1ሰሎሞንም፡ለእግዚአብሔር፡ስም፡ቤት፥ለመንግሥቱም፡ቤት፡ይሠራ፡ዘንድ፡ዐሰበ።
2ሰሎሞንም፡የሚሸከሙትን፡ሰባ፡ሺሕ፥ከተራራዎችም፡የሚጠርቡትን፡ሰማንያ፡ሺሕ፥በእነርሱም፡ላይ፡ የተሾሙትን፡ሦስት፡ሺሕ፡ስድስት፡መቶ፡ሰዎች፡ቈጠረ።
3ሰሎሞንም፡እንዲህ፡ሲል፡ወደጢሮስ፡ንጉሥ፡ወደ፡ኪራም፡ላከ፦ከአባቴ፡ከዳዊት፡ጋራ፡ እንዳደረግኽ፥የሚቀመጥበትንም፡ቤት፡ይሠራ፡ዘንድ፡የዝግባ፡ዕንጨት፡እንደ፡ሰደድኽለት፥እንዲሁ፡ለእኔ፡ አድርግ።
4እንሆ፥ለእስራኤል፡ለዘለዓለም፡እንደ፡ታዘዘው፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡የጣፋጩን፡ሽቱ፡ለማጠን፥የገጹንም፡ ኅብስት፡ለማኖር፥የሚቃጠለውንም፡መሥዋዕት፡በጧትና፡በማታ፡በሰንበታቱም፡በመባቻዎቹም፡በአምላካችንም፡ በእግዚአብሔር፡በዓላት፡ለማቅረብ፡ለአምላኬ፡ለእግዚአብሔር፡ስም፡ቤት፡እሠራና፡እቀድስ፡ዘንድ፡ዐሰብኹ።
5አምላካችንም፡ከአማልክት፡ዅሉ፡በላይ፡ታላቅ፡ነውና፥የምሠራው፡ቤት፡ታላቅ፡ነው።
6ነገር፡ግን፥ሰማይና፡ከሰማያት፡በላይ፡ያለ፡ሰማይ፡ይይዘው፡ዘንድ፡አይችልምና፡ለርሱ፡ቤት፡ይሠራ፡ ዘንድ፡ማን፡ይችላል፧በፊቱ፡ዕጣን፡ከማጠን፡በቀር፡ቤት፡እሠራለት፡ዘንድ፡እኔ፡ማን፡ነኝ፧
7አኹንም፡አባቴ፡ዳዊት፡ካዘጋጃቸው፡በእኔ፡ዘንድ፡በይሁዳና፡በኢየሩሳሌም፡ካሉት፡ብልኀተኛዎች፡ጋራ፡ የሚኾን፥ወርቁንና፡ብሩን፥ናሱንና፡ብረቱን፥ሐምራዊውንና፡ቀዩን፡ሰማያዊውንም፡ግምጃ፡የሚሠራ፥ቅርጽንም፡ የሚያውቅ፡ብልኀተኛ፡ሰው፡ላክልኝ።
8ደግሞም፡ባሪያዎችኽ፡ከሊባኖስ፡ዕንጨት፡መቍረጥ፡እንዲያውቁ፡እኔ፡ዐውቃለኹና፡ከሊባኖስ፡የዝግባና፡ የጥድ፡የሰንደልም፡ዕንጨት፡ስደድልኝ።
9የምሠራውም፡ቤት፡እጅግ፡ታላቅና፡ድንቅ፡ይኾናልና፥ብዙ፡ዕንጨት፡ያዘጋጁልኝ፡ ዘንድ፥እንሆ፥ባሪያዎቼ፡ከባሪያዎችኽ፡ጋራ፡ይኾናሉ።
10እንሆም፥ዕንጨቱን፡ለሚቈርጡ፡ለባሪያዎችኽ፡ኻያ፡ሺሕ፡የቆሮስ፡መስፈሪያ፡የተበጠረ፡ስንዴ፥ኻያ፡ ሺሕም፡የቆሮስ፡መስፈሪያ፡ገብስ፥ኻያ፡ሺሕም፡የባዶስ፡መስፈሪያ፡የወይን፡ጠጅ፥ኻያ፡ሺሕም፡የባዶስ፡ መስፈሪያ፡ዘይት፡እሰጣለኹ።
11የጢሮስ፡ንጉሥም፡ኪራም፦እግዚአብሔር፡ሕዝቡን፡ወዷ፟ልና፥በላያቸው፡አነገሠኽ፡ብሎ፡ለሰሎሞን፡ መልእክት፡ላከ።
12ኪራምም፡ደግሞ፡አለ፦ሰማይንና፡ምድርን፡የፈጠረ፥ለእግዚአብሔርም፡ቤት፡ለመንግሥቱም፡ቤት፡ ይሠራ፡ዘንድ፡ጥበበኛና፡ብልኀተኛ፡አስተዋይም፡ልጅ፡ለንጉሡ፡ለዳዊት፡የሰጠ፡የእስራኤል፡አምላክ፡ እግዚአብሔር፡ቡሩክ፡ይኹን።
13አኹንም፡ከብልኀተኛዎችኽ፡ጋራ፡ከጌታዬም፡ከአባትኽ፡ከዳዊት፡ብልኀተኛዎች፡ጋራ፡ይኾን፡ዘንድ፡ ኪራምአቢ፡የሚባል፡ብልኀተኛና፡አስተዋይ፡ሰው፡ሰድጄልኻለኹ።
14እናቱ፡ከዳን፡ልጆች፡ናት፥አባቱም፡የጢሮስ፡ሰው፡ነው፤ወርቁንና፡ብሩንም፥ናሱንና፡ ብረቱን፥ድንጋይንና፡ዕንጨቱን፥ሐምራዊውንና፡ሰማያዊውን፡ቀዩንም፡ግምጃ፥ጥሩውንም፡በፍታ፡ይሠራ፡ ዘንድ፥ቅርጽም፡ሌላም፡ነገር፡ዅሉ፡ያደርግ፡ዘንድ፡ያውቃል።
15አኹንም፡ጌታዬ፡የተናገረውን፡ስንዴውንና፡ገብሱን፡ዘይቱንና፡የወይን፡ጠጁን፡ወደ፡ባሪያዎቹ፡ይስደድ፤
16እኛም፡ከሊባኖስ፡የምትሻውን፡ያኽል፡ዕንጨት፡እንቈርጣለን፥በታንኳም፡አድርገን፡በባሕር፡ላይ፡ወዳንተ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ወደ፡ኢዮጴ፡እንሰዳ፟ለን፤አንተም፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ታስወስደዋለኽ።
17ሰሎሞንም፡በእስራኤል፡ምድር፡የነበሩትን፡መጻተኛዎች፡ዅሉ፡አባቱ፡ዳዊት፡እንደ፡ቈጠራቸው፡ ቈጠረ፤መቶ፡ዐምሳ፡ሦስት፡ሺሕ፡ስድስት፡መቶ፡ተገኙ።
18ከነርሱም፡የሚሸከሙትን፡ሰባ፡ሺሕ፥በተራራዎችም፡ላይ፡የሚጠርቡትን፡ሰማንያ፡ሺሕ፥በሕዝቡም፡ሥራ፡ ላይ፡የተሾሙትን፡ሦስት፡ሺሕ፡ስድስት፡መቶ፡አደረገ።