዚህም፡ያለ፡ነገር፡ተናገረ፤ሕዝቡም፡እንደ፡ ቀድሞው፡ያለ፡ነገር፡መለሱለት።
31ዳዊትም፡የተናገረው፡ቃል፡ተሰማ፥ለሳኦልም፡ነገሩት፤ወደ፡ርሱም፡አስጠራው።
32ዳዊትም፡ሳኦልን፦ስለ፡ርሱ፡የማንም፡ልብ፡አይውደቅ፤እኔ፡ባሪያኽ፡ኼጄ፡ያንን፡ፍልስጥኤማዊ፡ እወጋዋለኹ፡አለው።
33ሳኦልም፡ዳዊትን፦አንተ፡ገና፡ብላቴና፡ነኽና፥ርሱም፡ከብላቴንነቱ፡ዠምሮ፡ጦረኛ፡ነውና፥ይህን፡ ፍልስጥኤማዊ፡ለመውጋት፡ትኼድ፡ዘንድ፡አትችልም፡አለው።
34ዳዊትም፡ሳኦልን፡አለው፦እኔ፡ባሪያኽ፡የአባቴን፡በጎች፡ስጠብቅ፡አንበሳና፡ድብ፡ይመጣ፡ ነበር፥ከመንጋውም፡ጠቦት፡ይወስድ፡ነበር።
35በዃላውም፡እከተለውና፡እመታው፡ነበር፥ከአፉም፡አስጥለው፡ነበር፤በተነሣብኝም፡ጊዜ፡ጕረሮውን፡ይዤ፡ እመታውና፡እገድለው፡ነበር።
36እኔ፡ባሪያኽ፡አንበሳና፡ድብ፡መታኹ፤ይህም፡ያልተገረዘው፡ፍልስጥኤማዊ፡የሕያውን፡አምላክ፡ ጭፍራዎች፡ተገዳድሯልና፥ከነርሱ፡እንደ፡አንዱ፡ይኾናል።
37ዳዊትም፦ከአንበሳና፡ከድብ፡እጅ፡ያስጣለኝ፡እግዚአብሔር፡ከዚህ፡ፍልስጥኤማዊ፡እጅ፡ያስጥለኛል፡ አለ።ሳኦልም፡ዳዊትን፦ኺድ፥እግዚአብሔርም፡ከአንተ፡ጋራ፡ይኾናል፡አለው።
38ሳኦልም፡ዳዊትን፡የገዛ፡ራሱን፡ልብስ፡አለበሰው፥በራሱም፡ላይ፡የናስ፡ቍር፡ደፋለት፥ጥሩርም፡ አለበሰው።
39ዳዊትም፡ሰይፉን፡በልብሱ፡ላይ፡ታጠቀ፥ገናም፡አልፈተነውምና፡መኼድ፡ሞከረ።ዳዊትም፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ሳኦልን፦አልፈተንኹትምና፡እንዲህ፡ብዬ፡መኼድ፡አልችልም፡አለው።
40ዳዊትም፡አወለቀ።በትሩንም፡በእጁ፡ወሰደ፥ከወንዝም፡ዐምስት፡ድብልብል፡ድንጋዮችን፡ መረጠ፥በእረኛ፡ኰረጆውም፡በኪሱ፡ከተታቸው፤ወንጭፍም፡በእጁ፡ነበረ፤ወደ፡ፍልስጥኤማዊውም፡ቀረበ።
41ፍልስጥኤማዊውም፡መጥቶ፡ወደ፡ዳዊት፡ቀረበ፤ጋሻ፡ዣግሬውም፡በፊቱ፡ይኼድ፡ነበር።
42ጎልያድም፡ዳዊትን፡ትኵር፡ብሎ፡አየው፤ቀይ፡ብላቴና፡መልኩም፡ያማረ፡ነበረና፡ናቀው።
43ፍልስጥኤማዊውም፡ዳዊትን፦በትር፡ይዘኽ፡የምትመጣብኝ፡እኔ፡ውሻ፡ ነኝን፧አለው።ፍልስጥኤማዊውም፡በአምላኮቹ፡ስም፡ዳዊትን፡ረገመው።
44ፍልስጥኤማዊውም፡ዳዊትን፦ወደ፡እኔ፡ና፥ሥጋኽንም፡ለሰማይ፡ወፎችና፡ለምድር፡አራዊት፡እሰጣለኹ፡ አለው።
45ዳዊትም፡ፍልስጥኤማዊውን፡አለው፦አንተ፡ሰይፍና፡ጦር፡ጭሬም፡ይዘኽ፡ትመጣብኛለኽ፤እኔ፡ግን፡ ዛሬ፡በተገዳደርኸው፡በእስራኤል፡ጭፍራዎች፡አምላክ፡ስም፡በሰራዊት፡ጌታ፡በእግዚአብሔር፡ስም፡ እመጣብኻለኹ።
