Skip to content
← 1 Samuel

Chapter 22 · Amharic

1 Samuel

1ዳዊትም፡ከዚያ፡ተነሣ፡ወደዓዶላም፡ዋሻ፡ኰበለለ፤ወንድሞቹና፡የአባቱም፡ቤተ፡ሰብ፡ዅሉ፡ይህን፡በሰሙ፡ ጊዜ፡ወደ፡ርሱ፡ወደዚያ፡ወረዱ።

2የተጨነቀውም፡ዅሉ፥ብድርም፡ያለበት፡ዅሉ፥የተከፋም፡ዅሉ፡ወደ፡ርሱ፡ተከማቸ፤ርሱም፡በላያቸው፡ አለቃ፡ኾነ፤ከርሱም፡ጋራ፡አራት፡መቶ፡የሚያኽሉ፡ሰዎች፡ነበሩ።

3ዳዊትም፡ከዚያ፡በሞዐብ፡ምድር፡ወዳለችው፡ወደ፡ምጽጳ፡ኼደ፤የሞዐብንም፡ንጉሥ፦እግዚአብሔር፡ የሚያደርግልኝን፡እስካውቅ፡ድረስ፡አባቴና፡እናቴ፡ከአንተ፡ጋራ፡ይቀመጡ፡ዘንድ፡እለምንኻለኹ፡አለው።

4በሞዐብም፡ንጉሥ፡ፊት፡አመጣቸው፤ዳዊትም፡በዐምባ፡ውስጥ፡በነበረበት፡ወራት፡ዅሉ፡በርሱ፡ዘንድ፡ ተቀመጡ።

5ነቢዩ፡ጋድም፡ዳዊትን፦ተነሥተኽ፡ወደይሁዳ፡ምድር፡ኺድ፡እንጂ፡በዐምባው፡ውስጥ፡አትቀመጥ፡ አለው፤ዳዊትም፡ተነሥቶ፡ወደሔሬት፡ዱር፡መጣ።

6ሳኦልም፡ዳዊትና፡ከርሱ፡ጋራ፡የነበሩት፡እንደ፡ተገለጡ፡ሰማ።ሳኦልም፡በጊብዓ፡በዐጣጥ፡ዛፍ፡ በታች፣በኰረብታው፡ላይ፡ተቀምጦ፥በእጁም፡ጦር፡ይዞ፡ነበር፤ባሪያዎቹም፡ዅሉ፡በአጠገቡ፡ቆመው፡ነበር። 140 ዕብ.፥አኪሽ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

7ሳኦልም፡በአጠገቡ፡የቆሙትን፡ባሪያዎቹን፦ብንያማውያን፡ሆይ፥እንግዲህ፡ስሙ፤በእውኑ፡የእሴይ፡ልጅ፡ ዕርሻና፡የወይን፡ቦታ፡ለኹላችኹ፡ይሰጣችዃልን፧ዅላችኹንስ፡ሻለቃዎችና፡የመቶ፡አለቃዎች፡ያደርጋችዃልን፧

8ዅላችኹ፡በላዬ፡ዶልታችኹ፡ተነሣችኹብኝ፤ልጄ፡ከእሴይ፡ልጅ፡ጋራ፡ሲማማል፡ምንም፡ አይገልጥልኝም፤ከእናንተም፡አንድ፡ለእኔ፡የሚያዝን፡የለም፥ዛሬም፡እንደኾነው፡ዅሉ፡ልጄ፡ባሪያዬን፡ እንዲዶልት፡ሲያስነሣብኝ፡ማንም፡አላስታወቀኝም፡አላቸው።

9በሳኦልም፡ባሪያዎች፡አጠገብ፡የቆመው፡ኤዶማዊው፡ዶይቅ፡መልሶ፦የእሴይ፡ልጅ፡ወደ፡ኖብ፡ ወደአኪጦብ፡ልጅ፡ወደ፡አቢሜሌክ፡ሲመጣ፡አይቼዋለኹ።

10እግዚአብሔርንም፡ጠየቀለት፥ሥንቅንም፡ሰጠው፥የፍልስጥኤማዊውንም፡የጎልያድን፡ሰይፍ፡ሰጠው፡አለ።

11ንጉሡም፡የአኪጦብን፡ልጅ፡ካህኑን፡አቢሜሌክን፡በኖብም፡ያሉትን፡ካህናት፡የአባቱን፡ቤት፡ዅሉ፡ልኮ፡ አስጠራቸው፤ዅላቸውም፡ወደ፡ንጉሡ፡መጡ።

