1ንጉሡም፡ሕዝቅያስ፡ይህን፡በሰማ፡ጊዜ፥ልብሱን፡ቀደደ፥ማቅም፡ለበሰ፥ወደእግዚአብሔርም፡ቤት፡ገባ።
2የቤቱንም፡አዛዥ፡ኤልያቄምን፡ጸሓፊውንም፡ሳምናስን፡የካህናቱንም፡ሽማግሌዎች፡ማቅ፡ለብሰው፡ወደነቢዩ፡ ወደዓሞጽ፡ልጅ፡ወደ፡ኢሳይያስ፡ይኼዱ፡ዘንድ፡ላካቸው።
3እነርሱም፦ሕዝቅያስ፡እንዲህ፡ይላል፦ይህ፡ቀን፡የመከራና፡የተግሣጽ፡የዘለፋም፡ቀን፡ነው፤ልጆች፡ የሚወለዱበት፡ጊዜ፡ደርሷል፥ለመውለድም፡ኀይል፡የለም።
4ምናልባት፡በሕያው፡አምላክ፡ላይ፡ይገዳደር፡ዘንድ፡ጌታው፡የአሶር፡ንጉሥ፡የላከውን፡የራፋስቂስን፡ቃል፡ ዅሉ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ይሰማ፡እንደ፡ኾነ፥አምላክኽ፡እግዚአብሔርም፡ስለሰማው፡ቃል፡ይገሥጸው፡ እንደ፡ኾነ፥ስለዚህ፡ለቀረው፡ቅሬታ፡ጸልይ፡አሉት።
5እንዲሁ፡የንጉሡ፡የሕዝቅያስ፡ባሪያዎች፡ወደ፡ኢሳይያስ፡መጡ።
6ኢሳይያስም፦ለጌታችኹ፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የአሶር፡ንጉሥ፡ባሪያዎች፡ስለ፡ ሰደቡኝ፥ስለሰማኸው፡ቃል፡አትፍራ።
7እንሆ፥በላዩ፡መንፈስን፡እሰዳ፟ለኹ፥ወሬንም፡ይሰማል፥ወደ፡ምድሩም፡ይመለሳል፤በምድሩም፡በሰይፍ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org እንዲወድቅ፡አደርገዋለኹ፡በሉት፡አላቸው።
8የአሶርም፡ንጉሥ፡ከለኪሶ፡እንደ፡ራቀ፡ሰምቶ፡ነበርና፥ራፋስቂስ፡ተመልሶ፡በልብና፡ሲዋጋ፡አገኘው።
9ርሱም፦የኢትዮጵያ፡ንጉሥ፡ቲርሐቅ፡ሊወጋኽ፡መጥቷል፡የሚል፡ወሬ፡በሰማ፡ጊዜ፡ደግሞ፡ወደ፡ ሕዝቅያስ፡መልእክተኛዎችን፡ላከ፥እንዲህ፡ሲል፦
10ለይሁዳ፡ንጉሥ፡ለሕዝቅያስ፡እንዲህ፡ብላችኹ፡ንገሩት፦ኢየሩሳሌም፡በአሶር፡ንጉሥ፡እጅ፡አትሰጥም፡ ብሎ፡የምትታመንበት፡አምላክኽ፡አያታል፟ኽ።
11እንሆ፥የአሶር፡ነገሥታት፡በምድር፡ዅሉ፡ላይ፡ያደረጉትን፥እንዴትስ፡እንዳጠፏቸው፡ሰምተኻል፤አንተስ፡ ትድናለኽን፧
12አባቶቼ፡ያጠፏቸውን፥ጎዛንን፥ካራንን፥ራፊስን፥በተላሳር፡የነበሩትንም፡የዔዴንን፡ልጆች፥የአሕዛብ፡ አማልክት፡አዳኗቸውን፧
13የሐማት፡ንጉሥ፥የአርፋድ፡ንጉሥ፥የሴፈርዋይም፡ከተማ፡ንጉሥ፥የሄናና፡የዒዋ፡ንጉሥ፡ወዴት፡አሉ፧
