1እንዲህም፡ኾነ፤ዳዊትና፡ሰዎቹ፡በሦስተኛው፡ቀን፡ወደ፡ጺቅላግ፡በመጡ፡ጊዜ፥ዐማሌቃውያን፡በደቡብ፡ አገርና፡በጺቅላግ፡ላይ፡ዘምተው፡ነበር፥ጺቅላግንም፡መትተው፡በእሳት፡አቃጥለዋት፡ነበር፤
2ሴቶቹንና፡በውስጧም፡የነበሩትን፡ዅሉ፡ከታናሽ፡እስከ፡ታላቅ፡ድረስ፡ማርከው፡ነበር፤ዅሉንም፡ወስደው፡ መንገዳቸውን፡ኼዱ፡እንጂ፡አንድስ፡እንኳ፡አልገደሉም፡ነበር።
3ዳዊትና፡ሰዎቹም፡ወደ፡ከተማ፡በመጡ፡ጊዜ፥እንሆ፥በእሳት፡ተቃጥላ፥ሚስቶቻቸውም፡ወንዶችና፡ሴቶች፡ ልጆቻቸውም፡ተማርከው፡አገኙ።
4ዳዊት፡ከርሱም፡ጋራ፡የነበሩ፡ሕዝብ፡ድምፃቸውን፡ከፍ፡አድርገው፡ለማልቀስ፡ኀይል፡እስኪያጡ፡ድረስ፡ አለቀሱ።
5የዳዊትም፡ኹለቱ፡ሚስቶቹ፡ኢይዝራኤላዊቱ፡አኪናሖምና፡የቀርሜሎሳዊው፡የናባል፡ሚስት፡የነበረችው፡ አቢግያ፡ተማርከው፡ነበር።
6ስለ፡ወንዶችና፡ስለ፡ሴቶች፡ልጆቻቸው፡የሕዝቡ፡ዅሉ፡ልብ፡ተቈጥቶ፡ነበርና፥ሕዝቡ፡ሊወግሩት፡ስለ፡ ተናገሩ፡ዳዊት፡እጅግ፡ተጨነቀ፤ዳዊት፡ግን፡በአምላኩ፡በእግዚአብሔር፡ልቡን፡አበረታ።
7ዳዊትም፡የአቢሜሌክን፡ልጅ፡ካህኑን፡አብያታርን፦ኤፉዱን፡አቅርብልኝ፡አለው፤አብያታርም፡ኤፉዱን፡ ለዳዊት፡አቀረበለት።
8ዳዊትም፦የእነዚህን፡ሰራዊት፡ፍለጋ፡ልከተልን፧አገኛቸዋለኹን፧ብሎ፡እግዚአብሔርን፡ ጠየቀ፤ርሱም፦ታገኛቸዋለኽና፥ፈጽመኽም፡ምርኮውን፡ትመልሳለኽና፡ፍለጋቸውን፡ተከተል፡ብሎ፡መለሰለት።
9ዳዊትም፡ከርሱም፡ጋራ፡የነበሩት፡ስድስት፡መቶ፡ሰዎች፡ኼዱ፥እስከ፡ቦሦር፡ወንዝ፡ድረስም፡ መጡ፤ከነርሱም፡የቀሩት፡በዚያ፡ተቀመጡ።
10ዳዊትም፡ከርሱም፡ጋራ፡ያሉት፡አራት፡መቶ፡ሰዎች፡አሳደዱ፤ኹለቱ፡መቶ፡ሰዎች፡ግን፡የቦሦር፡ ወንዝን፡መሻገር፡ደክመዋልና፥እዃላ፡ቀሩ።
11በበረሓውም፡ውስጥ፡አንድ፡ግብጻዊ፡አግኝተው፡ወደ፡ዳዊት፡ይዘውት፡መጡ፤እንጀራም፡ሰጡትና፡ በላ፥ውሃም፡አጠጡት፤
12ከበለሱም፡ጥፍጥፍ፡ቍራጭና፡ኹለት፡የወይን፡ዘለላ፡ሰጡት፤ሦስት፡ቀንና፡ሦስት፡ሌሊት፡እንጀራ፡ አልበላም፡ውሃም፡አልጠጣም፡ነበርና፥በበላ፡ጊዜ፡ነፍሱ፡ወደ፡ርሱ፡ተመለሰች።
13ዳዊትም፦አንተ፡የማን፡ነኽ፧ከወዴት፡መጣኽ፧አለው።ርሱም፦እኔ፡የዐማሌቃዊ፡ባሪያ፡ግብጻዊ፡ ብላቴና፡ነኝ፤ከሦስት፡ቀንም፡በፊት፡ታምሜ፡ነበርና፥ጌታዬ፡ጥሎኝ፡ኼደ።
14እኛም፡በከሊታውያን፡ደቡብ፥በይሁዳም፡ምድር፥በካሌብም፡ደቡብ፡ላይ፡ዘመትን፤ጺቅላግንም፡በእሳት፡ አቃጠልናት፡አለ።
15ዳዊትም፦ወደ፡እነዚያ፡ሰራዊት፡ዘንድ፡ልትመራኝ፡ ትወዳ፟ለኽን፧አለው፤ርሱም፦እንዳትገድለኝ፥ለጌታዬም፡እጅ፡አሳልፈኽ፡እንዳትሰጠኝ፡በአምላክ፡ማልልኝ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org እንጂ፡ወደ፡እነዚያ፡ሰራዊት፡እመራኻለኹ፡አለ።
