1እንዲህም፡ኾነ፤በዚያ፡ወራት፡ከእስራኤል፡ጋራ፡ይዋጉ፡ዘንድ፡ፍልስጥኤማውያን፡ጭፍራዎቻቸውን፡ ለሰልፍ፡ሰበሰቡ፤አንኩስም፡ዳዊትን፦አንተና፡ሰዎችኽ፡ከእኔ፡ጋራ፡ወደ፡ሰልፍ፡እንድትወጡ፡በርግጥ፡ዕወቅ፡ አለው።
2ዳዊትም፡አንኩስን፦አኹን፡ባሪያኽ፡የሚያደርገውን፡ታያለኽ፡አለው።አንኩስም፡ዳዊትን፦እንግዲህ፡ በዘመኑ፡ዅሉ፡ራሴን፡ጠባቂ፡አደርግኻለኹ፡አለው።
3ሳሙኤል፡ግን፡ሞቶ፡ነበር፥እስራኤልም፡ዅሉ፡አልቅሰውለት፡ነበር፥በከተማውም፡በአርማቴም፡ቀብረውት፡ ነበር።ሳኦልም፡መናፍስት፡ጠሪዎችንና፡ጠንቋዮችን፡ከምድር፡አጥፍቶ፡ነበር።
4ፍልስጥኤማውያንም፡ተሰብስበው፡መጡ፡በሱነምም፡ሰፈሩ፤ሳኦልም፡እስራኤልን፡ዅሉ፡ሰበሰበ፥በጊልቦዓም፡ ሰፈሩ።
5ሳኦልም፡የፍልስጥኤማውያንን፡ጭፍራ፡ባየ፡ጊዜ፡ፈራ፥ልቡም፡እጅግ፡ተንቀጠቀጠ።
6ሳኦልም፡እግዚአብሔርን፡ጠየቀ፤እግዚአብሔርም፡በሕልም፡ወይም፡በኡሪም፡ወይም፡በነቢያት፡ አልመለሰለትም።
7ሳኦልም፡ባሪያዎቹን፦ወደ፡ርሷ፡ኼጄ፡እጠይቅ፡ዘንድ፡መናፍስትን፡የምትጠራ፡ሴት፡ፈልጉልኝ፡ አላቸው፤ባሪያዎቹም፦እንሆ፥መናፍስትን፡የምትጠራ፡አንዲት፡ሴት፡በዐይንዶር፡አለች፡አሉት።
8ሳኦልም፡መልኩን፡ለውጦ፡ሌላ፡ልብስም፡ለብሶ፡ኼደ፥ኹለትም፡ሰዎች፡ከርሱ፡ጋራ፡ነበሩ፥በሌሊትም፡ ወደ፡ሴቲቱ፡መጡ።ርሱም፦እባክሽ፥በመናፍስት፡አሟርቺልኝ፥የምልሽንም፡አስነሺልኝ፡አላት።
9ሴቲቱም፦እንሆ፥መናፍስት፡ጠሪዎችንና፡ጠንቋዮችን፡ከምድር፡እንዳጠፋ፡ሳኦል፡ያደረገውን፡ ታውቃለኽ፤ስለ፡ምን፡እኔን፡ለማስገደል፡ወጥመድ፡ለነፍሴ፡ታደርጋለኽ፧አለችው።
10ሳኦልም፦ሕያው፡እግዚአብሔርን! በዚህ፡ነገር፡ቅጣት፡አያገኝሽም፡ብሎ፡በእግዚአብሔር፡ማለላት።
11ሴቲቱም፦ማንን፡ላስነሣልኽ፧አለች፤ርሱም፦ሳሙኤልን፡አስነሺልኝ፡አለ።
12ሴቲቱም፡ሳሙኤልን፡ባየች፡ጊዜ፡በታላቅ፡ድምፅ፡ጮኸች፤ሴቲቱም፡ሳኦልን፦አንተ፡ሳኦል፡ስትኾን፡ ለምን፡አታለልኸኝ፧ብላ፡ተናገረችው።
13ንጉሡም፦አትፍሪ፤ያየሽው፡ምንድር፡ነው፧አላት።ሴቲቱም፡ሳኦልን፦አማልክት፡ከምድር፡ሲወጡ፡ አየኹ፡አለችው።
14ርሱም፦መልኩ፡ምን፡ዐይነት፡ነው፧አላት።ርሷም፦ሽማግሌ፡ሰው፡ወጣ፤መጐናጸፊያም፡ተጐናጽፏል፡ አለች።ሳኦልም፡ሳሙኤል፡እንደ፡ኾነ፡ዐወቀ፥በፊቱም፡ተጐነበሰ፥በምድርም፡ላይ፡እጅ፡ነሣ።
