1ሐናም፡ስትጸልይ፡እንዲህ፡አለች፦ልቤ፡በእግዚአብሔር፡ጸና፥ቀንዴ፡በእግዚአብሔር፡ከፍ፡ከፍ፡ አለ፤አፌ፡በጠላቶቼ፡ላይ፡ተከፈተ፤በማዳንኽ፡ደስ፡ብሎኛል።
2እንደ፡እግዚአብሔር፡ቅዱስ፡የለምና፥እንደ፡አምላካችንም፡ጻድቅ፡የለምና፤ከአንተ፡በቀር፡ቅዱስ፡የለም።
3አትታበዩ፥በኵራትም፡አትናገሩ፤እግዚአብሔር፡ዐዋቂ፡ነውና፥እግዚአብሔርም፡ሥራውን፡የሚመዝን፡ ነውና፥ከአፋችኹ፡የኵራት፡ነገር፡አይውጣ።
4የኀያላንን፡ቀስት፡ሰብሯል፥ደካማዎችንም፡በኀይል፡ታጥቀዋል።
5ጠግበው፡የነበሩ፡እንጀራ፡ዐጡ፤ተርበው፡የነበሩ፡ከራብ፡ዐርፈዋል፤መካኒቱ፡ሰባት፡ወልዳለችና፥ብዙም፡ የወለደችው፡ደክማለች።
6እግዚአብሔር፡ይገድላል፡ያድናልም፤ወደ፡ሲኦል፡ያወርዳል፥ያወጣል።
7እግዚአብሔር፡ድኻ፡ያደርጋል፥ባለጠጋም፡ያደርጋል፤ያዋርዳል፥ደግሞም፡ከፍ፡ከፍ፡ያደርጋል።
8ከሕዝቡ፡መኳንንት፡ጋራ፡ያስቀምጣቸው፡ዘንድ፥የክብርንም፡ዙፋን፡ያወርሳቸው፡ዘንድ፥ችግረኛውን፡ ከመሬት፡ያስነሣል፥ምስኪኑንም፡ከጕድፍ፡ያስነሣል፤የምድር፡መሠረቶች፡የእግዚአብሔር፡ናቸውና፥በእነርሱ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ላይም፡ዓለምን፡አደረገ።
9ርሱ፡የቅዱሳኑን፡እግር፡ይጠብቃል፡ኃጥኣን፡ግን፡ዝም፡ብለው፡በጨለማ፡ይቀመጣሉ፤ሰው፡በኀይሉ፡ አይበረታምና።
10ከእግዚአብሔር፡ጋራ፡የሚጣሉ፡ይደቃ፟ሉ፤በሰማይም፡ያንጐደጕድባቸዋል፤እግዚአብሔር፡እስከምድር፡ ዳርቻ፡ይፈርዳል፤ለንጉሡም፡ኀይል፡ይሰጣል፤የመሲሑንም፡ቀንድ፡ከፍ፡ከፍ፡ያደርጋል።
11ሕልቃናም፡ወደ፡ቤቱ፡ወደ፡አርማቴም፡ኼደ፤ብላቴናውም፡በካህኑ፡በዔሊ፡ፊት፡እግዚአብሔርን፡ ያገለግል፡ነበር።
12የዔሊም፡ልጆች፡ምናምንቴዎች፡ነበሩ፤እግዚአብሔርንም፡አያውቁም፡ነበር።
13የካህናትም፡ልማድ፡በሕዝቡ፡ዘንድ፡እንዲህ፡ነበረ፤ሰው፡ዅሉ፡መሥዋዕት፡ሲያቀርብ፡ሥጋው፡በተቀቀለ፡ ጊዜ፡የካህኑ፡ሎሌ፡ይመጣ፡ነበር፥በእጁም፡ሦስት፡ጣት፡ያለው፡ሜንጦ፡ነበረ፤
14ወደ፡ድስቱም፡ወይም፡ወደ፡ምንቸቱ፡ወይም፡ወደ፡አፍላሉ፡ወይም፡ወደ፡ቶፋው፡ይሰደ፟ው፡ ነበር፤ሜንጦውም፡ያወጣውን፡ዅሉ፡ካህኑ፡ለርሱ፡ይወስደው፡ነበር።ወደዚያም፡በመጡት፡በእስራኤላውያን፡ ላይ፡በሴሎ፡እንዲህ፡ያደርጉ፡ነበር።