16ወደ፡ታችም፡እንዲወርድ፡ባደረገው፡ጊዜ፥እንሆ፥ከፍልስጥኤማውያንና፡ከይሁዳ፡ምድር፡ከወሰዱት፡ ከብዙ፡ምርኮ፡ዅሉ፡የተነሣ፡በልተው፡ጠጥተውም፡የበዓልም፡ቀን፡አድርገው፡በምድር፡ዅሉ፡ላይ፡ተበትነው፡ ነበር።
17ዳዊትም፡ከማታ፡ዠምሮ፡እስከ፡ማግስቱ፡ማታ፡ድረስ፡መታቸው፤ከነርሱም፡በግመል፡ተቀምጠው፡ ከሸሹ፡ከአራት፡መቶ፡ጕልማሳዎች፡በቀር፡አንድ፡ያመለጠ፡የለም።
18ዳዊትም፡ዐማሌቃውያን፡የወሰዱትን፡ዅሉ፡አስጣላቸው፥ኹለቱንም፡ሚስቶቹን፡አዳነ።
19ከወንዶችና፡ከሴቶች፡ልጆች፥ከወሰዱትም፡ምርኮ፡ዅሉ፥ታላቅም፡ኾነ፡ታናሽም፡ኾነ፥ምንም፡ የጐደለባቸው፡የለም፤ዳዊትም፡ዅሉን፡አስጣለ።
20ዳዊትም፡የበጉንና፡የላሙን፡መንጋ፡ዅሉ፡ወሰደ፥ከራሱም፡ከብት፡ፊት፡እየነዳ፦ይህ፡የዳዊት፡ምርኮ፡ ነው፡አለ።
21ዳዊትም፡ደክመው፡ዳዊትን፡ይከተሉት፡ዘንድ፡ወዳልቻሉ፥በቦሦር፡ወንዝ፡ወዳስቀራቸው፡ወደ፡ኹለቱ፡ መቶ፡ሰዎች፡መጣ፤እነርሱም፡ዳዊትን፡ከርሱም፡ጋራ፡የነበሩትን፡ሕዝብ፡ሊቀበሉ፡ወጡ፤ዳዊትም፡ወደ፡ ሕዝቡ፡በቀረበ፡ጊዜ፡ደኅንነታቸውን፡ጠየቀ።
22ከዳዊትም፡ጋራ፡ከኼዱ፡ሰዎች፡ክፉዎቹና፡ምናምንቴዎቹ፡ዅሉ፦እነዚህ፡ከእኛ፡ጋራ፡አልመጡምና፡ እየራሳቸው፡ሚስቶቻቸውንና፡ልጆቻቸውን፡ይዘው፡ይኺዱ፡እንጂ፡ካስጣልነው፡ምርኮ፡ምንም፡አንሰጣቸውም፡ አሉ።
23ዳዊትም፦ወንድሞቼ፡ሆይ፥የጠበቀን፡በእኛም፡ላይ፡የመጣውን፡ጭፍራ፡በእጃችን፡አሳልፎ፡የሰጠን፡ እግዚአብሔር፡በሰጠን፡ነገር፡እንዲህ፡አታድርጉ፤
24ይህንስ፡ነገ፡ማን፡ይሰማችዃል፧ነገር፡ግን፡የተዋጉትና፡ዕቃውን፡የጠበቁት፡ዕድል፡ፈንታ፡እኩል፡ ይኾናል፥አንድነት፡ይካፈላሉ፡አለ።
25ከዚያም፡ቀን፡ዠምሮ፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡ይህን፡ለእስራኤል፡ሥርዐትና፡ፍርድ፡አደረገው።
26ዳዊትም፡ወደ፡ጺቅላግ፡በመጣ፡ጊዜ፡ለዘመዶቹ፡ለይሁዳ፡ሽማግሌዎች፦እንሆ፥ከእግዚአብሔር፡ ጠላቶች፡ምርኮ፡በረከትን፡ተቀበሉ፡ብሎ፡ከምርኮው፡ሰደደላቸው።
27በቤቴል፡ለነበሩ፥በራሞት፡በደቡብ፡ለነበሩ፡
28በየቲር፡ለነበሩ፥በዐሮዔር፡ለነበሩ፥በሢፍሞት፡ለነበሩ፥በኤሽትሞዐ፡ለነበሩ፥
29በቀርሜሎስ፡ለነበሩ፥በይረሕምኤላውያንና፡በቄናውያን፡ከተማዎችም፡ለነበሩ፥
30በሔርማ፡ለነበሩ፥በቦራሣን፡ለነበሩ፥በዓታክ፡ለነበሩ፥በኬብሮን፡ለነበሩ፥
31ዳዊትና፡ሰዎቹም፡በተመላለሱበት፡ስፍራ፡ለነበሩ፡ሰዎች፡ዅሉ፡ላከ።