1ዳዊትም፡ከአርማቴም፡አገር፡ከነዋትዘራማ፡ሸሸ፥ወደ፡ዮናታንም፡መጥቶ፦ምን፡አደረግኹ፧እኔንስ፡ ለመግደል፡የሚፈልግ፡በአባትኽ፡ፊት፡ጠማምነቴና፡ኀጢአቴ፡ምንድር፡ነው፧ብሎ፡ተናገረው።
2ዮናታንም፦ይህንስ፡ያርቀው፥አትሞትም፤እንሆ፥አባቴ፡አስቀድሞ፡ለእኔ፡ሳይገልጥ፡ትልቅም፡ትንሽም፡ ነገር፡ቢኾን፡አያደርግም፤አባቴስ፡ይህን፡ነገር፡ለምን፡ይሰውረኛል፧እንዲህ፡አይደለም፡አለው።
3ዳዊትም፦እኔ፡በፊትኽ፡ሞገስ፡እንዳገኘኹ፡አባትኽ፡በእውነት፡ያውቃል፤ርሱም፦ዮናታን፡እንዳይከፋው፡ አይወቅ፡ይላል፤ነገር፡ግን፥ሕያው፡እግዚአብሔርን! በሕያው፡ነፍስኽም፡እምላለኹ! በእኔና፡በሞት፡መካከል፡ አንድ፡ርምጃ፡ያኽል፡ቀርቷል፡ብሎ፡ማለ።
4ዮናታንም፡ዳዊትን፦ነፍስኽ፡የወደደችውን፡ዅሉ፡አደርግልኻለኹ፡አለው።
5ዳዊትም፡ዮናታንን፡አለው፦እንሆ፥ነገ፡መባቻ፡ነው፤በንጉሥም፡አጠገብ፡ለምሳ፡አልቀመጥም፤እስከ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ሦስተኛው፡ቀን፡ማታ፡ድረስ፡በውጭ፡በሜዳ፡እንድሸሸግ፡አሰናብተኝ።
6አባትኽም፡ቢፈልገኝ።ለዘመዶቹ፡ዅሉ፡በዚያ፡በቤተ፡ልሔም፡የዓመት፡መሥዋዕት፡አላቸውና፡ዳዊት፡ ወደ፡ከተማው፡ፈጥኖ፡ይኼድ፡ዘንድ፡አጽንቶ፡ለምኖኛል፡በለው።
7ርሱም፦መልካም፡ነው፡ቢል፡ለእኔ፡ለባሪያኽ፡ደኅንነት፡ይኾናል፤ቢቈጣ፡ግን፡ክፋት፡ከርሱ፡ዘንድ፡ በእኔ፡ላይ፡እንደ፡ተቈረጠች፡ዕወቅ።
8እንግዲህ፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ኪዳን፡ከባሪያኽ፡ጋራ፡አድርገኻልና፥ለባሪያኽ፡ቸርነት፡አድርግ፤በደል፡ ግን፡ቢገኝብኝ፡አንተ፡ግደለኝ፤ለምን፡ወደ፡አባትኽ፡ታደርሰኛለኽ፧
9ዮናታንም፦ይህ፡ከአንተ፡ይራቅ፤ከአባቴ፡ዘንድ፡ክፋት፡በላይኽ፡እንደ፡ተቈጠረች፡ያወቅኹ፡እንደ፡ኾነ፡ አልነግርኽምን፧አለ።
10ዳዊትም፡ዮናታንን፦አባትኽ፡ስለ፡እኔ፡ክፉ፡ነገር፡የነገረኽ፡እንደ፡ኾን፡ማን፡ይነግረኛል፧አለው።
11ዮናታንም፡ዳዊትን፦ና፡ወደ፡ሜዳ፡እንውጣ፡አለው።ኹለቱም፡ወደ፡ሜዳ፡ወጡ።
12ዮናታንም፡ዳዊትን፡አለው፦የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ምስክር፡ይኹን፤ነገ፡ወይም፡ከነገ፡ ወዲያ፡በዚህ፡ጊዜ፡አባቴን፡መርምሬ፥እንሆ፥በዳዊት፡ላይ፡መልካም፡ቢያስብ፡ልኬ፡እገልጥልኻለኹ፤
