1እንዲሁም፡ሰሎሞን፡ስለእግዚአብሔር፡ቤት፡የሠራው፡ሥራ፡ዅሉ፡ተጨረሰ።አባቱም፡ዳዊት፡የቀደሰውን፡ የብርና፡የወርቅ፡ዕቃ፡ዅሉ፡ሰሎሞን፡አምጥቶ፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡ውስጥ፡በነበረው፡ግምጃ፡ቤት፡ አኖረው።
2በዚያን፡ጊዜም፡ሰሎሞን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡ከዳዊት፡ከተማ፡ከጽዮን፡ያወጡ፡ዘንድ፡ የእስራኤልን፡ሽማግሌዎችና፡የነገድ፡አለቃዎች፡ዅሉ፡የእስራኤልንም፡ልጆች፡አባቶች፡ቤቶች፡መሳፍንት፡ወደ፡ ኢየሩሳሌም፡ሰበሰበ።
3የእስራኤልም፡ሰዎች፡ዅሉ፡በሰባተኛው፡ወር፡በበዓሉ፡ጊዜ፡ጊዜ፡ወደ፡ንጉሡ፡ተከማቹ።
4የእስራኤልም፡ሽማግሌዎች፡ዅሉ፡መጡ፥ሌዋውያንም፡ታቦቱን፡አነሡ።
5ታቦቱንም፡የመገናኛውንም፡ድንኳን፡በድንኳኑም፡ውስጥ፡የነበረውን፡የተቀደሰውን፡ዕቃ፡ዅሉ፡ አመጡ፤እነዚህንም፡ዅሉ፡ካህናቱና፡ሌዋውያኑ፡አመጡ።
6ንጉሡም፡ሰሎሞን፡ከርሱም፡ጋራ፡የተሰበሰቡ፡የእስራኤል፡ማኅበር፡ዅሉ፡በታቦቱ፡ፊት፡ኾነው፡ከብዛት፡ የተነሣ፡የማይቈጠሩትንና፡የማይመጠኑትን፡በጎችና፡በሬዎች፡ይሠዉ፡ነበር።
7ካህናቱም፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡ወደ፡ቤቱ፡አምጥተው፡በቅድስት፡ቅዱሳን፡ውስጥ፡ ከኪሩቤል፡ክንፍ፡በታች፡በነበረው፡በስፍራው፡አኖሩት።
8ኪሩቤልም፡በታቦቱ፡ስፍራ፡ላይ፡ክንፎቻቸውን፡ዘርግተው፡ነበር፥ኪሩቤልም፡ታቦቱንና፡መሎጊያዎቹን፡ በስተላዩ፡በኩል፡ይሸፍኑ፡ነበር።
9መሎጊያዎቹም፡ረዣዥሞች፡ነበሩና፥በቅድስተ፡ቅዱሳን፡ፊት፡ከመቅደሱ፡ውስጥ፡ጫፎቻቸው፡ይታዩ፡ ነበር፤ነገር፡ግን፥ከውጪ፡አይታዩም፡ነበር፤እስከ፡ዛሬም፡ድረስ፡እዚያ፡አሉ።
10በታቦቱም፡ውስጥ፡የእስራኤል፡ልጆች፡ከግብጽ፡ምድር፡በወጡ፡ጊዜ፥እግዚአብሔርም፡ከነርሱ፡ጋራ፡ ቃል፡ኪዳን፡ባደረገ፡ጊዜ፡ሙሴ፡በኰሬብ፡ካስቀመጣቸው፡ከኹለቱ፡ጽላቶች፡በቀር፡ምንም፡አልነበረበትም።
11በዚያም፡የነበሩት፡ካህናት፡ዅሉ፡ተቀድሰው፡ነበር፥በሰሞናቸውም፡አልተከፈሉም፡ነበር፤
12መዘምራንም፡የነበሩት፡ሌዋውያን፡ዅሉ፥አሣፍና፡ኤማን፡ኤዶታምም፡ልጆቻቸውም፡ ወንድሞቻቸውም፥ጥሩ፡በፍታ፡ለብሰው፡ጸናጽልና፡በገና፡መሰንቆም፡እየመቱ፡በመሠዊያው፡አጠገብ፡ በምሥራቅ፡በኩል፡ቆመው፡ነበር፤ከነርሱም፡ጋራ፡መቶ፡ኻያ፡ካህናት፡መለከት፡ይነፉ፡ነበር።ካህናቱም፡ ከመቅደሱ፡በወጡ፡ጊዜ፥
13መለከቱንም፡የሚነፉ፡መዘምራኑም፡በአንድነት፡ኾነው፡እግዚአብሔርን፡እያመሰገኑና፡ እያከበሩ፦እግዚአብሔር፡ቸር፡ነውና፥ምሕረቱም፡ለዘለዓለም፡ነውና፥እግዚአብሔርን፡አመስግኑ፡እያሉ፡ ባንድ፡ቃል፡ድምፃቸውን፡ወደ፡ላይ፡ከፍ፡አድርገው፡በመለከትና፡በጸናጽል፡በዜማም፡ዕቃ፡ዅሉ፡ እግዚአብሔርን፡ባመሰገኑ፡ጊዜ፥ደመናው፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡ሞላው።
14የእግዚአብሔርም፡ክብር፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡ሞልቶት፡ነበርና፥ካህናቱ፡ከደመናው፡የተነሣ፡መቆምና፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ማገልገል፡አልተቻላቸውም።