Skip to content
← 2 Chronicles

Chapter 22 · Amharic

2 Chronicles

1በኢየሩሳሌም፡የነበሩትም፡ታናሹን፡ልጁን፡አካዝያስን፡በርሱ፡ፋንታ፡አነገሡት።የመጣባቸው፡የዐረብና፡ የአሊማዞን፡የሽፍቶች፡ጭፍራ፡የርሱን፡ታላቆች፡ገድለዋቸው፡ነበርና።የይሁዳ፡ንጉሥ፡የኢዮራም፡ልጅ፡ አካዝያስ፡ነገሠ።

2አካዝያስም፡መንገሥ፡በዠመረ፡ጊዜ፡ዕድሜው፡አርባ፡ኹለት፡ዓመት፡ነበረ፥በኢየሩሳሌምም፡አንድ፡ ዓመት፡ነገሠ፤እናቱም፡ጎቶሊያ፡የተባለች፡የዘንበሪ፡ልጅ፡ነበረች።

3እናቱም፡ክፉ፡ለማድረግ፡ትመክረው፡ነበርና፥ርሱ፡ደግሞ፡በአክአብ፡ቤት፡መንገድ፡ኼደ።

4አባቱም፡ከሞተ፡በዃላ፡የአክአብ፡ቤት፡እንዳደረገ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ክፉ፡አደረገ፤እስኪጠፉ፡ድረስ፡ መካሪዎች፡ነበሩትና።

5በምክራቸውም፡ኼደ፥ከእስራኤልም፡ንጉሥ፡ከአክአብ፡ልጅ፡ከኢዮራም፡ጋራ፡የሶርያን፡ንጉሥ፡አዛሄልን፡ በሬማት፡ዘገለአድ፡ሊዋጋ፡ኼደ፤ሶርያውያንም፡ኢዮራምን፡አቈሰሉት።

6ከሶርያም፡ንጉሥ፡ከአዛሄል፡ጋራ፡በተዋጋ፡ጊዜ፡ሶርያውያን፡በሬማት፡ያቈሰሉትን፡ቍስል፡ይታከም፡ዘንድ፡ ወደ፡ኢይዝራኤል፡ተመለሰ፤ታሞ፟ም፡ነበርና፥የይሁዳ፡ንጉሥ፡የኢዮራም፡ልጅ፡አካዝያስ፡የአክአብን፡ልጅ፡ ኢዮራምን፡ያይ፡ዘንድ፡ወደ፡ኢይዝራኤል፡ወረደ።

7አካዝያስም፡ወደ፡ኢዮራም፡በመምጣቱ፡ይጠፋ፡ዘንድ፡የእግዚአብሔር፡ፈቃድ፡ነበረ፤በመጣም፡ጊዜ፡ ከኢዮራም፡ጋራ፡እግዚአብሔር፡የአክአብን፡ቤት፡ያጠፋ፡ዘንድ፡ወደቀባው፡ወደናሜሲ፡ልጅ፡ወደ፡ኢዩ፡ ወጣ።

8ኢዩም፡በአክአብ፡ቤት፡ላይ፡ፍርድን፡ሲፈጽም፡የይሁዳን፡መሳፍንትና፡አካዝያስን፡ያገለግሉ፡የነበሩትን፡ የአካዝያስን፡ወንድሞች፡ልጆች፡አግኝቶ፡ገደላቸው።

9አካዝያስንም፡ፈለገው፥በሰማርያ፡ተሸሽጎ፡ሳለ፡አገኙት፤ወደ፡ኢዩም፡አምጥተው፡ገደሉትና፦በፍጹም፡ ልብ፡እግዚአብሔርን፡የፈለገው፡የኢዮሳፍጥ፡ልጅ፡ነው፡ብለው፡ቀበሩት።ከአካዝያስም፡ቤት፡ማንም፡ መንግሥትን፡ይይዝ፡ዘንድ፡የሚችል፡አልነበረም።

10የአካዝያስም፡እናት፡ጎቶሊያ፡ልጇ፡እንደ፡ሞተ፡ባየች፡ጊዜ፡ተነሥታ፡የይሁዳን፡ቤተ፡መንግሥት፡ዘር፡ ዅሉ፡አጠፋች።

11የንጉሡ፡ልጅ፡ዮሳቤት፡ግን፡ከተገደሉት፡ከንጉሡ፡ልጆች፡መካከል፡የአካዝያስን፡ልጅ፡ኢዮአስን፡ሰርቃ፡ ወሰደች፤ርሱንና፡ሞግዚቱን፡በዕልፍኝ፡ውስጥ፡አኖረቻቸው፤ጎቶሊያ፡እንዳታስገድለው፡የንጉሡ፡የኢዮራም፡ ልጅ፡የአካዛያስ፡እኅት፡የካህኑ፡የዮዳዔ፡ሚስት፡ዮሳቤት፡እንዲሁ፡ሸሸገችው።

12በእነርሱም፡ዘንድ፡ተሸሽጎ፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡ስድስት፡ዓመት፡ያኽል፡ተቀመጠ፤ጎቶልያም፡በምድር፡ ላይ፡ነገሠች። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source