15ሳሙኤልም፡ሳኦልን፦ለምን፡አወክኸኝ፧ለምንስ፡አስነሣኸኝ፧አለው።ሳኦልም፡ መልሶ፦ፍልስጥኤማውያን፡ይወጉኛልና፥እጅግ፡ተጨንቄያለኹ፥እግዚአብሔርም፡ከእኔ፡ርቋል፤በነቢያት፡ ወይም፡በሕልም፡አልመለሰልኝም፤ስለዚህም፡የማደርገውን፡ታስታውቀኝ፡ዘንድ፡ጠራኹኽ፡አለው።
16ሳሙኤልም፡አለ፦እግዚአብሔር፡ከራቀኽ፡ጠላትም፡ከኾነኽ፡ለምን፡ትጠይቀኛለኽ፧
17እግዚአብሔርም፡በቃሌ፡እንደ፡ተናገረ፡አድርጓል፤እግዚአብሔርም፡መንግሥትኽን፡ከእጅኽ፡ነጥቆ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ለጎረቤትኽ፡ለዳዊት፡ሰጥቶታል።
18የእግዚአብሔርን፡ቃል፡አልሰማኽምና፥በዐማሌቅም፡ላይ፡ታላቅ፡የኾነ፡ቍጣውን፡አላደረግኽምና፡ስለዚህ፡ ዛሬ፡እግዚአብሔር፡ይህን፡ነገር፡አድርጎብኻል።
19እግዚአብሔርም፡እስራኤልን፡ከአንተ፡ጋራ፡በፍልስጥኤማውያን፡እጅ፡አሳልፎ፡ይሰጣል፤ነገም፡አንተና፡ ልጆችኽ፡ከእኔ፡ጋራ፡ትኾናላችኹ፤እግዚአብሔርም፡የእስራኤልን፡ጭፍራ፡ደግሞ፡በፍልስጥኤማውያን፡እጅ፡ አሳልፎ፡ይሰጣል።
20ሳኦልም፡በዚያን፡ጊዜ፡በቁመቱ፡ሙሉ፡በምድር፡ላይ፡ወደቀ፥ከሳሙኤልም፡ቃል፡የተነሣ፡እጅግ፡ ፈራ።በዚያም፡ቀን፡ዅሉ፡በዚያም፡ሌሊት፡ዅሉ፡እንጀራ፡አልበላምና፡ኀይል፡አልቀረለትም።
21ሴቲቱም፡ወደ፡ሳኦል፡መጣች፥እጅግም፡ደንግጦ፡እንደ፡ነበረ፡አይታ፦እንሆ፥እኔ፡ባሪያኽ፡ቃልኽን፡ ሰማኹ፥ነፍሴንም፡በእጄ፡ጣልኹ፥የነገርኸኝንም፡ቃል፡ሰማኹ።
22አኹን፡እንግዲህ፡አንተ፡ደግሞ፡የባሪያኽን፡ቃል፡እንድትሰማ፡እለምንኻለኹ፥በፊትኽም፡ቍራሽ፡እንጀራ፡ ላኑርልኽ፤በመንገድም፡ስትኼድ፡ትበረታ፡ዘንድ፡ብላ፡አለችው።
23ርሱ፡ግን፦አልበላም፡ብሎ፡እንቢ፡አለ፤ነገር፡ግን፥ባሪያዎቹና፡ሴቲቱ፡አስገደዱት፥ቃላቸውንም፡ ሰማ፤ከምድርም፡ተነሥቶ፡በዐልጋ፡ላይ፡ተቀመጠ።
24ለሴቲቱም፡ማለፊያ፡እንቦሳ፡ነበራት፤ፈጥና፡ዐረደችው፤ዱቄቱንም፡ወስዳ፡ለወሰችው፥ቂጣም፡እንጀራ፡ አድርጋ፡ጋገረችው።
25በሳኦልና፡በባሪያዎቹም፡ፊት፡አቀረበችው፤በልተውም፡ተነሡ፥በዚያም፡ሌሊት፡ኼዱ።