1እስራኤልም፡ዅሉ፡ያነግሡት፡ዘንድ፡ወደ፡ሴኬም፡መጥተው፡ነበርና፥ሮብዓም፡ወደ፡ሴኬም፡ኼደ።
2የናባጥ፡ልጅ፡ኢዮርብዓምም፡ከንጉሡ፡ከሰሎሞን፡ፊት፡ሸሽቶ፡በግብጽ፡ይኖር፡ነበርና፥ይህን፡በሰማ፡ ጊዜ፡ኢዮርብዓም፡ከግብጽ፡ተመለሰ።
3ልከውም፡ጠሩት፤ኢዮርብዓምና፡እስራኤልም፡ዅሉ፡መጥተው፡ሮብዓምን፦
4አባትኽ፡ቀንበር፡አክብዶብን፡ነበር፤አኹንም፡አንተ፡ጽኑውን፡የአባትኽን፡አገዛዝ፥በላያችንም፡የጫነውን፡ የከበደውን፡ቀንበር፡አቅል፟ልን፥እኛም፡እንገዛልኻለን፡ብለው፡ተናገሩት።
5ርሱም፦ከሦስት፡ቀን፡በዃላ፡ወደ፡እኔ፡ተመለሱ፡አላቸው።ሕዝቡም፡ኼዱ።
6ንጉሡም፡ሮብዓም፦ለዚህ፡ሕዝብ፡እመልስለት፡ዘንድ፡የምትመክሩኝ፡ምንድር፡ነው፧ብሎ፡አባቱ፡ ሰሎሞን፡በሕይወት፡ሳለ፡በፊቱ፡ይቆሙ፡ከነበሩት፡ሽማግሌዎች፡ጋራ፡ተማከረ።
7እነርሱም፦ለዚህ፡ሕዝብ፡ቸርነት፡ብታደርግላቸው፥ደስም፡ብታሠኛቸው፥በገርነትም፡ ብትናገራቸው፥ለዘለዓለም፡ባሪያዎች፡ይኾኑልኻል፡ብለው፡ተናገሩት።
8ርሱ፡ግን፡ሽማግሌዎች፡የመከሩትን፡ነገር፡ትቶ፡ከርሱ፡ጋራ፡ካደጉትና፡በፊቱ፡ይቆሙ፡ከነበሩት፡ ብላቴናዎች፡ጋራ፡ተማከረ።
9ርሱም፦አባትኽ፡የጫነብንን፡ቀንበር፡አቅል፟ልን፡ለሚሉኝ፡ሕዝብ፡እመልስላቸው፡ዘንድ፡የምትመክሩኝ፡ ምንድር፡ነው፧አላቸው።
10ከርሱም፡ጋራ፡ያደጉት፡ብላቴናዎች፦አባትኽ፡ቀንበር፡አክብዶብን፡ነበር፥አንተ፡ግን፡አቅል፟ልን፡ ለሚሉኽ፡ሕዝብ፦ታናሺቱ፡ጣቴ፡ከአባቴ፡ወገብ፡ትወፍራለች፤
11አኹንም፡አባቴ፡ከባድ፡ቀንበር፡ጭኖባችኹ፡ነበር፥እኔ፡ግን፡በቀንበራችኹ፡ላይ፡እጨምራለኹ፤አባቴ፡ በዐለንጋ፡ገርፏችኹ፡ነበር፥እኔ፡ግን፡በጊንጥ፡እገርፋችዃለኹ፡በላቸው፡ብለው፡ተናገሩት።
12ንጉሡም፦በሦስተኛው፡ቀን፡ወደ፡እኔ፡ተመለሱ፡ብሎ፡እንደ፡ተናገረ፡ኢዮርብዓምና፡ሕዝቡ፡ዅሉ፡ በሦስተኛው፡ቀን፡ወደ፡ሮብዓም፡መጡ።
13ንጉሡም፡ጽኑ፡ምላሽ፡መለሰላቸው፤ንጉሡም፡ሮብዓም፡የሽማግሌዎቹን፡ምክር፡ትቶ፦
14አባቴ፡ቀንበር፡አክብዶባችኹ፡ነበር፥እኔ፡ግን፡እጨምርበታለኹ፤አባቴ፡በዐለንጋ፡ገርፏችኹ፡ነበር፥እኔ፡ ግን፡በጊንጥ፡እገርፋችዃለኹ፡ብሎ፡እንደ፡ብላቴናዎቹ፡ምክር፡ተናገራቸው።
15እግዚአብሔርም፡በሴሎናዊው፡በአኂያ፡አድርጎ፡ለናባጥ፡ልጅ፡ለኢዮርብዓም፡የተናገረውን፡ቃል፡ እንዲያጸና፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ተወስኖ፡ነበርና፥ንጉሡ፡ሕዝቡን፡አልሰማም።
16እስራኤልም፡ዅሉ፡ንጉሡ፡እንዳልሰማቸው፡ባዩ፡ጊዜ፡ሕዝቡ፦በዳዊት፡ዘንድ፡ምን፡ክፍል፡ አለን፧በእሴይም፡ልጅ፡ዘንድ፡ርስት፡የለንም፤እስራኤል፡ሆይ፥ወደ፡እየድንኳኖቻችኹ፡ተመለሱ፤ዳዊት፡ ሆይ፥አኹን፡ቤትኽን፡ተመልከት፡ብለው፡ለንጉሡ፡መለሱለት።እስራኤልም፡ዅሉ፡ወደ፡እየድንኳኖቻቸው፡ ኼዱ።
17በይሁዳ፡ከተማዎች፡በተቀመጡት፡በእስራኤል፡ልጆች፡ላይ፡ግን፡ሮብዓም፡ነገሠባቸው። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
18ንጉሡም፡ሮብዓም፡አስገባሪውን፡አዶራምን፡ሰደደ፤የእስራኤልም፡ልጆች፡በድንጋይ፡ ወገሩት፥ሞተም፤ንጉሡም፡ሮብዓም፡ፈጥኖ፡ወደ፡ሠረገላው፡ወጣ፡ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡ሸሸ።
19እስራኤልም፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡ከዳዊት፡ቤት፡ሸፈተ።