12ሳኦልም፦የአኪጦብ፡ልጅ፡ሆይ፥እንግዲህ፡ስማ፡አለ፤ርሱም፦እንሆኝ፥ጌታዬ፡ሆይ፡ብሎ፡መለሰ።

13ሳኦልም፦አንተና፡የእሴይ፡ልጅ፡ለምን፡ዶለታችኹብኝ፧እንጀራና፡ሰይፍ፡ሰጠኸው፥ዛሬም፡እንደ፡ ትውልድ፡ጠላት፡ኾኖ፡ይነሣብኝ፡ዘንድ፡እግዚአብሔርን፡ስለ፡ርሱ፡ጠየቅኽለት፡አለው።

14አቢሜሌክም፡መልሶ፡ንጉሡን፦ከባሪያዎችኽ፡ዅሉ፡የታመነ፥ለንጉሥም፡ዐማች፡የኾነ፥በትእዛዝኽ፡ የሚኼድ፥በቤትኽም፡የከበረ፡እንደ፡ዳዊት፡ያለ፡ማን፡ነው፧

15በእውኑ፡ስለ፡ርሱ፡እግዚአብሔርን፡እጠይቅ፡ዘንድ፡ዛሬ፡ዠመርኹን፧ይህ፡ከእኔ፡ይራቅ፤እኔ፡ባሪያኽ፡ ይህን፡ዅሉ፡እጅግ፡ወይም፡ጥቂት፡ቢኾን፡አላውቅምና፡ንጉሡ፡እንደዚህ፡ያለውን፡ነገር፡በእኔ፡በባሪያውና፡ በአባቴ፡ቤት፡ዅሉ፡ላይ፡አያኑር፡አለ።

16ንጉሡም፦አቢሜሌክ፡ሆይ፥አንተና፡የአባትኽ፡ቤት፡ዅሉ፡ፈጽማችኹ፡ትሞታላችኹ፡አለ።

17ንጉሡም፡በዙሪያው፡የቆሙትን፡እግረኛዎች፦የእግዚአብሔር፡ካህናት፡እጅ፡ከዳዊት፡ጋራ፡ ነውና፥ኵብለላውንም፡ሲያውቁ፡በዦሮዬ፡አልገለጡምና፡ዞራችኹ፡ግደሏቸው፡አላቸው።የንጉሡ፡ባሪያዎች፡ ግን፡እጃቸውን፡በእግዚአብሔር፡ካህናት፡ላይ፡ይዘረጉ፡ዘንድ፡እንቢ፡አሉ።

18ንጉሡም፡ዶይቅን፦አንተ፡ዞረኽ፡በካህናቱ፡ላይ፡ውደቅባቸው፡አለው።ኤዶማዊውም፡ዶይቅ፡ዞሮ፡ በካህናቱ፡ላይ፡ወደቀ፥በዚያም፡ቀን፡የበፍታ፡ኤፉድ፡የለበሱትን፡ሰማንያ፡ዐምስት፡ሰዎች፡ገደለ።

19የካህናቱም፡ከተማ፡ኖብን፡በሰይፍ፡ስለት፡መታ፤ወንዶችንና፡ሴቶችንም፥ብላቴናዎችንና፡ጡት፡ የሚጠቡትን፥በሬዎችንና፡አህያዎችንም፡በጎችንም፡በሰይፍ፡ስለት፡ገደለ።

20ከአኪጦብም፡ልጅ፡ከአቢሜሌክ፡ልጆች፡ስሙ፡አብያታር ፡የሚባል፡አንዱ፡ልጅ፡አምልጦ፡ወደ፡ዳዊት፡ ሸሸ።

21አብያታርም፡ሳኦል፡የእግዚአብሔርን፡ካህናት፡እንደ፡ፈጀ፡ለዳዊት፡ነገረው።

22ዳዊት፡አብያታርን፦ኤዶማዊው፡ዶይቅ፡በዚያ፡መኖሩን፡ባየኹ፡ጊዜ፦ለሳኦል፡በርግጥ፡ይነግራል፡ብዬ፡ በዚያው፡ቀን፡ዐውቄዋለኹ፤ለአባትኽ፡ቤት፡ነፍስ፡ዅሉ፡የጥፋታቸው፡ምክንያት፡እኔ፡ነኝ።

23ነፍሴን፡የሚፈልግ፡የአንተን፡ነፍስ፡ይፈልጋልና፥ከእኔም፡ጋራ፡ተጠብቀኽ፡ትኖራለኽና፡በእኔ፡ዘንድ፡ ተቀመጥ፥አትፍራ፡አለው።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source