1እንዲህም፡ኾነ፤ሰሎሞን፡የእግዚአብሔርን፡ቤትና፡የራሱን፡ቤት፡የሠራበት፡ኻያ፡ዓመት፡በተፈጸመ፡ጊዜ፥
2ኪራም፡ለሰሎሞን፡የሰጠውን፡ከተማዎች፡ሰሎሞን፡ሠራቸው፥የእስራኤልንም፡ልጆች፡አኖረባቸው።
3ሰሎሞንም፡ወደ፡ሐማትሱባ፡ኼደ፥አሸነፋትም።
4በምድረ፡በዳም፡ያለውን፡ተድሞርን፥በሐማትም፡የሠራቸውን፡የዕቃ፡ቤቱን፡ከተማዎች፡ዅሉ፡ሠራ።
5ደግሞም፡ቅጥርና፡መዝጊያ፡መወርወሪያም፡የነበራቸውን፡የተመሸጉትን፡ከተማዎች፡ላይኛውን፡ቤትሖሮን፡ ታችኛውንም፡ቤትሖሮን፡ሠራ።
6ባዕላትንም፥ለሰሎሞንም፡የነበሩትን፡የዕቃ፡ቤት፡ከተማዎች፡ዅሉ፥የሠረገላውንም፡ከተማዎች፡ ዅሉ፥የፈረሰኛዎችንም፡ከተማዎች፥በኢየሩሳሌምም፡በሊባኖስም፡በመንግሥቱም፡ምድር፡ዅሉ፡ሰሎሞን፡ይሠራ፡ ዘንድ፡የወደደውን፡ዅሉ፡ሠራ።
7ከኬጢያውያንም፡ከአሞራውያንም፡ከፌርዜያውያንም፡ከዔዊያውያንም፡ከኢያቡሳውያንም፡የቀሩትን፡ከእስራኤል፡ ወገን፡ያልኾኑትን፡ሕዝብ፡ዅሉ፥
8የእስራኤልም፡ልጆች፡ያላጠፏቸውን፥በዃላቸው፡በምድር፡ላይ፡የቀሩትን፡ልጆቻቸውን፡ሰሎሞን፡እስከ፡ ዛሬ፡ድረስ፡ገባሮች፡አድርጎ፡መለመላቸው።
9ሰሎሞንም፡ለሥራው፡ከእስራኤል፡ልጆች፡ማንንም፡ባሪያ፡አላደረገም፤እነርሱ፡ግን፡ ሰልፈኛዎች፥የሹማምቶችም፡አለቃዎች፥የሠረገላዎችና፡የፈረሰኛዎች፡ባልደራሶች፡ነበሩ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
10እነዚህም፡በሕዝቡ፡ላይ፡ሠልጥነው፡የነበሩ፡የንጉሡ፡የሰሎሞን፡ዐይነተኛዎች፡አለቃዎች፡ኹለት፡መቶ፡ ዐምሳ፡ነበሩ።
11ሰሎሞንም፦የእግዚአብሔር፡ታቦት፡የገባበት፡ስፍራ፡ቅዱስ፡ነውና፥ሚስቴ፡በእስራኤል፡ንጉሥ፡በዳዊት፡ ቤት፡አትቀመጥም፡ሲል፡የፈርዖንን፡ልጅ፡ከዳዊት፡ከተማ፡ወደሠራላት፡ቤት፡አወጣት።
12በዚያን፡ጊዜም፡ሰሎሞን፡በወለሉ፡ፊት፡በሠራው፡በእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡ላይ፡ለእግዚአብሔር፡ የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡አቀረበ።
13ሙሴም፡እንዳዘዘ፡እንደ፡ሥርዐታቸው፡በየቀኑ፡ዅሉ፥በየሰንበታቱም፥በየመባቻዎቹም፥በየተወሰኑትም፡ በዓላት፥በየዓመቱ፡ሦስት፡ጊዜ፡በየቂጣው፡በዓልና፡በየሰባቱ፡ሱባዔ፡በዓል፡በየዳሱም፡በዓል፡ቍርባን፡ያቀርቡ፡ ነበር።
14የእግዚአብሔርም፡ሰው፡ዳዊት፡እንዲህ፡አዞ፟፡ነበርና፥ካህናቱን፡እንደ፡አባቱ፡እንደ፡ዳዊት፡ሥርዐት፡ በያገልግሎታቸው፡ሰሞን፡ከፈላቸው፤ሌዋውያንም፡እንደ፡ሥርዐታቸው፡ያመሰግኑ፡ዘንድ፥በካህናቱም፡ፊት፡ ያገለግሉ፡ዘንድ፡በየሰሞናቸው፡ከፈላቸው፤በረኛዎቹንም፡ደግሞ፡በየበሩ፡ዅሉ፡በየሰሞናቸው፡ከፈላቸው።
15እነርሱም፡ንጉሡ፡ስለ፡ነገሩ፡ዅሉና፡ስለ፡መዝገቡ፡ካህናቱንና፡ሌዋውያኑን፡ያዘዘውን፡ነገር፡ዅሉ፡ አልተላለፉም።
16የእግዚአብሔርም፡ቤት፡መሠረት፡ከተጣለ፡ዠምሮ፡እስከተጨረሰ፡ድረስ፡የሰሎሞን፡ሥራ፡ዅሉ፡ የተዘጋጀ፡ነበረ።የእግዚአብሔርም፡ቤት፡ተፈጸመ።
17ሰሎሞንም፡የዚያን፡ጊዜ፡በኤዶምያስ፡ምድር፡በባሕር፡ዳር፡ወዳሉ፡ወደ፡ዔጽዮንጋብርና፡ወደ፡ኤሎት፡ ኼደ።
18ኪራምም፡መርከቦችንና፡የባሕርን፡ነገር፡የሚያውቁትን፡መርከበኛዎች፡በባሪያዎቹ፡እጅ፡ ሰደደለት፤እነርሱም፡ከሰሎሞን፡ባሪያዎች፡ጋራ፡ወደ፡ኦፊር፡መጡ፥ከዚያም፡አራት፡መቶ፡ዐምሳ፡መክሊት፡ ወርቅ፡ወስደው፡ወደ፡ንጉሡ፡ወደ፡ሰሎሞን፡አመጡ።