13አባቴም፡ባንተ፡ላይ፡ክፋት፡ማድረግ፡ቢወድ፟፡እኔም፡ባላስታውቅኽ፡በደኅና፡ትኼድ፡ዘንድ፡ ባላሰናብትኽ፥እግዚአብሔር፡በዮናታን፡ይህን፡ያድርግ፡ይህንም፡ይጨምር፤እግዚአብሔርም፡ከአባቴ፡ጋራ፡ እንደ፡ነበረ፡ከአንተ፡ጋራ፡ይኹን።
14እኔም፡እንዳልሞት፡በሕይወቴ፡ዘመን፡የእግዚአብሔርን፡ቸርነት፡አድርግልኝ፤
15ደግሞም፡እግዚአብሔር፡የዳዊትን፡ጠላቶች፡ዅሉ፡እያንዳንዱ፡ከምድር፡ባጠፋቸው፡ጊዜ፡ለዘለዓለም፡ ቸርነትኽን፡ከቤቴ፡አታርቀው።
16ዮናታንም፦እግዚአብሔር፡ከዳዊት፡ጠላቶች፡እጅ፡ይፈልገው፡ብሎ፡ከዳዊት፡ቤት፡ጋራ፡ቃል፡ኪዳን፡ አደረገ።
17ዮናታንም፡ዳዊትን፡እንደ፡ነፍሱ፡ይወድ፟፡ነበርና፥እንደ፡ገና፡ማለለት።
18ዮናታንም፡አለው፦ነገ፡መባቻ፡ነው፥መቀመጫኽም፡ባዶ፡ኾኖ፡ይገኛልና፥ትታሰባለኽ።
19ሦስት፡ቀንም፡ያኽል፡ቈይ፤ከዚህም፡በዃላ፡ፈጥነኽ፡ውረድ፥ነገሩም፡በተደረገበት፡ቀን፡ ወደተሸሸግኽበት፡ስፍራ፡ኺድ፥በኤዜል፡ድንጋይም፡አጠገብ፡ቈይ።
20እኔም፡በዐላማ፡ላይ፡እወረውራለኹ፡ብዬ፡ሦስት፡ፍላጻዎችን፡ወደ፡አጠገቡ፡እወረውራለኹ።
21እንሆም፦ኺድ፡ፍላጻዎችን፡ፈልግ፡ብዬ፡ብላቴናውን፡እልከዋለኹ፤ብላቴናውንም፦እንሆ፥ፍላጻው፡ ከአንተ፡ወደዚህ፡ነው፤ይዘኸው፡ወደ፡እኔ፡ና፡ያልኹት፡እንደ፡ኾነ፥ሕያው፡እግዚአብሔርን! ለአንተ፡ ደኅንነት፡ነውና፥ምንም፡የለብኽም።
22ብላቴናውን፡ግን፦እንሆ፥ፍላጻው፡ከአንተ፡ወዲያ፡ነው፡ያልኹት፡እንደ፡ኾነ፥እግዚአብሔር፡ አሰናብቶኻልና፥መንገድኽን፡ኺድ።
23አንተና፡እኔም፡ስለ፡ተነጋገርነው፥እንሆ፥እግዚአብሔር፡ለዘለዓለም፡በመካከላችን፡ምስክር፡ነው።
24ዳዊትም፡በሜዳው፡ተሸሸገ፤መባቻም፡በኾነ፡ጊዜ፡ንጉሡ፡ግብር፡ለመብላት፡ተቀመጠ።
25ንጉሡም፡እንደ፡ቀድሞው፡በግንቡ፡አጠገብ፡በዙፋኑ፡ላይ፡ተቀመጠ፤ዮናታንም፡ቆሞ፡ነበር፥አበኔርም፡ በሳኦል፡አጠገብ፡ተቀመጠ፤የዳዊትም፡ስፍራ፡ባዶውን፡ነበረ።
26ሳኦልም፦አንድ፡ነገር፡ኾኗል፥ንጹሕም፡አይደለም፤በእውነት፡ንጹሕ፡አይደለም፡ብሎ፡ ዐስቧልና፥በዚያን፡ቀን፡ምንም፡አልተናገረም። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
27ከመባቻም፡በዃላ፡በማግስቱ፡በኹለተኛው፡ቀን፡የዳዊት፡ስፍራ፡ባዶውን፡ነበረ፤ሳኦልም፡ልጁን፡ ዮናታንን፦የእሴይ፡ልጅ፡ትናንትና፡ወይም፡ዛሬ፡ግብር፡ሊበላ፡ያልመጣ፡ስለ፡ምን፡ነው፧አለው።
