1ብላቴናውም፡ሳሙኤል፡በዔሊ፡ፊት፡እግዚአብሔርን፡ያገለግል፡ነበር፤በዚያም፡ዘመን፡የእግዚአብሔር፡ ቃል፡ብርቅ፡ነበረ፤ራእይም፡አይገለጥም፡ነበር።
2በዚያም፡ዘመን፡እንዲህ፡ኾነ፤የዔሊ፡ዐይኖች፡ማየት፡እስኪሳናቸው፡ድረስ፡መፍዘዝ፡ዠምረው፡ነበር።
3ዔሊም፡በስፍራው፡ተኝቶ፡ሳለ፥የእግዚአብሔር፡መብራት፡ገና፡ሳይጠፋ፥ሳሙኤልም፡የእግዚአብሔር፡ ታቦት፡ባለበት፡በእግዚአብሔር፡መቅደስ፡ተኝቶ፡ሳለ፥
4እግዚአብሔር፡ሳሙኤልን፡ጠራው፤ርሱም፦እንሆኝ፡አለ።
5ወደ፡ዔሊም፡ሮጠ፦እንሆኝ፡የጠራኸኝ፡አለው።ርሱም፦አልጠራኹኽም፤ተመልሰኽ፡ተኛ፡ አለው።ኼዶም፡ተኛ።
6እግዚአብሔርም፡ደግሞ፦ሳሙኤል፡ሆይ፡ብሎ፡ጠራው።ሳሙኤልም፡ተነሥቶ፡ወደ፡ዔሊ፡ ኼደና፦እንሆኝ፡የጠራኸኝ፡አለው።ርሱም፦ልጄ፡ሆይ፥አልጠራኹኽም፤ተመልሰኽ፡ተኛ፡ብሎ፡መለሰ።
7ሳሙኤል፡ግን፡ገና፡እግዚአብሔርን፡አላወቀም፡ነበር፥የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ገና፡አልተገለጠለትም፡ ነበር።
8እግዚአብሔርም፡ሳሙኤልን፡እንደ፡ገና፡ሦስተኛ፡ጊዜ፡ጠራው።ርሱም፡ተነሥቶ፡ወደ፡ዔሊ፡ ኼደና፦እንሆኝ፡የጠራኸኝ፡አለ።ዔሊም፡እግዚአብሔር፡ብላቴናውን፡እንደ፡ጠራው፡አስተዋለ።
9ዔሊም፡ሳሙኤልን፦ኼደኽ፡ተኛ፡ቢጠራኽም፦አቤቱ፥ባሪያኽ፡ይሰማልና፥ተናገር፡በለው፡ አለው።ሳሙኤልም፡ኼዶ፡በስፍራው፡ተኛ።
10እግዚአብሔርም፡መጥቶ፡ቆመ፥እንደ፡ቀድሞውም፦ሳሙኤል፥ሳሙኤል፥ብሎ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ጠራው።ሳሙኤልም፦ባሪያኽ፡ይሰማልና፥ተናገር፡አለው።
11እግዚአብሔርም፡ሳሙኤልን፡አለው፦እንሆ፥የሰማውን፡ዅሉ፡ኹለቱ፡ዦሮዎቹ፡ጭው፡የሚያደርግ፡ አንድ፡ነገርን፡በእስራኤል፡አደርጋለኹ።
12በዚያም፡ቀን፡በቤቱ፡ላይ፡የተናገርኹትን፡ዅሉ፡በዔሊ፡አወርዳለኹ፤እኔም፡ዠምሬ፡እፈጽምበታለኹ።
13ልጆቹ፡የርግማን፡ነገር፡እንዳደረጉ፡ዐውቆ፡አልከለከላቸውምና፡ስለ፡ኀጢአቱ፡በቤት፡ለዘለዓለም፡ እንድፈርድ፡አስታውቄዋለኹ።
14ስለዚህም፡የዔሊ፡ቤት፡ኀጢአት፡በመሥዋዕትና፡በቍርባን፡ለዘለዓለም፡እንዳይሰረይለት፡ለዔሊ፡ቤት፡ ምያለኹ።
15ሳሙኤልም፡እስኪነጋ፡ተኛ፥ማልዶም፡ተነሥቶ፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡ደጅ፡ከፈተ።ሳሙኤልም፡ራእዩን፡ ለዔሊ፡መንገር፡ፈራ።
16ዔሊም፡ሳሙኤልን፡ጠርቶ፦ልጄ፡ሳሙኤል፡ሆይ፥አለ፤ርሱም፦እንሆኝ፡አለ።
17ርሱም፦እግዚአብሔር፡የነገረኽ፡ነገር፡ምንድር፡ነው፧ከእኔ፡አትሸሽግ፤ከነገረኽ፡ነገር፡ዅሉ፡ የሸሸግኸኝ፡እንደ፡ኾነ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ያድርግብኽ፥እንዲህም፡ይጨምርብኽ፡አለው።
18ሳሙኤልም፡ነገሩን፡ዅሉ፡ነገረው፥አንዳችም፡አልሸሸገውም።ዔሊም፦ርሱ፡እግዚአብሔር፡ነው፤ደስ፡ ያሠኘውን፡ያድርግ፡አለ።
19ሳሙኤልም፡አደገ፥እግዚአብሔርም፡ከርሱ፡ጋራ፡ነበረ፤ከቃሉም፡አንዳች፡በምድር፡ላይ፡አይወድቅም፡ ነበር።
20እስራኤልም፡ዅሉ፡ከዳን፡እስከ፡ቤርሳቤሕ፡ድረስ፡ሳሙኤል፡ለእግዚአብሔር፡ነቢይ፡ይኾን፡ዘንድ፡ የታመነ፡እንደ፡ኾነ፡ዐወቀ።
21እግዚአብሔርም፡ደግሞ፡በሴሎ፡ተገለጠ፤እግዚአብሔርም፡በእግዚአብሔር፡ቃል፡ለሳሙኤል፡በሴሎ፡ ይገለጥ፡ነበር።የሳሙኤልም፡ቃል፡ለእስራኤል፡ዅሉ፡ደረሰ።