15ደግሞም፡ስቡን፡ሳያቃጥሉ፡የካህኑ፡ሎሌ፡መጥቶ፡የሚሠዋውን፡ሰው፦ጥሬውን፡እንጂ፡የተቀቀለውን፡ ሥጋ፡ከአንተ፡አይወስድምና፡እጠብስለት፡ዘንድ፡ለካህኑ፡ሥጋ፡ስጠኝ፡ይለው፡ነበር።
16ሰውዮውም፦አስቀድሞ፡ስቡን፡ያቃጥሉት፡ዃላም፡ሰውነትኽ፡ደስ፡የሚያሠኛትን፡ትወስዳለኽ፡ ቢለው፥ርሱ፦አይኾንም፥ነገር፡ግን፥አኹን፡ስጠኝ፤እንቢም፡ብትል፡በግድ፡እወስደዋለኹ፡ይለው፡ነበር።
17ሰዎቹም፡የእግዚአብሔርን፡ቍርባን፡ይንቁ፡ነበርና፥የጐበዛዝቱ፡ኀጢአት፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡እጅግ፡ ታላቅ፡ነበረች።
18ሳሙኤል፡ግን፡ገና፡ብላቴና፡ሳለ፡የበፍታ፡ኤፉድ፡ለብሶ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ያገለግል፡ነበር።
19እናቱም፡ታናሽ፡መደረቢያ፡ሠራችለት፥በየዓመቱም፡መሥዋዕት፡ለመሠዋት፡ከባሏ፡ጋራ፡ስትወጣ፡ ታመጣለት፡ነበር።
20ዔሊም፡ሕልቃናንና፡ሚስቱን፦ለእግዚአብሔር፡ስለ፡ተሳለችው፡ስጦታ፡ፋንታ፡ከዚች፡ሴት፡እግዚአብሔር፡ ዘር፡ይስጥኽ፡ብሎ፡ባረካቸው፤እነርሱም፡ወደ፡ቤታቸው፡ኼዱ።
21እግዚአብሔርም፡ሐናን፡ዐሰበ፥ፀነሰችም፥ሦስት፡ወንዶችና፡ኹለትም፡ሴቶች፡ልጆች፡ ወለደች።ብላቴናውም፡ሳሙኤል፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡አደገ።
22ዔሊም፡እጅግ፡አረጀ፤ልጆቹም፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ላይ፡ያደረጉትን፡ዅሉ፥በመገናኛውም፡ድንኳን፡ ደጅ፡ከሚያገለግሉት፡ሴቶች፡ጋራ፡እንደ፡ተኙ፡ሰማ።
23ርሱም፡አላቸው፦ስለ፡ክፉ፡ሥራችኹ፡ከዚህ፡ሕዝብ፡ዅሉ፡ሰምቻለኹና፡ስለምን፡እንዲህ፡ያለ፡ነገር፡ ታደርጋላችኹ፧
24ልጆቼ፡ሆይ፥የእግዚአብሔርን፡ሕዝብ፡ኀጢአተኛ፡በማድረጋችኹ፡ስለ፡እናንተ፡የደረሰኝ፡ወሬ፡ መልካም፡አይደለምና፡ይህ፡አይኾንም።
25ሰውስ፡ሰውን፡ቢበድል፡እግዚአብሔር፡ይፈርድበታል፤ሰው፡ግን፡እግዚአብሔርን፡ቢበድል፡ስለ፡ርሱ፡ የሚለምን፡ማን፡ነው፧እነርሱ፡ግን፡እግዚአብሔር፡ሊገድላቸው፡ወዷ፟ልና፥የአባታቸውን፡ቃል፡አልሰሙም።
26ብላቴናውም፡ሳሙኤል፡እያደገ፡ኼደ፤በእግዚአብሔርም፡በሰውም፡ፊት፡ሞገስ፡እያገኘ፡ኼደ።
