1የሳባም፡ንግሥት፡የሰሎሞንን፡ዝና፡በሰማች፡ጊዜ፡በግመሎች፡ላይ፡ሽቱና፡ብዙ፡ወርቅ፡የከበረም፡ዕንቍ፡ አስጭና፡ከታላቅ፡ጓዝ፡ጋራ፡ሰሎሞንን፡በኢየሩሳሌም፡በእንቆቅልሽ፡ትፈትነው፡ዘንድ፡መጣች፤ወደ፡ ሰሎሞንም፡በገባች፡ጊዜ፡በልቧ፡ያለውን፡ዅሉ፡አጫወተችው።
2ሰሎሞንም፡የጠየቀችውን፡ዅሉ፡ፈታላት፤ሰሎሞንም፡ያልፈታው፡ስውር፡ነገር፡አልነበረም።
3የሳባም፡ንግሥት፡የሰሎሞንን፡ጥበብ፥ሠርቶትም፡የነበረውን፡ቤት፥የማእዱንም፡መብል፥
4የብላቴናዎቹንም፡አቀማመጥ፥የሎሌዎቹንም፡አሠራር፡አለባበሳቸውንም፥ጠጅ፡አሳላፊዎቹንም፡ አለባበሳቸውንም፡በእግዚአብሔርም፡ቤት፡የሚያሳርገውን፡መሥዋዕት፡ባየች፡ጊዜ፡መንፈስ፡አልቀረላትም።
5ንጉሡንም፡አለችው፦ስለ፡ነገርኽና፡ስለ፡ጥበብኽ፡በአገሬ፡ሳለኹ፡የሰማኹት፡ዝና፡እውነት፡ነው።
6እኔ፡ግን፡መጥቼ፡በዐይኔ፡እስካየኹ፡ድረስ፡የነገሩኝን፡አላመንኹም፤እንሆ፥የጥበብኽን፡ታላቅነት፡ እኩሌታ፡አልነገሩኝም፤ከሰማኹት፡ዝና፡ትበልጣለኽ።
7በፊትኽ፡ዅልጊዜ፡የሚቆሙ፡ጥበብኽንም፡የሚሰሙ፡ሰዎችኽና፡እነዚህ፡ባሪያዎችኽ፡ምስጉኖች፡ናቸው።
8በአምላክኽ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ንጉሥ፡እንድትኾን፡በዙፋኑ፡ላይ፡ያስቀምጥኽ፡ዘንድ፡የወደደኽ፡ አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ቡሩክ፡ይኹን፤አምላክኽ፡እስራኤልን፡ለዘለዓለም፡ያጸናቸው፡ዘንድ፡ ወዷ፟ቸዋልና፥ስለዚህ፡ፍርድና፡ጽድቅ፡ታደርግ፡ዘንድ፡በላያቸው፡አነገሠኽ።
9ለንጉሡም፡መቶ፡ኻያ፡መክሊት፡ወርቅ፥እጅግም፡ብዙ፡ሽቱ፡የከበረም፡ዕንቍ፡ሰጠችው፤የሳባም፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ንግሥት፡ለንጉሡ፡ለሰሎሞን፡እንደ፡ሰጠችው፡ያለ፡ሽቱ፡ከቶ፡አልነበረም።
10ከኦፊርም፡ወርቅ፡ያመጡ፡የኪራም፡ባሪያዎችና፡የሰሎሞን፡ባሪያዎች፡የሰንደል፡ዕንጨትና፡የከበረ፡ዕንቍ፡ ደግሞ፡አመጡ።
11ንጉሡም፡ከሰንደሉ፡ዕንጨት፡ለእግዚአብሔር፡ቤትና፡ለንጉሡ፡ቤት፡ደርብ፥ለመዘምራኑም፡መሰንቆና፡ በገና፡አደረገ፤እንደዚህም፡ያለ፡በይሁዳ፡ምድር፡ከቶ፡አልታየም፡ነበር።
12የሳባም፡ንግሥት፡ወደ፡ንጉሡ፡ካመጣችው፡የሚበልጥ፥ንጉሡ፡ሰሎሞን፡የወደደችውን፡ዅሉ፡ከርሱም፡ የለመነችውን፡ዅሉ፡ሰጣት፤ርሷም፡ተመልሳ፡ከባሪያዎቿ፡ጋራ፡ወደ፡ምድሯ፡ኼደች።
13ነጋድራሶችና፡ነጋዴዎች፡ካመጡለት፡ሌላ፡በየዓመቱ፡ወደ፡ሰሎሞን፡የሚመጣ፡የወርቅ፡ሚዛን፡ስድስት፡ መቶ፡ስድሳ፡ስድስት፡መክሊት፡ወርቅ፡ነበረ።
14የዐረብም፡ነገሥታት፡ዅሉ፡የምድሩም፡ሹማምት፡ወርቅና፡ብር፡ወደ፡ሰሎሞን፡ያመጡ፡ነበር።
15ንጉሡም፡ሰሎሞን፡በጥፍጥፍ፡ወርቅ፡ኹለት፡መቶ፡አላባሽ፡አግሬ፡ጋሻ፡አሠራ፤በአንዱም፡አላባሽ፡ አግሬ፡ጋሻ፡ውስጥ፡የገባው፡ጥፍጥፍ፡ወርቅ፡ስድስት፡መቶ፡ሰቅል፡ነበረ።
