1አሣ፡በነገሠ፡በሠላሳ፡ስድስተኛው፡ዓመት፡የእስራኤል፡ንጉሥ፡ባኦስ፡በይሁዳ፡ላይ፡ወጣ፥ወደይሁዳም፡ ንጉሥ፡ወደ፡አሣ፡ማንም፡መውጣትና፡መግባት፡እንዳይችል፡ራማን፡ሠራ።
2አሣም፡ከእግዚአብሔር፡ቤትና፡ከንጉሡ፡ቤት፡መዝገብ፡ብርና፡ወርቅ፡ወስዶ፦
3በአባቴና፡በአባትኽ፡መካከል፡እንደ፡ነበረው፡ቃል፡ኪዳን፡በእኔና፡ባንተ፡መካከል፡ይኾናል፤እንሆ፥ብርና፡ ወርቅ፡ሰድጄልኻለኹ፤ርሱ፡ከእኔ፡ዘንድ፡እንዲርቅ፡ኼደኽ፡ከእስራኤል፡ንጉሥ፡ከባኦስ፡ጋራ፡ያለኽን፡ቃል፡ ኪዳን፡አፍርስ፡ብሎ፡በደማስቆ፡ወደተቀመጠው፡ወደሶርያ፡ንጉሥ፡ወደ፡ወልደ፡አዴር፡ሰደደ።
4ወልደ፡አዴር፡ንጉሡን፡አሣን፡ዕሺ፡አለው፥የሰራዊቱም፡አለቃዎች፡በእስራኤል፡ከተማዎች፡ላይ፡ ሰደደ፤እነርሱም፡ዒዮንንና፡ዳንን፡አቤልማይምንና፡የንፍታሌምን፡የዕቃ፡ቤት፡ከተማዎች፡ዅሉ፡መቱ።
5ባኦስም፡በሰማ፡ጊዜ፡ራማን፡መሥራት፡ተወ፥ሥራውንም፡አቋረጠ።
6ንጉሡም፡አሣ፡የይሁዳን፡ሰዎች፡ዅሉ፡ሰበሰበ፤ባኦስ፡ይሠራበት፡የነበረውን፡የራማን፡ድንጋይና፡ዕንጨት፡ አስወገዱ፥ርሱም፡ጌባንና፡ምጽጳን፡ሠራበት።
7በዚያን፡ጊዜም፡ባለራእዩ፡ዐናኒ፡ወደይሁዳ፡ንጉሥ፡ወደ፡አሣ፡መጥቶ፡እንዲህ፡አለው፦በሶርያ፡ንጉሥ፡ ታምነኻልና፥በአምላክኽም፡በእግዚአብሔር፡አልታመንኽምና፡ስለዚህ፡የሶርያ፡ንጉሥ፡ጭፍራ፡ከእጅኽ፡ አምልጧል።
8ኢትዮጵያውያንና፡የልብያ፡ሰዎች፡እጅግ፡ብዙ፡ሠረገላዎችና፡ፈረሰኛዎች፡የነበሯቸው፡እጅግ፡ታላቅ፡ ጭፍራ፡አልነበሩምን፧በእግዚአብሔር፡ስለ፡ታመንኽ፡በእጅኽ፡አሳልፎ፡ሰጣቸው፥
9እግዚአብሔር፥ልቡ፡በርሱ፡ዘንድ፡ፍጹም፡የኾነውን፡ያጸና፡ዘንድ፥ዐይኖቹ፡በምድር፡ዅሉ፡ ይመለከታሉና፦አኹንም፡ስንፍና፡አድርገኻል።ስለዚህም፡ከዛሬ፡ዠምሮ፡ሰልፍ፡ይኾንብኻል።
10አሣም፡በባለራእዩ፡ላይ፡ተቈጣ፤ስለዚህም፡ነገር፡ተቈጥቷልና፥በግዞት፡አኖረው፤በዚያን፡ጊዜም፡አሣ፡ ከሕዝቡ፡ዐያሌ፡ሰዎችን፡አስጨነቀ።
11የአሣም፡የፊተኛውና፡የዃለኛው፡ነገር፥እንሆ፥በይሁዳና፡በእስራኤል፡ነገሥታት፡መጽሐፍ፡ተጽፏል።
12በነገሠም፡በሠላሳ፡ዘጠነኛው፡ዓመት፡አሣ፡እግሩን፡ታመመ፤ደዌውም፡ጸናበት፤ነገር፡ግን፥በታመመ፡ ጊዜ፡ባለመድኀኒቶችን፡እንጂ፡እግዚአብሔርን፡አልፈለገም።
13አሣም፡ከአባቶቹ፡ጋራ፡አንቀላፋ፥በነገሠም፡በአርባ፡አንደኛው፡ዓመት፡ሞተ።
14ለርሱም፡ለራሱ፡በሠራው፡መቃብር፡በዳዊት፡ከተማ፡ቀበሩት፤በቀማሚ፡ብልኀት፡የተሰናዳ፡ልዩ፡ልዩ፡ መልካም፡ሽቱ፡በተሞላ፡ዐልጋ፡ላይም፡አኖሩት፤እጅግም፡ታላቅ፡የኾነ፡የመቃብር፡ወግ፡አደረጉለት።