28ዮናታንም፡ለሳኦል፦ዳዊት፡ወደ፡ቤተ፡ልሔም፡ይኼድ፡ዘንድ፡አጽንቶ፡ለመነኝ፤
29ርሱም፦ዘመዶቼ፡በከተማ፡ውስጥ፡መሥዋዕት፡አላቸውና፥ወንድሜም፡ ጠርቶኛልና፥እባክኽ፥አሰናብተኝ፤አኹንም፡በዐይኖችኽ፡ሞገስ፡አግኝቼ፡እንደ፡ኾነ፡ልኺድና፡ወንድሞቼን፡ ልይ፡አለ፤ስለዚህ፥ወደ፡ንጉሥ፡ሰደቃ፡አልመጣም፡ብሎ፡መለሰለት።
30የሳኦልም፡ቍጣ፡በዮናታን፡ላይ፡ነደደና።አንተ፡የጠማማ፡ሴት፡ልጅ፥የእሴይን፡ልጅ፡ለአንተ፡ማፈሪያ፡ ለእናትኽም፡ኀፍረተ፡ሥጋ፡ማፈሪያ፡እንደ፡መረጥኽ፡እኔ፡አላውቅምን፧
31የእሴይም፡ልጅ፡በምድር፡ላይ፡በሕይወት፡በሚኖርበት፡ዘመን፡ዅሉ፡አንተና፡መንግሥትኽ፡ አትጸኑም፤አኹንም፡የሞት፡ልጅ፡ነውና፥ልከኽ፡አስመጣልኝ፡አለው።
32ዮናታንም፡ለአባቱ፡ለሳኦል።ስለ፡ምን፡ይሞታል፧ያደረገውስ፡ምንድር፡ነው፧ብሎ፡መለሰለት።
33ሳኦልም፡ሊወጋው፡ጦሩን፡ወረወረበት፤ዮናታንም፡አባቱ፡ዳዊትን፡ፈጽሞ፡ሊገድለው፡እንደ፡ፈቀደ፡ ዐወቀ።
34አባቱ፡ዳዊትን፡ስላሳፈረው፡ዮናታን፡ስለ፡ዳዊት፡ዐዝኗልና፥እጅግ፡ተቈጥቶ፡ከሰደቃው፡ ተነሣ፥በመባቻውም፡በኹለተኛ፡ቀን፡ግብር፡አልበላም።
35እንዲህም፡ኾነ፤በነጋው፡ዮናታን፡ከዳዊት፡ጋራ፡ወደተቃጠረበት፡ቦታ፡ወደ፡ሜዳ፡ወጣ፥ከርሱም፡ጋራ፡ ታናሽ፡ብላቴና፡ነበረ።
36ብላቴናውንም፦ሮጠኽ፡የምወረውራቸውን፡ፍላጻዎች፡ፈልግልኝ፡አለው።ብላቴናውም፡በሮጠ፡ጊዜ፡ ፍላጻውን፡ወደ፡ማዶ፡ወረወረው።
37ብላቴናውም፡ዮናታን፡ፍላጻውን፡ወደወረወረበት፡ስፍራ፡በመጣ፡ጊዜ፡ዮናታን፦ፍላጻው፡ከአንተ፡ወዲያ፡ ነው፡ብሎ፡ወደ፡ብላቴናው፡ጮኸ።
38ዮናታንም፡ደግሞ፦ቶሎ፡ፍጠን፥አትቈይ፡ብሎ፡ወደ፡ብላቴናው፡ጮኸ፤የዮናታንም፡ብላቴና፡ ፍላጻዎቹን፡ሰብስቦ፡ወደ፡ጌታው፡መጣ።
39ዮናታንና፡ዳዊት፡ብቻ፡ነገሩን፡ያውቁ፡ነበር፡እንጂ፡ብላቴናው፡ምንም፡አያውቅም፡ነበር።
40ዮናታንም፡መሣሪያውን፡ለብላቴናው፡ሰጥቶ፦ወደ፡ከተማ፡ውሰድ፡አለው።
41ብላቴናውም፡በኼደ፡ጊዜ፡ዳዊት፡ከስፍራው፡በደቡብ፡አጠገብ፡ተነሣ፥በምድርም፡ላይ፡በግንባሩ፡ ተደፋ፥ሦስት፡ጊዜም፡ለሰላምታ፡ሰገደ፤እየተላቀሱም፡ርስ፡በርሳቸው፡ተሳሳሙ፥ይልቁንም፡ዳዊት፡እጅግ፡ አለቀሰ።
42ዮናታንም፡ዳዊትን፦በደኅና፡ኺድ፤እንሆ፥እኛ፡ኹለታችን፡በእኔና፡በአንተ፥በዘሬና፡በዘርኽ፡መካከል፡ ለዘለዓለም፡እግዚአብሔር፡ይኹን፡ብለን፡በእግዚአብሔር፡ስም፡ተማምለናል፡አለው።ዳዊትም፡ተነሥቶ፡ ኼደ፤ዮናታንም፡ወደ፡ከተማ፡ገባ።