16ከጥፍጥም፡ወርቅ፡ሦስት፡መቶ፡ጋሻ፡አሠራ፤በአንዱም፡ጋሻ፡የገባው፡ወርቅ፡ሦስት፡መቶ፡ሰቅል፡ ነበረ፤ንጉሡም፡የሊባኖስ፡ዱር፡በተባለው፡ቤት፡ውስጥ፡አኖራቸው።
17ንጉሡም፡ደግሞ፡ከዝኆን፡ጥርስ፡ታላቅ፡ዙፋን፡አሠራ፥በጥሩ፡ወርቅም፡ለበጠው።
18ከዙፋኑም፡ጋራ፡ተጋጥመው፡ወደ፡ዙፋኑም፡የሚያስኼዱ፡ስድስት፡ዕርከኖች፡ነበሩ፤የወርቅ፡ብርኵማም፡ ነበረ፤በዚህና፡በዚያም፡በመቀመጫው፤አጠገብ፡ኹለት፡የክንድ፡መደገፊያዎች፡ነበሩበት፥በመደገፊያዎችም፡ አጠገብ፡ኹለት፡አንበሳዎች፡ቆመው፡ነበር።
19በስድስቱም፡ዕርከኖች፡ላይ፡በዚህና፡በዚያ፡ዐሥራ፡ኹለት፡አንበሳዎች፡ቆመው፡ነበር፤በመንግሥታት፡ ዅሉ፡እንዲህ፡ያለ፡ሥራ፡አልተሠራም።
20ንጉሡም፡ሰሎሞን፡የሚጠጣበት፡ዕቃ፡ዅሉ፡የወርቅ፡ነበረ፥የሊባኖስ፡ዱር፡በተባለውም፡ቤቱ፡የነበረው፡ ዕቃ፡ዅሉ፡ጥሩ፡ወርቅ፡ነበረ፤በሰሎሞን፡ዘመን፡ብር፡ከቶ፡አይቈጠርም፡ነበር።
21ለንጉሡም፡ከኪራም፡ባሪያዎች፡ጋራ፡ወደ፡ተርሴስ፡የሚኼዱ፡መርከቦች፡ነበሩት፤በሦስት፡በሦስት፡ ዓመትም፡አንድ፡ጊዜ፡የተርሴስ፡መርከቦች፡ወርቅና፡ብር፡የዝኆንም፡ጥርስ፡ዝንጀሮና፡ዝጕርጕር፡ወፍም፡ ይዘው፡ይመጡ፡ነበር።
22ንጉሡም፡ሰሎሞን፡ከምድር፡ነገሥታት፡ዅሉ፡በባለጠግነትና፡በጥበብ፡በለጠ።
23የምድርም፡ነገሥታት፡ዅሉ፡እግዚአብሔር፡በልቡ፡ያኖረውን፡ጥበቡን፡ይሰሙ፡ዘንድ፡የሰሎሞንን፡ፊት፡ ሊያዩ፡ይመኙ፡ነበር።
24እያንዳንዱም፡ገጸ፡በረከቱን፥የወርቅንና፡የብርን፡ዕቃ፥ልብስንና፡የጦር፡ መሣሪያን፥ሽቱውንም፥ፈረሶችንና፡በቅሎዎችን፡እየያዘ፡በየዓመቱ፡ያመጣ፡ነበር።
25ሰሎሞንም፡ለፈረሶችና፡ለሠረገላዎች፡አራት፡ሺሕ፡ጋጥ፥ዐሥራ፡ኹለት፡ሺሕም፡ፈረሰኛዎች፡ ነበሩት፥በሠረገላዎችም፡ከተማዎች፥ከንጉሡም፡ጋራ፡በኢየሩሳሌም፡አኖራቸው።
26ከኤፍራጥስም፡ወንዝ፡ዠምሮ፡እስከፍልስጥኤም፡ምድርና፡እስከግብጽ፡ዳርቻ፡ድረስ፡ባሉ፡ነገሥታት፡ ዅሉ፡ላይ፡ነገሠ።
27ንጉሡም፡ብሩን፡በኢየሩሳሌም፡እንደ፡ድንጋይ፡እንዲበዛ፡አደረገው፤የዝግባውንም፡ዕንጨት፡ብዛት፡ በቈላ፡እንደሚበቅል፡ሾላ፡አደረገው።
28ለሰሎሞንም፡ፈረሶች፡ከግብጽና፡ከየአገሩ፡ዅሉ፡ያመጡለት፡ነበር።
29የቀረውም፡ፊተኛውና፡ዃለኛው፡የሰሎሞን፡ነገር፡በነቢዩ፡በናታን፡ታሪክ፥በሴሎናዊውም፡በኦሒያ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ትንቢት፥ስለ፡ናባጥም፡ልጅ፡ስለ፡ኢዮርብዓም፡ባየው፡በባለራእዩ፡በአዶ፡ራእይ፡የተጻፈ፡አይደለምን፧
30ሰሎሞንም፡በኢየሩሳሌም፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ላይ፡አርባ፡ዓመት፡ነገሠ።
31ሰሎሞንም፡ከአባቶቹ፡ጋራ፡አንቀላፋ፥በአባቱም፡በዳዊት፡ከተማ፡ተቀበረ፤ልጁም፡ሮብዓም፡በርሱ፡ፋንታ፡ ነገሠ።