1ፍልስጥኤማውያንም፡ጭፍራዎቻቸውን፡ዅሉ፡ወደ፡አፌቅ፡ሰበሰቡ፤እስራኤላውያንም፡በኢይዝራኤል፡ባለው፡ ውሃ፡ምንጭ፡አጠገብ፡ሰፈሩ።
2የፍልስጥኤማውያንም፡አለቃዎች፡በመቶ፡በመቶ፡በሺሕ፡በሺሕ፡እየኾኑ፡ያልፉ፡ነበር፤ዳዊትና፡ሰዎቹም፡ ከአንኩስ፡ጋራ፡በዃለኛው፡ጭፍራ፡በኩል፡ያልፉ፡ነበር።
3የፍልስጥኤማውያንም፡አለቃዎች፦እነዚህ፡ዕብራውያን፡በዚህ፡ምን፡ያደርጋሉ፧አሉ፤አንኩስም፡ የፍልስጥኤማውያንን፡አለቃዎች፦ይህ፡የእስራኤል፡ንጉሥ፡የሳኦል፡ባሪያ፡ዳዊት፡አይደለምን፧ርሱም፡በእነዚህ፡ ቀኖች፡በእነዚህ፡ዓመታት፡ከእኔ፡ጋራ፡ነበረ፥ወደ፡እኔም፡ከተጠጋበት፡ቀን፡ዠምሮ፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡ ምንም፡አላገኘኹበትም፡አላቸው።
4የፍልስጥኤማውያን፡አለቃዎች፡ግን፡ተቈጥተው፦ይህ፡ሰው፡ባስቀመጥኸው፡ስፍራ፡ይቀመጥ፡ዘንድ፡ ይመለስ፤በሰልፉ፡ውስጥ፡ጠላት፡እንዳይኾነን፡ከእኛ፡ጋራ፡ወደ፡ሰልፍ፡አይውረድ፤ከጌታው፡ጋራ፡በምን፡ ይታረቃል፧የእነዚህን፡ሰዎች፡ራስ፡በመቍረጥ፡አይደለምን፧
5ወይስ፡ሴቶች፦ሳኦል፡ሺሕ፡ገደለ፥ዳዊት፡እልፍ፡ገደለ፡ብለው፡በዘፈን፡የዘመሩለት፡ይህ፡ዳዊት፡ አይደለምን፧አሉት።
6አንኩስም፡ዳዊትን፡ጠርቶ፦ሕያው፡እግዚአብሔርን! አንተ፡ቅን፡ነኽ፥ከእኔም፡ጋራ፡በጭፍራው፡በኩል፡ መውጣትኽና፡መግባትኽ፡በፊቴ፡መልካም፡ነው፤ወደ፡እኔም፡ከመጣኽ፡ዠምሮ፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡አንዳች፡ ክፋት፡አላገኘኹብኽም፤ነገር፡ግን፥በአለቃዎች፡ዘንድ፡አልተወደድኽም።
7አኹንም፡ተመልሰኽ፡በደኅና፡ኺድ፥በፍልስጥኤማውያንም፡አለቃዎች፡ዐይን፡ክፋት፡አታድርግ፡አለው።
8ዳዊትም፡አንኩስን፦ምን፡አድርጌያለኹ፧ኼጄስ፡ከጌታዬ፡ከንጉሡ፡ጠላቶች፡ጋራ፡እንዳልዋጋ፥በፊትኽ፡ ከተቀመጥኹ፡ዠምሬ፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡በእኔ፡በባሪያኽ፡ምን፡አግኝተኽብኛል፧አለው። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
9አንኩስም፡መልሶ፡ዳዊትን፦እንደ፡አምላክ፡መልእክተኛ፡በዐይኔ፡ፊት፡መልካም፡እንደ፡ኾንኽ፡ ዐውቃለኹ፤ነገር፡ግን፥የፍልስጥኤማውያን፡አለቃዎች፦ከእኛ፡ጋራ፡ወደ፡ሰልፍ፡አይወጣም፡አሉ።
10አኹንም፡አንተ፡ከአንተም፡ጋራ፡የመጡ፡የጌታኽ፡ባሪያዎች፡ማልዳችኹ፡ተነሡ፤ሲነጋም፡ተነሥታችኹ፡ ኺዱ፡አለው።
11ዳዊትና፡ሰዎቹም፡ማልደው፡ይኼዱ፡ዘንድ፥ወደፍልስጥኤማውያንም፡አገር፡ይመለሱ፡ዘንድ፡ ተነሡ።ፍልስጥኤማውያንም፡ወደ፡ኢይዝራኤል፡ወጡ።