Skip to content
← 1 Samuel

Chapter 7 · Amharic

1 Samuel

1የቂርያትይዓሪም፡ሰዎችም፡መጥተው፡የእግዚአብሔርን፡ታቦት፡አወጡ፥በኰረብታውም፡ላይ፡ወዳለው፡ ወደዐሚናዳብ፡ቤት፡አገቡት፤የእግዚአብሔርም፡ታቦት፡እንዲጠብቅ፡ልጁን፡አልዓዛርን፡ቀደሱት።

2ታቦቱም፡በቂርያትይዓሪም፡ከተቀመጠበት፡ቀን፡ዠምሮ፡ወራቱ፡ረዘመ፥ኻያ፡ዓመትም፡ኾነ፤የእስራኤልም፡ ቤት፡ዅሉ፡ዐዝኖ፡እግዚአብሔርን፡ተከተለ።

3ሳሙኤልም፡የእስራኤልን፡ቤት፡ዅሉ፦በሙሉ፡ልባችኹ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ከተመለሳችኹ፡ እንግዳዎችን፡አማልክትና፡ዐስታሮትን፡ከመካከላችኹ፡አርቁ፥ልባችኹንም፡ወደ፡እግዚአብሔር፡አቅኑ፥ርሱንም፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ብቻ፡አምልኩ፤ከፍልስጥኤማውያንም፡እጅ፡ያድናችዃል፡ብሎ፡ተናገራቸው።

4የእስራኤልም፡ልጆች፡በዓሊምንና፡ዐስታሮትን፡አራቁ፥እግዚአብሔርንም፡ብቻ፡አመለኩ።

5ሳሙኤልም፦እስራኤልን፡ዅሉ፡ወደ፡ምጽጳ፡ሰብስቡ፥ስለ፡እናንተም፡ወደ፡እግዚአብሔር፡እጸልያለኹ፡ አለ።

6ወደ፡ምጽጳም፡ተሰበሰቡ፤ውሃም፡ቀድተው፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡አፈሰሱ፥በዚያም፡ቀን፡ ጾሙ፥በዚያም፦እግዚአብሔርን፡በድለናል፡አሉ።ሳሙኤልም፡በእስራኤል፡ልጆች፡ላይ፡በምጽጳ፡ፈረደ።

7ፍልስጥኤማውያንም፡የእስራኤል፡ልጆች፡ወደ፡ምጽጳ፡እንደ፡ተሰበሰቡ፡በሰሙ፡ጊዜ፡የፍልስጥኤማውያን፡ አለቃዎች፡በእስራኤል፡ላይ፡ወጡ፤የእስራኤልም፡ልጆች፡ሰምተው፡ፍልስጥኤማውያንን፡ፈሩ።

8የእስራኤልም፡ልጆች፡ሳሙኤልን፦ከፍልስጥኤማውያን፡እጅ፡ያድነን፡ዘንድ፡ወደ፡አምላካችን፡ወደ፡ እግዚአብሔር፡ትጸልይልን፡ዘንድ፡አትታክት፡አሉት።

9ሳሙኤልም፡አንድ፡የሚጠባ፡የበግ፡ጠቦት፡ወስዶ፡ለእግዚአብሔር፡ፈጽሞ፡የሚቃጠል፡መሥዋዕት፡ አድርጎ፡አቀረበው፤ሳሙኤልም፡ስለ፡እስራኤል፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ጮኸ፥እግዚአብሔርም፡ሰማው።

10ሳሙኤልም፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡ሲያሳርግ፡ፍልስጥኤማውያን፡ከእስራኤል፡ጋራ፡ሊዋጉ፡ ቀረቡ፤እግዚአብሔርም፡በዚያች፡ቀን፡በፍልስጥኤማውያን፡ላይ፡ታላቅ፡ነጐድጓድ፡ አንጐደጐደ፥አስደነገጣቸውም፡በእስራኤልም፡ፊት፡ድል፡ተመቱ።

11የእስራኤልም፡ሰዎች፡ከምጽጳ፡ወጡ፥ፍልስጥኤማውያንንም፡አሳደዱ፤በቤትካር፡ታችም፡እስኪደርሱ፡ድረስ፡ መቷቸው።

12ሳሙኤልም፡አንድ፡ድንጋይ፡ወስዶ፡በምጽጳና፡በሼን፡መካከል፡አኖረው፤ስሙንም፦እስከ፡አኹን፡ ድረስ፡እግዚአብሔር፡ረድቶናል፡ሲል፡አቤንዔዘር፡ብሎ፡ጠራው።

13ፍልስጥኤማውያንም፡ተዋረዱ፥ዳግመኛም፡ከዚያ፡ወዲያ፡ወደእስራኤል፡ድንበር፡አልወጡም፤በሳሙኤል፡ ዕድሜ፡ዅሉ፡የእግዚአብሔር፡እጅ፡በፍልስጥኤማውያን፡ላይ፡ነበረች።

14ፍልስጥኤማውያንም፡ከአስቀሎና፡ዠምሮ፡እስከ፡ጌት፡ድረስ፡ከእስራኤል፡የወሰዷቸው፡ከተማዎች፡ ለእስራኤል፡ተመለሱ፤እስራኤልም፡ድንበሩን፡ከፍልስጥኤማውያን፡እጅ፡አዳነ።በእስራኤልና፡በአሞራውያንም፡ መካከል፡ዕርቅ፡ነበረ።

15ሳሙኤልም፡በዕድሜው፡ዅሉ፡በእስራኤል፡ላይ፡ይፈርድ፡ነበር።

16በየዓመቱም፡ወደ፡ቤቴል፡ወደ፡ገልገላ፡ወደ፡ምጽጳም፡ይዞር፡ነበር፤በእነዚያም፡ስፍራዎች፡ዅሉ፡ በእስራኤል፡ላይ፡ይፈርድ፡ነበር።

17ቤቱም፡በዚያ፡ነበረና፡ወደ፡አርማቴም፡ይመለስ፡ነበር፤በዚያም፡በእስራኤል፡ላይ፡ይፈርድ፡ ነበር፥በዚያም፡ለእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡ሠራ።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source