Skip to content
← 2 Chronicles

Chapter 32 · Amharic

2 Chronicles

1ከዚህም፡ነገርና፡ከዚህ፡እምነት፡በዃላ፡የአሶር፡ንጉሥ፡ሰናክሬም፡መጥቶ፡ወደ፡ይሁዳ፡ ገባ፥በተመሸጉትም፡ከተማዎች፡ፊት፡ሰፈረ፥ሊወስዳቸውም፡ዐሰበ።

2ሕዝቅያስም፡ሰናክሬም፡እንደ፡መጣ፥ኢየሩሳሌምንም፡ሊወጋ፡ፊቱን፡እንዳቀና፡ባየ፡ጊዜ፥

3ከከተማዪቱ፡በስተውጭ፡ያለውን፡የውሃውን፡ምንጭ፡ይደፍኑ፡ዘንድ፡ከአለቃዎቹና፡ከኀያላኑ፡ጋራ፡ ተማከረ፤እነርሱም፡ረዱት።

4እጅግም፡ሰዎች፡ተሰብስበው፦የአሶር፡ነገሥታት፡መጥተው፡ብዙ፡ውሃ፡ስለ፡ምን፡ያገኛሉ፧ብለው፡ ምንጩን፡ዅሉ፥በምድርም፡መካከል፡ይንዶለዶል፡የነበረውን፡ወንዝ፡ደፈኑ።

5ሰውነቱንም፡አጸናና፥የፈረሰውንም፡ቅጥር፡ዅሉ፡ጠገነ፥በላዩም፡ግንብ፡ሠራበት፥ከርሱም፡በስተውጭ፡ ሌላ፡ቅጥር፡ሠራ፤በዳዊትም፡ከተማ፡ያለችውን፡ሚሎን፡አጠነከረ፤ብዙም፡መሣሪያና፡ጋሻ፡ሠራ።

6የጦር፡አለቃዎቹንም፡በሕዝቡ፡ላይ፡ሾሞ፥ዅሉንም፡በከተማዪቱ፡በር፡ወዳለው፡አደባባይ፡ሰብስቦ።

7ጽኑ፥አይዟችኹ፤ከእኛም፡ጋራ፡ያለው፡ከርሱ፡ጋራ፡ካለው፡ይበልጣልና፥ከአሶር፡ንጉሥና፡ከርሱ፡ጋራ፡ ካለው፡ጭፍራ፡ዅሉ፡አትፍሩ፥አትደንግጡም።

8ከርሱ፡ጋራ፡የሥጋ፡ክንድ፡ነው፤ከእኛ፡ጋራ፡ያለው፡ግን፡የሚረዳንና፡የሚዋጋልን፡አምላካችን፡ እግዚአብሔር፡ነው፡ብሎ፡አጸናናቸው።ሕዝቡም፡በይሁዳ፡ንጉሥ፡በሕዝቅያስ፡ቃል፡ተጽናና።

9ከዚህም፡በዃላ፡የአሶር፡ንጉሥ፡ሰናክሬም፡ከሰራዊቱ፡ዅሉ፡ጋራ፡በለኪሶ፡ፊት፡ሳለ፡ባሪያዎቹን፡ወደ፡ ኢየሩሳሌም፡ወደይሁዳ፡ንጉሥ፡ወደ፡ሕዝቅያስና፡በኢየሩሳሌም፡ወደነበሩ፡ወደ፡ይሁዳ፡ዅሉ፡እንዲህ፡ሲል፡ ላከ።

10የአሶር፡ንጉሥ፡ሰናክሬም፡እንዲህ፡ይላል፦እናንተ፡በማን፡ተማምናችኹ፡በኢየሩሳሌም፡ምሽግ፡ ትቀመጣላችኹ፧

11አምላካችን፡እግዚአብሔር፡ከአሶር፡ንጉሥ፡እጅ፡ያድነናል፡እያለ፡በራብና፡በጥም፡እንድትሞቱ፡አሳልፎ፡ ይሰጣችኹ፡ዘንድ፡የሚያባብላችኹ፡ሕዝቅያስ፡አይደለምን፧