27የእግዚአብሔርም፡ሰው፡ወደ፡ዔሊ፡መጥቶ፡አለው፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በግብጽ፡በፈርዖን፡ ቤት፡ባሪያ፡ሳለ፡ለአባትኽ፡ቤት፡ተገለጥኹ፤
28ከእስራኤልም፡ነገድ፡ዅሉ፡ካህን፡ይኾነኝ፡ዘንድ፥በመሠዊያዬ፡ላይ፡ይሠዋ፡ዘንድ፥ዕጣንንም፡ያጥን፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ዘንድ፡ኤፉድንም፡በፊቴ፡ይለብስ፡ዘንድ፡ለእኔ፡መረጥኹት፤የእስራኤልንም፡ልጆች፡የእሳት፡ቍርባን፡ዅሉ፡ ስለ፡ምግብ፡ለአባትኽ፡ቤት፡ሰጠኹ።
29በማደሪያዬ፡ያቀርቡት፡ዘንድ፡ያዘዝኹትን፡መሥዋዕቴንና፡ቍርባኔን፡ስለ፡ምን፡ ረገጣችኹ፧እንድትወፍሩም፡የሕዝቤን፡የእስራኤልን፡ቍርባን፡ዅሉ፡መዠመሪያ፡በመብላታችኹ፡ከእኔ፡ይልቅ፡ ልጆችኽን፡ለምን፡አከበርኽ፧
30ስለዚህም፡የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በእውነት፡ቤትኽ፡የአባትኽም፡ቤት፡ ለዘለዓለም፡በፊቴ፡እንዲኖር፡ተናግሬያለኹ፤አኹን፡ግን፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ያከበሩኝን፡ አከብራለኹና፥የናቁኝም፡ይናቃሉና፡ይህ፡አይኾንልኝም።
31እንሆ፥ለቤትኽ፡ሽማግሌ፡እንዳይገኝ፥ክንድኽን፡የአባትኽንም፡ቤት፡ክንድ፡የምሰብርበት፡ዘመን፡ ይመጣል።
32በእስራኤል፡በረከት፡ዅሉ፥በማደሪያዬ፡ጠላትኽን፡ታያለኽ፡በቤትኽም፡ለዘለዓለም፡ሽማግሌ፡አይገኝም።
33ከመሠዊያዬ፡ያልተቈረጠ፡ልጅኽ፡ቢገኝ፡ዐይንኽን፡ያፈዘ፟ዋል፥ነፍስኽንም፡ያሳዝናል፡ከቤትኽም፡ የሚወለዱ፡ሰዎች፡ዅሉ፡በጐልማስነት፡ይሞታሉ።
34ይህ፡በኹለቱ፡ልጆችኽ፡በአፍኒንና፡በፊንሐስ፡ላይ፡የሚመጣ፡ለአንተ፡ምልክት፡ነው፤ኹለቱ፡ባንድ፡ ቀን፡ይሞታሉ።
35የታመነም፡ካህን፡ለእኔ፡አስነሣለኹ፥በልቤም፡በነፍሴም፡እንዳለ፡እንዲሁ፡ያደርጋል፤እኔም፡የታመነ፡ ቤት፡እሠራለታለኹ፥ዘመኑን፡ዅሉ፡እኔ፡በቀባኹት፡ሰው፡ፊት፡ይኼዳል።
36ከቤትኽም፡የቀረው፡ዅሉ፡ይመጣል፥በፊቱም፡ሰግዶ፥ቍራሽ፡እንጀራ፡እበላ፡ዘንድ፡ከካህናት፡ወደ፡ አንዲቱ፡ዕጣ፥እባክኽ፥ስደደኝ፡ብሎ፡አንድ፡ብር፡አንድ፡እንጀራም፡ይለምናል።