46እግዚአብሔር፡ዛሬ፡አንተን፡በእጄ፡አሳልፎ፡ይሰጣል፤እመታኽማለኹ፥ራስኽንም፡ከአንተ፡ አነሣዋለኹ፤የፍልስጥኤማውያንንም፡ሰራዊት፡ሬሶች፡ለሰማይ፡ወፎችና፡ለምድር፡አራዊት፡ዛሬ፡ እሰጣለኹ።ይኸውም፡ምድር፡ዅሉ፡በእስራኤል፡ዘንድ፡አምላክ፡እንዳለ፡ታውቅ፡ዘንድ፤
47ይህም፡ጉባኤ፡ዅሉ፡እግዚአብሔር፡በሰይፍና፡በጦር፡የሚያድን፡እንዳይደል፡ያውቅ፡ዘንድ፡ነው።ሰልፉ፡ ለእግዚአብሔር፡ነውና፤እናንተንም፡በእጃችን፡አሳልፎ፡ይሰጣል።
48ፍልስጥኤማዊውም፡ተነሥቶ፡ዳዊትን፡ሊገናኘው፡በቀረበ፡ጊዜ፡ዳዊት፡ፍልስጥኤማዊውን፡ሊገናኘው፡ወደ፡ ሰልፉ፡ሮጠ።
49ዳዊትም፡እጁን፡ወደ፡ኰረጆው፡አግብቶ፡አንድ፡ድንጋይ፡ወሰደ፥ወነጨፈውም፥ፍልስጥኤማዊውንም፡ ግንባሩን፡መታ፤ድንጋዩም፡በግንባሩ፡ተቀረቀረ፥ርሱም፡በምድር፡ላይ፡በፊቱ፡ተደፋ።
50ዳዊትም፡ፍልስጥኤማዊውን፡በወንጭፍና፡በድንጋይ፡አሸነፈው፥ፍልስጥኤማዊውንም፡መቶ፟፡ ገደለ፤በዳዊትም፡እጅ፡ሰይፍ፡አልነበረም።
51ዳዊትም፡ሮጦ፡በፍልስጥኤማዊው፡ላይ፡ቆመ፤ሰይፉንም፡ይዞ፡ከሰገባው፡መዘዘው፥ገደለውም፥ራሱንም፡ ቈረጠው።ፍልስጥኤማውያንም፡ዋናቸው፡እንደ፡ሞተ፡ባዩ፡ጊዜ፡ሸሹ።
52የእስራኤልና፡የይሁዳ፡ሰዎች፡ተነሥተው፡እልል፡አሉ፥ፍልስጥኤማውያንንም፡እስከ፡ጌትና፡እስከ፡ አስቀሎና፡በር፡ድረስ፡አሳደዷቸው።ፍልስጥኤማውያንም፡ከሸዓራይም፡ዠምሮ፡እስከ፡ጌትና፡እስከ፡ዐቃሮን፡ ድረስ፡በመንገድ፡ላይ፡የተመቱት፡ወደቁ።
53የእስራኤልም፡ልጆች፡ፍልስጥኤማውያንን፡ከማሳደድ፡ተመልሰው፡ሰፈራቸውን፡በዘበዙ።
54ዳዊትም፡የፍልስጥኤማዊውን፡ራስ፡ይዞ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡አመጣው፤ጋሻ፡ጦሩን፡ግን፡በድንኳኑ፡ ውስጥ፡አኖረው።
55ሳኦልም፡ዳዊትን፡ወደ፡ፍልስጥኤማዊው፡ሲወጣ፡ባየው፡ጊዜ፡ለሰራዊቱ፡አለቃ፡ለአበኔር፦አበኔር፡ ሆይ፥ይህ፡ብላቴና፡የማን፡ልጅ፡ነው፧አለው።አበኔርም፦ንጉሥ፡ሆይ፥በሕያው፡ነፍስኽ፡እምላለኹ! አላውቅም፡አለ።
56ንጉሡም፦ይህ፡ብላቴና፡የማን፡ልጅ፡እንደ፡ኾነ፡አንተ፡ጠይቅ፡አለ።
57ዳዊትም፡ፍልስጥኤማዊውን፡ገድሎ፡በተመለሰ፡ጊዜ፡አበኔር፡ወሰደው፥ወደሳኦልም፡ፊት፡ አመጣው፤የፍልስጥኤማዊውንም፡ራስ፡በእጁ፡ይዞ፡ነበር።
58ሳኦልም፦አንተ፡ብላቴና፥የማን፡ልጅ፡ነኽ፧አለው።ዳዊትም፦እኔ፡የቤተ፡ልሔሙ፡የባሪያኽ፡የእሴይ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ልጅ፡ነኝ፡ብሎ፡መለሰ።