12ባንድ፡መሠዊያ፡ፊት፡ስገዱ፥በርሱም፡ላይ፡ዕጠኑ፡እያለ፡ይሁዳንና፡ኢየሩሳሌምን፡አዞ፟፥የኰረብታው፡ መስገጃዎቹና፡መሠዊያዎቹን፡ያፈረሰ፡ይህ፡ሕዝቅያስ፡አይደለምን፧

13እኔና፡አባቶቼ፡በምድር፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ያደረግነውን፡አላወቃችኹምን፧የምድርስ፡ዅሉ፡አሕዛብ፡ አማልክት፡አገራቸውን፡ከእጄ፡ያድኑ፡ዘንድ፡በእውኑ፡ተቻላቸውን፧

14አምላካችኹስ፡ከእጄ፡እናንተን፡ለማዳን፡ይችል፡ዘንድ፡አባቶቼ፡ካጠፏቸው፡ከአሕዛብ፡አማልክት፡ዅሉ፡ ሕዝቡን፡ከእጄ፡ያድን፡ዘንድ፡የቻለ፡ማን፡ነው፧

15አኹንም፡ሕዝቅያስ፡አያስታችኹ፥እንዲህም፡አያባብላችኹ፥አትመኑትም፤ከአሕዛብና፡ከመንግሥታት፡ አማልክት፡ዅሉ፡ሕዝቡን፡ከእጄና፡ከአባቶቼ፡እጅ፡ያድን፡ዘንድ፡ዘንድ፡ማንም፡አልቻለም፤ይልቁንስ፡ አምላካችኹ፡ከእጄ፡ያድናችኹ፡ዘንድ፡እንዴት፡ይችላል፧

16ባሪያዎቹም፡ደግሞ፡በአምላክ፡በእግዚአብሔርና፡በባሪያው፡በሕዝቅያስ፡ላይ፡ሌላ፡ብዙ፡ነገር፡ተናገሩ።

17ደግሞም፡የእስራኤልን፡አምላክ፡እግዚአብሔርን፡ለመስደብ፥በርሱም፡ላይ፡ለመናገር።የምድር፡አሕዛብ፡ አማልክት፡ሕዝባቸውን፡ከእጄ፡ያድኑ፡ዘንድ፡እንዳልቻሉ፥እንዲሁ፡የሕዝቅያስ፡አምላክ፡ሕዝቡን፡ከእጄ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ያድን፡ዘንድ፡አይችልም፡የሚል፡ደብዳቤ፡ጻፈ።

18ከተማዪቱንም፡እንዲወስዱ፥በቅጥር፡ላይ፡የተቀመጡትን፡የኢየሩሳሌም፡ሕዝብ፡ያስፈሩና፡ያስደነግጡ፡ ዘንድ፥በታላቅ፡ድምፅ፡በዕብራይስጥ፡ቋንቋ፡ይጮኹባቸው፡ነበር።

19በሰውም፡እጅ፡በተሠሩ፡በምድር፡አሕዛብ፡አማልክት፡ላይ፡እንደሚናገሩ፡መጠን፡በኢየሩሳሌም፡አምላክ፡ ላይ፡ተናገሩ።

20ንጉሡም፡ሕዝቅያስና፡የዓሞጽ፡ልጅ፡ነቢዩ፡ኢሳይያስ፡ስለዚህ፡ጸለዩ፥ወደ፡ሰማይም፡ጮኹ።

21እግዚአብሔርም፡ጽኑዓን፡ኀያላኑንና፡መሳፍንቱን፡አለቃዎቹንም፡ከአሶር፡ንጉሥ፡ሰፈር፡እንዲያጠፋ፡ መልአኩን፡ሰደደ።የአሶርም፡ንጉሥ፡ዐፍሮ፡ወደ፡አገሩ፡ተመለሰ።ወደአምላኩም፡ቤት፡በገባ፡ጊዜ፡ከወገቡ፡ የወጡት፡ልጆቹ፡በዚያ፡በሰይፍ፡ገደሉት።

