Skip to content
← 2 Chronicles

Chapter 18 · Amharic

2 Chronicles

1ለኢዮሳፍጥም፡ብዙ፡ብልጥግናና፡ክብር፡ነበረው፤ለአክአብም፡ጋብቻ፡ኾነ።

2ከጥቂት፡ዓመት፡በዃላም፡ወደ፡አክአብ፡ወደ፡ሰማርያ፡ወረደ።አክአብም፡ለርሱና፡ከርሱ፡ጋራ፡ለነበሩት፡ ሕዝብ፡ብዙ፡በጎችንና፡በሬዎችን፡ዐረደ፥ከርሱም፡ጋራ፡ወደ፡ሬማት፡ዘገለዓድ፡ይኼድ፡ዘንድ፡አባበለው።

3የእስራኤልም፡ንጉሥ፡አክአብ፡የይሁዳን፡ንጉሥ፡ኢዮሳፍጥን፦ከእኔ፡ጋራ፡ወደ፡ሬማት፡ዘገለዓድ፡ ትኼዳለኽን፧አለው።ርሱም፡እኔ፡እንደ፡አንተ፡ነኝ፥ሕዝቤም፡እንደ፡ሕዝብኽ፡ናቸው፤በሰልፍም፡ከአንተ፡ ጋራ፡እንኾናለን፡ብሎ፡መለሰለት።

4ኢዮሳፍጥም፡የእስራኤልን፡ንጉሥ፦የእግዚአብሔርን፡ቃል፡አስቀድመኽ፡ትጠይቅ፡ዘንድ፡እለምንኻለኹ፡ አለው።

5የእስራኤልም፡ንጉሥ፡ነቢያቱን፡አራት፡መቶ፡ሰዎች፡ሰብስቦ፦ወደ፡ሬማት፡ዘገለዓድ፡ለሰልፍ፡ ልኺድን፧ወይስ፡ልቅር፧አላቸው።እነርሱም፦እግዚአብሔር፡በንጉሡ፡እጅ፡አሳልፎ፡ይሰጣታልና፥ውጣ፡ አሉት። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

6ኢዮሳፍጥ፡ግን፦እንጠይቀው፡ዘንድ፡የእግዚአብሔርን፡ነቢይ፡የኾነ፡ሌላ፡ሰው፡በዚህ፡አይገኝምን፧አለ።

7የእስራኤልም፡ንጉሥ፡ኢዮሳፍጥን፦እግዚአብሔርን፡የምንጠይቅበት፡አንድ፡ሰው፡አለ፤ነገር፡ግን፥ዅል፡ ጊዜ፡ክፉ፡እንጂ፡ከቶ፡መልካም፡ትንቢት፡አይነግርልኝምና፡እጠላዋለኹ፤ርሱም፡የይምላ፡ልጅ፡ሚክያስ፡ነው፡ አለው።ኢዮሳፍጥም፦ንጉሥ፡እንዲህ፡አይበል፡አለው።

8የእስራኤልም፡ንጉሥ፡አንድ፡ጃን፡ደረባ፡ጠርቶ፦የይምላን፡ልጅ፡ሚክያስን፡ፈጥነኽ፡አምጣው፡አለው።

9የእስራኤል፡ንጉሥና፡የይሁዳ፡ንጉሥ፡ኢዮሳፍጥ፡ልብሰ፡መንግሥት፡ለብሰው፡በሰማርያ፡በር፡መግቢያ፡ አጠገብ፡በአደባባይ፡በዙፋኖቻቸው፡ላይ፡ተቀምጠው፡ነበር፤ነቢያትም፡ዅሉ፡በፊታቸው፡ትንቢት፡ይናገሩ፡ ነበር።

10የክንዓና፡ልጅ፡ሰዴቅያስም፡የብረት፡ቀንዶች፡ሠርቶ፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ሶርያውያንን፡ እስኪጠፉ፡ድረስ፡በእነዚህ፡ትወጋለኽ፡አለ።

