1እንዲህም፡ኾነ፤የሮብዓም፡መንግሥት፡በጸናች፡ጊዜ፥ርሱም፡በበረታ፡ጊዜ፥ርሱና፡እስራኤል፡ዅሉ፡ የእግዚአብሔርን፡ሕግ፡ተዉ።
2እግዚአብሔርን፡በድለዋልና፥ሮብዓም፡በነገሠ፡በዐምስተኛው፡ዓመት፡የግብጽ፡ንጉሥ፡ሺሻቅ፡ሺሕ፡ ኹለት፡መቶ፡ሠረገላዎችና፡ስድሳ፡ሺሕ፡ፈረሰኛዎች፡ይዞ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ወጣ።
3ከርሱም፡ጋራ፡ከግብጽ፡ለመጣው፡ሕዝብ፡ቍጥር፡አልነበረውም፤እነርሱም፡የልብያ፡ ሰዎች፥ሱካውያን፥የኢትዮጵያ፡ሰዎችም፡ነበሩ።
4ለይሁዳም፡የነበሩትን፡ምሽጎች፡ከተማዎች፡ወሰደ፥ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡መጣ።
5ነቢዩም፡ሸማያ፡ወደ፡ሮብዓምና፡ከሺሻቅ፡ሸሽተው፡በኢየሩሳሌም፡ወደተሰበሰቡባት፡ወደይሁዳ፡መሳፍንት፡ መጥቶ፡እንዲህ፡አላቸው፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እናንተ፡ተዋችኹኝ፤ስለዚህ፥እኔ፡ደግሞ፡ በሺሻቅ፡እጅ፡ተውዃችኹ።
6የእስራኤልም፡መሳፍንትና፡ንጉሡ።እግዚአብሔር፡ጻድቅ፡ነው፡ብለው፡ሰውነታቸውን፡አዋረዱ።
7እግዚአብሔርም፡ሰውነታቸውን፡እንዳዋረዱ፡ባየ፡ጊዜ፡የእግዚአብሔር፡ቃል።ሰውነታቸውን፡ አዋርደዋል፤አላጠፋቸውም፤ከጥቂት፡ቀንም፡በዃላ፡አድናቸዋለኹ፥ቍጣዬም፡በሺሻቅ፡እጅ፡በኢየሩሳሌም፡ ላይ፡አይፈስ፟ም፤
8ነገር፡ግን፥ለእኔ፡መገዛትንና፡ለምድር፡ነገሥታት፡መገዛትን፡ያውቁ፡ዘንድ፡ይገዙለታል፡ሲል፡ወደ፡ ሸማያ፡መጣ።
9የግብጽ፡ንጉሥ፡ሺሻቅም፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡መጣ፥የእግዚአብሔርንም፡ቤት፡መዛግብትና፡የንጉሡን፡ ቤት፡መዛግብት፡ወሰደ፤ዅሉንም፡ወሰደ፤ደግሞም፡ሰሎሞን፡የሠራቸውን፡የወርቁን፡ጋሻዎች፡ወሰደ።
10ንጉሡም፡ሮብዓም፡በእነርሱ፡ፋንታ፡የናስ፡ጋሻዎችን፡ሠራ፥የንጉሡንም፡ቤት፡ደጅ፡በሚጠብቁ፡ በዘበኛዎች፡አለቃ፡እጅ፡አኖራቸው።
11ንጉሡም፡ወደእግዚአብሔር፡ቤት፡በገባ፡ቍጥር፡ዘበኛዎች፡መጥተው፡ይሸከሟቸው፡ነበር፥መልሰውም፡ በዘበኛዎች፡ቤት፡ውስጥ፡ያኖሯቸው፡ነበር።
12ሰውነቱንም፡ባዋረደ፡ጊዜ፡የእግዚአብሔር፡ቍጣ፡ፈጽሞ፡እንዳያጠፋው፡ከርሱ፡ዘንድ፡ ተመለሰ፤በይሁዳም፡ደግሞ፡መልካም፡ነገር፡ተገኘ።
13ንጉሡም፡ሮብዓም፡በኢየሩሳሌም፡በረታ፡ንጉሥም፡ኾነ፤ሮብዓምም፡በነገሠ፡ጊዜ፡የአርባ፡አንድ፡ዓመት፡ ጕልማሳ፡ነበረ፤እግዚአብሔርም፡ስሙን፡ያኖርባት፡ዘንድ፡ከእስራኤል፡አገር፡ዅሉ፡በመረጣት፡ከተማ፡ በኢየሩሳሌም፡ዐሥራ፡ሰባት፡ዓመት፡ነገሠ፤እናቱም፡የዐሞን፡ሴት፡ናዕማ፡ነበረች።
14እግዚአብሔርንም፡ይሻ፡ዘንድ፡ልቡን፡አላዘጋጀም፡ነበርና፥ክፉ፡ነገር፡አደረገ።
15የሮብዓምም፡የፊተኛውና፡የዃለኛው፡ነገር፡በነቢዩ፡ሸማያና፡በባለራእዩ፡በአዶ፡የትውልድ፡ታሪክ፡ መጽሐፍ፡የተጻፈ፡አይደለምን፧በሮብዓምና፡በኢዮርብዓም፡መካከልም፡በዘመናቸው፡ዅሉ፡ሰልፍ፡ነበረ።
16ሮብዓምም፡ከአባቶቹ፡ጋራ፡አንቀላፋ፥በዳዊትም፡ከተማ፡ተቀበረ፤ልጁም፡አብያ፡በርሱ፡ፋንታ፡ነገሠ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org