1የእግዚአብሔርም፡መንፈስ፡በዖዴድ፡ልጅ፡በዐዛርያስ፡ላይ፡ኾነ፤
2አሣንም፡ሊገናኘው፡ወጣ፥እንዲህም፡አለው፦አሣ፡ይሁዳና፡ብንያም፡ዅሉ፡ሆይ፥ስሙኝ፤እናንተ፡ ከእግዚአብሔር፡ጋራ፡ስትኾኑ፡ርሱ፡ከእናንተ፡ጋራ፡ነው፤ብትፈልጉትም፡ይገኝላችዃል፤ብትተዉት፡ግን፡ ይተዋችዃል።
3እስራኤልም፡ብዙ፡ዘመን፡ያለእውነተኛ፡አምላክ፥ያለአስተማሪም፡ካህን፥ያለሕግም፡ይኖሩ፡ነበር።
4በመከራቸውም፡ወደእስራኤል፡አምላክ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ተመልሰው፡በፈለጉት፡ጊዜ፡አገኙት።
5በዚያም፡ዘመን፡ለሚወጣውና፡ለሚገባው፡ሰላም፡አልነበረም፥በምድርም፡በሚኖሩት፡ዅሉ፡ላይ፡ታላቅ፡ ድንጋጤ፡ነበረ።
6እግዚአብሔር፡በመከራው፡ዅሉ፡ያስጨንቃቸው፡ነበርና፥ወገን፡ከወገን፡ጋራ፥ከተማም፡ከከተማ፡ጋራ፡ ይዋጋ፡ነበር።
7እናንተ፡ግን፡ለሥራችኹ፡ብድራት፡ይኾንላችዃልና፥በርቱ፥እጃችኹም፡አይላላ።
8አሣም፡ይህን፡ቃልና፡የነቢዩን፡የዖዴድን፡ትንቢት፡በሰማ፡ጊዜ፡ልቡ፡ጸና፥ከይሁዳና፡ከቢንያምም፡አገር፡ ዅሉ፡በተራራማውም፡በኤፍሬም፡አገር፡ከያዛቸው፡ከተማዎች፡ጸያፉን፡ነገር፡አስወገደ፤በእግዚአብሔርም፡ቤት፡ ፊት፡የነበረውን፡የእግዚአብሔርን፡መሠዊያ፡ዐደሰ።
9አምላኩም፡እግዚአብሔር፡ከርሱ፡ጋራ፡እንደ፡ኾነ፡ባዩ፡ጊዜ፡ከእስራኤል፡ዘንድ፡ብዙ፡ሰዎች፡ወደ፡ርሱ፡ ተጠግተው፡ነበርና፥ርሱ፡ይሁዳንና፡ብንያምን፡ዅሉ፥ከኤፍሬምና፡ከምናሴም፡ከስምዖንም፡መጥተው፡ከነርሱ፡ ጋራ፡የተቀመጡትን፡ሰበሰበ።
10አሣም፡በነገሠ፡በዐሥራ፡ዐምስተኛው፡ዓመት፡በሦስተኛው፡ወር፡በኢየሩሳሌም፡ተሰበሰቡ።
11በዚያም፡ቀን፡ካመጡት፡ምርኮ፡ሰባት፡መቶ፡በሬዎችና፡ሰባት፡ሺሕ፡በጎች፡ለእግዚአብሔር፡ሠዉ።
12በፍጹም፡ልባቸውና፡በፍጹም፡ነፍሳቸው፡የአባቶቻቸውን፡አምላክ፡እግዚአብሔርን፡ይሹ፡ዘንድ፡ቃል፡ ኪዳን፡አደረጉ፤
13የእስራኤልንም፡አምላክ፡እግዚአብሔርን፡የማይፈልግ፥ታናሽ፡ወይም፡ታላቅ፥ወንድ፡ወይም፡ሴት፡ ቢኾን፥ይገደል፡ዘንድ፡ማሉ።
14ለእግዚአብሔርም፡በታላቅ፡ድምፅና፡በእልልታ፥በእንቢልታና፡በቀንደ፡መለከት፡ማሉ።
15በፍጹምም፡ልባቸው፡ምለዋልና፥በፍጹምም፡ኅሊናቸው፡ፈልገውታልና፥ርሱም፡ተገኝቶላቸዋልና፥ይሁዳ፡ ዅሉ፡በመሐላው፡ደስ፡አላቸው፤እግዚአብሔርም፡በዙሪያቸው፡ዕረፍት፡ሰጣቸው።
16ንጉሡም፡አሣ፡እናቱን፡መዓካን፡በማምለኪያ፡ዐጸድ፡ጣዖት፡ስላደረገች፡ከእቴጌነቷ፡አዋረዳት፤አሣም፡ ምስሏን፡ቈርጦ፡ቀጠቀጠው፥በቄድሮንም፡ወንዝ፡አጠገብ፡አቃጠለው።
17በኰረብታ፡ላይ፡የነበሩትን፡መስገጃዎች፡ግን፡ከእስራኤል፡አላራቀም፤ይኹን፡እንጂ፡የአሣ፡ልብ፡ በዘመኑ፡ዅሉ፡ፍጹም፡ነበረ።
18አባቱም፡የቀደሰውን፥ርሱም፡የቀደሰውን፡ወርቁንና፡ብሩን፥ልዩ፡ልዩውንም፡ዕቃ፡ወደእግዚአብሔር፡ቤት፡ አገባ።
19አሣም፡እስከነገሠበት፡እስከ፡ሠላሳ፡ዐምስተኛው፡ዓመት፡ድረስ፡ሰልፍ፡አልነበረም። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org