11ነቢያትም፡ዅሉ፦እግዚአብሔር፡በንጉሡ፡እጅ፡አሳልፎ፡ይሰጣታልና፥ወደ፡ሬማት፡ዘገለዓድ፡ኺድና፡ ተከናወን፡እያሉ፡እንዲሁ፡ትንቢት፡ይናገሩ፡ነበር።

12ሚክያስንም፡ሊጠራ፡የኼደ፡መልእክተኛ፦እንሆ፥ነቢያት፡ባንድ፡አፍ፡ኾነው፡ለንጉሡ፡መልካም፡ ይናገራሉ፤ቃልኽም፡እንደ፡ቃላቸው፡እንዲኾን፡መልካም፡እንድትናገር፡እለምንኻለኹ፡አለው።

13ሚክያስም፦ሕያው፡እግዚአብሔርን! አምላኬ፡የሚለውን፡ርሱን፡እናገራለኹ፡አለ።

14ወደ፡ንጉሡም፡በመጣ፡ጊዜ፡ንጉሡ፦ሚክያስ፡ሆይ፥ወደ፡ሬማት፡ዘገለዓድ፡ለሰልፍ፡ እንኺድን፧ወይስ፡እንቅር፧አለው።ርሱም፦ውጣ፥ተከናወን፤በእጅኽም፡ዐልፈው፡ይሰጣሉ፡አለ።

15ንጉሡም፦በእግዚአብሔር፡ስም፡ከእውነት፡በቀር፡እንዳትነግረኝ፡ስንት፡ጊዜ፡አምልኻለኹ፧አለው።

16ርሱም፦እስራኤል፡ዅሉ፡ጠባቂ፡እንደሌላቸው፡በጎች፡በተራራዎች፡ላይ፡ተበትነው፡ አየኹ፤እግዚአብሔርም፦ለእነዚህ፡ጌታ፡የላቸውም፥እያንዳንዱም፡በሰላም፡ወደ፡ቤቱ፡ይመለስ፡አለ፡ብሎ፡ ተናገረ።

17የእስራኤልም፡ንጉሥ፡ኢዮሳፍጥን፦ክፉ፡እንጂ፡መልካም፡ትንቢት፡አይናገርልኝም፡ አላልኹኽምን፧አለው።

18ሚክያስም፡አለ፦እንግዲህ፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ስሙ፤እግዚአብሔር፡በዙፋኑ፡ተቀምጦ፥የሰማይም፡ ሰራዊት፡ዅሉ፡በቀኙና፡በግራው፡ቆመው፡አየኹ።

19እግዚአብሔርም፦ወጥቶ፡በሬማት፡ዘገለዓድ፡ይወድቅ፡ዘንድ፡የእስራኤልን፡ንጉሥ፡አክአብን፡የሚያታልል፡ ማን፡ነው፧አለ።አንዱም፡እንደዚህ፥ሌላውም፡እንደዚያ፡ያለ፡ነገር፡ተናገረ።

20መንፈስም፡መጣ፥በእግዚአብሔርም፡ፊት፡ቆሞ፦እኔ፡አታልለዋለኹ፡ አለ።እግዚአብሔርም፦በምን፧አለው።

21ርሱም፦ወጥቼ፡በነቢያቱ፡ዅሉ፡አፍ፡ሐሰተኛ፡መንፈስ፡እኾናለኹ፡ አለ።እግዚአብሔርም፦ታታልለዋለኽ፤ይቀናኻል፤ውጣ፥እንዲህም፡አድርግ፡አለ።

