1ዳዊትም፡ወደ፡ካህኑ፡ወደ፡አቢሜሌክ፡ወደ፡ኖብ፡መጣ፤አቢሜሌክም፡እየተንቀጠቀጠ፡ዳዊትን፡ ሊገናኘው፡መጣና፦ስለ፡ምን፡አንተ፡ብቻኽን፡ነኽ፧ከአንተስ፡ጋራ፡ስለ፡ምን፡ማንም፡የለም፧አለው።
2ዳዊትም፡ካህኑን፡አቢሜሌክን፦የተላክኽበትን፡ነገርና፡የሰጠኹኽን፡ትእዛዝ፡ማንም፡አይወቅ፡ብሎ፡ ንጉሡ፡አንድ፡ነገር፡አዞ፟ኛል፤ስለዚህም፡ብላቴናዎቹን፡እንዲህ፡ባለ፡ስፍራ፡ተውዃቸው።
3አኹንስ፡በእጅኽ፡ምን፡አለ፧ዐምስት፡እንጀራ፡ወይም፡የተገኘውን፡በእጄ፡ስጠኝ፡አለው። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
4ካህኑም፡ለዳዊት፡መልሶ፦ዅሉ፡የሚበላው፡እንጀራ፡የለኝም፥ነገር፡ግን፥የተቀደስ፡እንጀራ፡ አለ፤ብላቴናዎቹ፡ከሴቶቹ፡ንጹሓን፡እንደ፡ኾኑ፡መብላት፡ይቻላል፡አለው።
5ዳዊትም፡ለካህኑ፡መልሶ፦በእውነት፡ከወጣን፡ዠምረን፡እኛ፡ሰውነታችንን፡ከሴቶች፡ሦስት፡ቀን፡ ጠብቀናል፤የብላቴናዎችም፡ዕቃ፡የተቀደሰች፡ናት፤ስለዚህ፥ዛሬ፡ዕቃቸው፡የተቀደሰች፡በመኾኗ፥እንጀራው፡ እንደሚበላ፡እንጀራ፡ይኾናል፡አለው።
6ካህኑም፡በርሱ፡ፋንታ፡ትኵስ፡እንጀራ፡ይደረግ፡ዘንድ፡ከእግዚአብሔር፡ፊት፡ከተነሣው፡ከገጹ፡ኅብስት፡ በቀር፡ሌላ፡እንጀራ፡አልነበረምና፡የተቀደሰውን፡እንጀራ፡ሰጠው።
7በዚያም፡ቀን፡ከሳኦል፡ባሪያዎች፡አንድ፡ሰው፡በዚያ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ተገኝቶ፡ነበር፤ስሙም፡ ኤዶማዊው፡ዶይቅ፡ነበረ፥ለሳኦልም፡የእረኛዎቹ፡አለቃ፡ነበረ።
8ዳዊትም፡አቢሜሌክን፦የንጉሥ፡ጕዳይ፡ስላስቸኰለኝ፡ሰይፌንና፡መሣሪያዬን፡አላመጣኹምና፡ባንተ፡ዘንድ፡ ጦር፡ወይም፡ሰይፍ፡አለ፡ወይ፧አለው።
9ካህኑም፦በኤላ፡ሸለቆ፡የገደልኸው፡የፍልስጥኤማዊው፡የጎልያድ፡ሰይፍ፥እንሆ፥በመጐናጸፊያ፡ተጠቅሎ፟፡ ከዚህ፡ከኤፉዱ፡በዃላ፡አለ፤ትወደ፟ውም፡እንደ፡ኾነ፡ውሰደው፤ሌላ፡ከዚህ፡የለም፡አለ።ዳዊትም፦እንደ፡ ርሱ፡ያለ፡የለምና፡ርሱን፡ስጠኝ፡አለው።
10ዳዊትም፡ተነሣ፡በዚያም፡ቀን፡ሳኦልን፡ፈርቶ፡ሸሸ፥ወደጌትም፡ንጉሥ፡ወደ፡አንኩስ ፡ኼደ።
11የአንኩስ፡ባሪያዎችም፦ይህ፡ዳዊት፡የአገሩ፡ንጉሥ፡አይደለምን፧ሳኦል፡ሺሕ፥ዳዊትም፡እልፍ፡ገደለ፡ ብለው፡ሴቶች፡በዘፈን፡የዘመሩለት፡ርሱ፡አይደለምን፧አሉት።
12ዳዊትም፡ይህን፡ቃል፡በልቡ፡አኖረ፥የጌትንም፡ንጉሥ፡አንኩስን፡እጅግ፡ፈራ።
13በፊታቸውም፡አእምሮውን፡ለወጠ፥በያዙትም፡ጊዜ፡እንደ፡እብድ፡ኾነ፥በበሩም፡መድረክ፡ላይ፡ ተንፈራፈረ፥ልጋጉም፡በጢሙ፡ላይ፡ይወርድ፡ነበር።
14አንኩስም፡ባሪያዎቹን፦እንሆ፥ይህ፡ሰው፡እብድ፡እንደ፡ኾነ፡አይታችዃል፤ለምን፡ወደ፡እኔ፡ አመጣችኹት፧በፊቴ፡ያብድ፡ዘንድ፡ይህን፡ያመጣችኹት፡እብድ፡ጠፍቶብኝ፡ነውን፧እንዲህ፡ያለውስ፡ወደ፡ ቤቴ፡ይገባልን፧አላቸው።