Skip to content
← 2 Chronicles

Chapter 25 · Amharic

2 Chronicles

1አሜስያስም፡መንገሥ፡በዠመረ፡ጊዜ፡የኻያ፡ዐምስት፡ዓመት፡ጕልማሳ፡ነበረ፥በኢየሩሳሌምም፡ኻያ፡ ዘጠኝ፡ዓመት፡ነገሠ፤እናቱ፡ዮዓዳን፡የተባለች፡የኢየሩሳሌም፡ሴት፡ነበረች።

2በእግዚአብሔርም፡ፊት፡ቅን፡ነገር፡አደረገ፥ነገር፡ግን፥በፍጹም፡ልብ፡አይደለም።

3መንግሥትም፡በጸናለት፡ጊዜ፡አባቱን፡የገደሉትን፡ባሪያዎች፡ገደለ።

4በሙሴም፡ሕግ፡መጽሐፍ፡እንደ፡ተጻፈ፥እግዚአብሔርም፦ሰው፡ዅሉ፡በገዛ፡ኀጢአቱ፡ይሙት፡እንጂ፡ አባቶች፡በልጆች፡ፋንታ፡አይሙቱ፥ልጆችም፡በአባቶች፡ፋንታ፡አይሙቱ፡ብሎ፡እንዳዘዘ፡የነፍሰ፡ገዳዮችን፡ ልጆች፡አልገደለም።

5አሜስያስም፡ይሁዳን፡ሰበሰበ፥በያባቶቻቸውም፡ቤቶች፡ከሺሕ፡አለቃዎችና፡ከመቶ፡አለቃዎች፡እጅ፡በታች፡ አቆማቸው፤ከኻያ፡ዓመት፡ዠምሮ፡ከዚያም፡በላይ፡ያሉትን፡ይሁዳንና፡ብንያምን፡ዅሉ፡ቈጠረ፥ለሰልፍም፡ የሚወጡ፥ጋሻና፡ጦርም፡የሚይዙ፡ሦስት፡መቶ፡ሺሕ፡የተመረጡ፡ሰዎች፡አገኘ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

6ደግሞም፡ከእስራኤል፡ዘንድ፡መቶ፡ሺሕ፡ጽኑዓን፡ኀያላን፡በመቶ፡መክሊት፡ብር፡ቀጠረ።

7አንድ፡የእግዚአብሔር፡ሰው፡ግን፡ወደ፡ርሱ፡መጥቶ፦ንጉሥ፡ሆይ፥እግዚአብሔር፡ከእስራኤልና፡ ከኤፍሬም፡ልጆች፡ጋራ፡አይደለምና፡የእስራኤል፡ጭፍራ፡ከአንተ፡ጋራ፡አይውጣ።

8ብትኼድ፡ግን፥በእነርሱም፡ማሸነፍን፡ብታስብ፥የመርዳትና፡የመጣል፡ኀይል፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ ነውና፥እግዚአብሔር፡በጠላቶችኽ፡ፊት፡ይጥልኻል፡አለው።

9አሜስያስም፡የእግዚአብሔርን፡ሰው፦ለእስራኤል፡ጭፍራ፡የሰጠኹት፡መቶ፡መክሊት፡ምን፡ ይኹን፧አለው።የእግዚአብሔርም፡ሰው፦ከዚህ፡አብልጦ፡ይሰጥኽ፡ዘንድ፡እግዚአብሔር፡ይችላል፡ብሎ፡ መለሰለት።

10አሜስያስም፡ከኤፍሬም፡የመጡት፡ጭፍራዎች፡ወደ፡ስፍራቸው፡ይመለሱ፡ዘንድ፡ለይቶ፡ አሰናበታቸው፤ስለዚህም፡ቍጣቸው፡በይሁዳ፡ላይ፡ጸና፥ወደ፡አገራቸውም፡በጽኑ፡ቍጣ፡ተመለሱ።

11አሜስያስም፡በረታ፥ሕዝቡንም፡አውጥቶ፡ወደጨው፡ሸለቆ፡ኼደ፥ከሴይርም፡ልጆች፡ዐሥር፡ሺሕ፡ገደለ።

12የይሁዳም፡ልጆች፡ደግሞ፡ዐሥር፡ሺሕ፡ሰዎችን፡በሕይወታቸው፡ማረኩ፥ወደአለቱም፡ራስ፡ላይ፡ አመጧቸው፤ከአለቱም፡ራስ፡ላይ፡ጣሏቸው፥ዅሉም፡ተፈጠፈጡ።

13አሜስያስ፡ግን፡ከርሱ፡ጋራ፡ወደ፡ሰልፍ፡እንዳይኼዱ፡ያሰናበታቸው፡ጭፍራዎች፡ከሰማርያ፡ዠምረው፡ እስከ፡ቤትሖሮን፡ድረስ፡በይሁዳ፡ከተማዎች፡ላይ፡አደጋ፡ጣሉ፥ከነርሱም፡ሦስት፡ሺሕ፡ገደሉ፥ብዙ፡ ምርኮም፡ማረኩ።

14አሜስያስም፡የኤዶምያስን፡ሰዎች፡ከገደለ፡በዃላ፡የሴይርን፡ልጆች፡አማልክት፡አመጣ፥የርሱም፡ አማልክት፡ይኾኑ፡ዘንድ፡አቆማቸው፥ይሰግድላቸውም፡ያጥንላቸውም፡ነበር።