22አኹንም፥እንሆ፥እግዚአብሔር፡በእነዚህ፡በነቢያትኽ፡አፍ፡ሐሰተኛ፡መንፈስን፡ አድርጓል፤እግዚአብሔርም፡ባንተ፡ላይ፡ክፉ፡ተናግሮብኻል።

23የክንዓናም፡ልጅ፡ሴዴቅያስ፡ቀረበ፥ሚክያስንም፡በጥፊ፡መታውና፦የእግዚአብሔር፡መንፈስ፡ከአንተ፡ ጋራ፡ይናገር፡ዘንድ፡በምን፡መንገድ፡ከእኔ፡ዐለፈ፧አለ።

24ሚክያስም፦እንሆ፥በዚያ፡ቀን፡ልትሸሸግ፡ወደ፡ዕልፍኝኽ፡ስትኼድ፡ታያለኽ፡አለ።

25የእስራኤልም፡ንጉሥ።ሚክያስን፡ውሰዱ፥ወደከተማዪቱም፡አለቃ፡ወደ፡ዐሞን፥ወደንጉሡም፡ልጅ፡ወደ፡ ኢዮአስ፡መልሳችኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

26ንጉሡ፡እንዲህ፡ይላል፦በደኅና፡እስክመለስ፡ድረስ፡ይህን፡ሰው፡በግዞት፡አኑሩት፥የመከራም፡እንጀራ፡ መግቡት፥የመከራም፡ውሃ፡አጠጡት፡በሉ፡አለ።

27ሚክያስም፦በደኅና፡ብትመለስ፡እግዚአብሔር፡በእኔ፡የተናገረ፡አይደለም፡አለ።ደግሞም፦እናንተ፡ ሕዝብ፡ዅሉ፥ስሙኝ፡አለ።

28የእስራኤል፡ንጉሥና፡የይሁዳ፡ንጉሥ፡ኢዮሳፍጥ፡ወደ፡ሬማት፡ዘገለዓድ፡ወጡ።

29የእስራኤል፡ንጉሥም፡ኢዮሳፍጥን፦ልብሴን፡ለውጬ፡ወደ፡ሰልፍ፡እገባለኹ፤አንተ፡ግን፡ልብስኽን፡ ልበስ፡አለው።የእስራኤልም፡ንጉሥ፡ልብሱን፡ለወጠ፥ወደ፡ሰልፍም፡ገቡ።

30የሶርያም፡ንጉሥ፡የሠረገላዎቹን፡አለቃዎች፦ከእስራኤል፡ንጉሥ፡በቀር፡ትንሽ፡ቢኾን፡ወይም፡ትልቅ፡ ከማናቸውም፡ጋራ፡አትጋጠሙ፡ብሎ፡አዞ፟፡ነበር።

31የሠረገላዎችም፡አለቃዎች፡ኢዮሳፍጥን፡ባዩ፡ጊዜ፦የእስራኤል፡ንጉሥ፡ነው፡አሉ፥ሊጋጠሙትም፡ ከበቡት፤ኢዮሳፍጥ፡ግን፡ጮኸ፥እግዚአብሔርም፡ረዳው፥አምላኩም፡ከርሱ፡መለሳቸው።

32የሠረገላዎቹም፡አለቃዎች፡የእስራኤል፡ንጉሥ፡እንዳልኾነ፡ባዩ፡ጊዜ፡ርሱን፡ከማሳደድ፡ተመለሱ።

33አንድ፡ሰውም፡ቀስቱን፡በድንገት፡ገትሮ፡የእስራኤልን፡ንጉሥ፡በጥሩሩ፡መጋጠሚያ፡በኩል፡ሳምባውን፡ ወጋው።ሠረገላኛውንም፦ተወግቻለኹና፡እጅኽን፡ግታ፥ከሰልፍም፡ውስጥ፡አውጣኝ፡አለው።

34በዚያም፡ቀን፡ሰልፍ፡በረታ፤የእስራኤልም፡ንጉሥ፡በሶርያውያን፡ፊት፡እስከ፡ማታ፡ድረስ፡በሠረገላው፡ ላይ፡ራሱን፡ይደግፍ፡ነበር፤ፀሓይም፡በገባ፡ጊዜ፡ሞተ።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source