22እንዲሁም፡እግዚአብሔር፡ሕዝቅያስንና፡በኢየሩሳሌም፡የሚኖሩትን፡ከአሶር፡ንጉሥ፡ከሰናክሬም፡እጅ፡ ከዅሉም፡እጅ፡አዳናቸው፤በዙሪያቸውም፡ካለው፡ዅሉ፡አሳረፋቸው።

23ብዙዎቹም፡ለእግዚአብሔር፡መባ፡ይዘው፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ይመጡ፡ነበር፥ለይሁዳም፡ንጉሥ፡ ለሕዝቅያስ፡እጅ፡መንሻ፡ይሰጡ፡ነበር፤ርሱም፡ከዚህ፡ነገር፡በዃላ፡በአሕዛብ፡ዅሉ፡ፊት፡ከፍ፡ከፍ፡አለ።

24በዚያም፡ወራት፡ሕዝቅያስ፡እስኪሞት፡ድረስ፡ታመመ፥ወደ፡እግዚአብሔርም፡ጸለየ፤ርሱም፡ ተናገረው፥ምልክትም፡ሰጠው።

25ሕዝቅያስ፡ግን፡እንደተቀበለው፡ቸርነት፡መጠን፡አላደረገም፥ልቡም፡ኰራ፤ስለዚህም፡በርሱና፡በይሁዳ፡ በኢየሩሳሌምም፡ላይ፡ቍጣ፡ኾነ።

26ሕዝቅያስም፡ከኢየሩሳሌም፡ሰዎች፡ጋራ፡ስለልቡ፡ኵራት፡ሰውነቱን፡አዋረደ፥የእግዚአብሔርም፡ቍጣ፡ በሕዝቅያስ፡ዘመን፡አልመጣባቸውም።

27ለሕዝቅያስም፡እጅግ፡ብዙ፡ሀብትና፡ክብር፡ነበረው፤ለብርና፡ለወርቅም፥ለከበረው፡ዕንቍና፡ ለሽቱው፥ለጋሻውና፡ለከበረው፡ዕቃ፡ዅሉ፡ግምጃ፡ቤቶች፡ሠራ።

28ለእኽልና፡ለወይን፡ጠጅም፡ለዘይትም፡ዕቃ፡ቤቶች፥ለልዩ፡ልዩም፡እንስሳ፡ጋጥ፥ለመንጋዎችም፡በረት፡ ሠራ።

29እግዚአብሔርም፡እጅግ፡ብዙ፡ጥሪት፡ሰጥቶት፡ነበርና፥ከተማዎችን፡ሠራ፥ብዙም፡የበግና፡የላም፡መንጋ፡ ሰበሰበ።

30ይህም፡ሕዝቅያስ፡የላይኛውን፡የግዮንን፡ውሃ፡ምንጭ፡ደፈነ፥በዳዊትም፡ከተማ፡በምዕራብ፡በኩል፡ አቅንቶ፡አወረደው።የሕዝቅያስም፡ሥራ፡ዅሉ፡ተከናወነ።

31ነገር፡ግን፥የባቢሎን፡መሳፍንት፡መልእክተኛዎች፡በአገሩ፡ላይ፡ስለተደረገው፡ተኣምራት፡ይጠይቁት፡ ዘንድ፡ወደ፡ርሱ፡በተላኩ፡ጊዜ፡እግዚአብሔር፡ይፈትነውና፡በልቡ፡ያለውን፡ዅሉ፡ያውቅ፡ዘንድ፡ተወው።

32የሕዝቅያስም፡የቀረው፡ነገር፥ቸርነቱም፥እንሆ፥በዓሞጽ፡ልጅ፡በነቢዩ፡በኢሳይያስ፡ራእይ፡በይሁዳና፡ በእስራኤልም፡ነገሥታት፡መጽሐፍ፡ተጽፏል።

33ሕዝቅያስም፡ከአባቶቹ፡ጋራ፡አንቀላፋ፥በዳዊትም፡ልጆች፡መቃብር፡በላይኛው፡ክፍል፡ቀበሩት፤በይሁዳና፡ በኢየሩሳሌምም፡የሚኖሩ፡ዅሉ፡በሞቱ፡አከበሩት።ልጁም፡ምናሴ፡በርሱ፡ፋንታ፡ነገሠ።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source