15ስለዚህም፡የእግዚአብሔር፡ቍጣ፡በአሜስያስ፡ላይ፡ነደደና፦ሕዝባቸውን፡ከአንተ፡እጅ፡ያላዳኑትን፡ የአሕዛብን፡አማልክት፡ስለ፡ምን፡ፈለግኻቸው፧የሚል፡ነቢይ፡ሰደደበት።

16ርሱም፡ሲናገር፡ንጉሡ፦በእውኑ፡አንተ፡የንጉሡ፡አማካሪ፡ልትኾን፡ሾመንኻልን፧ተው፤ቅጣትን፡ስለ፡ ምን፡ትሻለኽ፧አለው።ነቢዩም፦ይህን፡አድርገኻልና፥ምክሬንም፡አልሰማኽምና፡እግዚአብሔር፡ሊያጠፋኽ፡ እንዳሰበ፡ዐወቅኹ፡ብሎ፡ተወ።

17የይሁዳም፡ንጉሥ፡አሜስያስ፡ምክር፡አደረገና፦ና፥ርስ፡በርሳችን፡ፊት፡ለፊት፡እንተያይ፡ብሎ፡ ወደእስራኤል፡ንጉሥ፡ወደኢዩ፡ልጅ፡ወደኢዮአካዝ፡ልጅ፡ወደ፡ኢዮአስ፡ላከ።

18የእስራኤልም፡ንጉሥ፡ኢዮስያስ፦የሊባኖስ፡ኵርንችት፦ልጅኽን፡ለልጄ፡ሚስት፡አድርገኽ፡ስጠው፡ብሎ፡ ወደ፡ሊባኖስ፡ዝግባ፡ላከ፤የሊባኖስም፡አውሬ፡ዐልፎ፡ኵርንችቱን፡ረገጠ።

19አንተም፦እንሆ፥ኤዶምያስን፡መትቻለኹ፡ብለኽ፡ኰርተኻል፤በቤትኽ፡ተቀመጥ፤አንተ፡ከይሁዳ፡ጋራ፡ ትወድቅ፡ዘንድ፡ስለ፡ምን፡መከራን፡ትሻለኽ፧ብሎ፡ወደይሁዳ፡ንጉሥ፡ወደ፡አሜስያስ፡ላከ።

20የኤዶምያስንም፡አማልክት፡ስለ፡ፈለጉ፡በጠላቶቻቸው፡እጅ፡አሳልፎ፡ይሰጣቸው፡ዘንድ፡የእግዚአብሔር፡ ፈቃድ፡ነበረና፡አሜስያስ፡አልሰማም።

21የእስራኤልም፡ንጉሥ፡ኢዮአስ፡ወጣ፤ርሱና፡የይሁዳ፡ንጉሥ፡አሜስያስም፡በይሁዳ፡ባለች፡በቤትሳሚስ፡ ላይ፡ርስ፡በርሳቸው፡ተያዩ።

22ይሁዳም፡በእስራኤል፡ፊት፡ተመታ፥እያንዳንዱም፡ወደ፡ድንኳኑ፡ሸሸ።

23የእስራኤልም፡ንጉሥ፡ኢዮአስ፡የይሁዳን፡ንጉሥ፡የአካዝያስን፡ልጅ፡የኢዮአስን፡ልጅ፡አሜስያስን፡ በቤትሳሚስ፡ይዞ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡አመጣው፥የኢየሩሳሌምንም፡ቅጥር፡ከኤፍሬም፡በር፡ዠምሮ፡እስከማእዘኑ፡ በር፡ድረስ፡አራት፡መቶ፡ክንድ፡አፈረሰ።

24ወርቁንና፡ብሩን፡ዅሉ፥በእግዚአብሔርም፡ቤት፡ከዖቤድኤዶም፡ጋራ፡የነበሩትን፡ዕቃዎች፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ዅሉ፥የንጉሡን፡ቤት፡መዛግብት፥በመያዣ፡የተያዙትንም፡ወስዶ፡ወደ፡ሰማርያ፡ተመለሰ።

25የይሁዳም፡ንጉሥ፡የኢዮአስ፡ልጅ፡አሜስያስ፡ከእስራኤል፡ንጉሥ፡ከኢዮአካዝ፡ልጅ፡ከኢዮአስ፡ሞት፡ በዃላ፡ዐሥራ፡ዐምስት፡ዓመት፡ኖረ።

26የቀረውም፡የፊተኛውና፡የዃላኛው፡የአሜስያስ፡ነገር፥እንሆ፥በይሁዳና፡በእስራኤል፡ነገሥታት፡መጽሐፍ፡ የተጻፈ፡አይደለምን፧

27አሜስያስም፡እግዚአብሔርን፡ከመከተል፡ከራቀ፡በዃላ፡በኢየሩሳሌም፡የዐመፅ፡መሐላ፡አደረጉበት፥ወደ፡ ለኪሶም፡ኰበለለ፤በስተዃላውም፡ወደ፡ለኪሶ፡ላኩ፥በዚያም፡ገደሉት።

28በፈረስም፡ጭነው፡አመጡት፥በዳዊትም፡ከተማ፡ከአባቶቹ፡ጋራ፡ቀበሩት።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source