14ሕዝቅያስም፡ደብዳቤውን፡ከመልእክተኛዎች፡እጅ፡ተቀብሎ፡አነበበው፤ሕዝቅያስም፡ወደእግዚአብሔር፡ ቤት፡ወጥቶ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ዘረጋው።
15ሕዝቅያስም፡ወደ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ብሎ፡ጸለየ፦በኪሩቤል፡ላይ፡የምትቀመጥ፡የእስራኤል፡ አምላክ፡አቤቱ፥አንተ፡ብቻኽን፡የምድር፡ነገሥታት፡ዅሉ፡አምላክ፡ነኽ፤ሰማይንና፡ምድርን፡ፈጥረኻል።
16አቤቱ፥ዦሮኽን፡አዘንብልና፡ስማ፤አቤቱ፥ዐይንኽን፡ክፈትና፡እይ፤በሕያው፡አምላክ፡ላይ፡ይገዳደር፡ ዘንድ፡የላከውን፡የሰናክሬምን፡ቃል፡ስማ።
17አቤቱ፥በእውነት፡የአሶር፡ነገሥታት፡አሕዛብንና፡ምድራቸውን፡አፍርሰዋል፥
18አማልክታቸውንም፡በእሳት፡ላይ፡ጥለዋል፤የዕንጨትና፡የድንጋይ፡የሰው፡እጅ፡ሥራ፡ነበሩ፡እንጂ፡ አማልክት፡አልነበሩምና፤ስለዚህ፥አጥፍተዋቸዋል።
19እንግዲህም፡አምላካችን፡አቤቱ፥የምድር፡መንግሥታት፡ዅሉ፡አንተ፡ብቻ፡እግዚአብሔር፡አምላክ፡እንደ፡ ኾንኽ፡ያውቁ፡ዘንድ፡ከእጁ፡እንድታድነን፡እለምንኻለኹ።
20የዓሞጽም፡ልጅ፡ኢሳይያስ፡እንዲህ፡ብሎ፡ወደ፡ሕዝቅያስ፡ላካ፦የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ እንዲህ፡ይላል፦ስለአሶር፡ንጉሥ፡ስለ፡ሰናክሬም፡ወደ፡እኔ፡የለመንኸውን፡ሰምቻለኹ።
21እግዚአብሔር፡በርሱ፡ላይ፡የተናገረው፡ቃል፡ይህ፡ነው፦ድንግሊቱ፡የጽዮን፡ልጅ፡ቀላል፡ አድርጋኻለች፥በንቀትም፡ሥቃብኻለች፤የኢየሩሳሌም፡ልጅ፡በላይኽ፡ራሷን፡ነቅንቃብኻለች።
22የተገዳደርኸው፥የሰደብኸውስ፡ማን፡ነው፧ቃልኽንስ፡ከፍ፡ከፍ፡ያደረግኸው፡ዐይንኽንም፡ወደ፡ላይ፡ ያነሣኸው፡በማን፡ላይ፡ነው፧በእስራኤል፡ቅዱስ፡ላይ፡ነው።
23አንተስ፦በሠረገላዬ፡ብዛት፡ወደተራራዎች፡ከፍታ፥ወደሊባኖስ፡ጥግ፡ላይ፡ወጥቻለኹ፤ረዣዥሞቹንም፡ ዝግባዎች፡የተመረጡትንም፡ጥዶች፡እቈርጣለኹ፥ወዳገሩም፡ዳርቻና፡ወደቀርሜሎስ፡ዱር፡እገባለኹ።
24ቈፈርኹም፥እንግዳውንም፡ውሃ፡ጠጣኹ፤የተገደበውንም፡ውሃ፡ዅሉ፡በእግሬ፡ጫማ፡አደርቃለኹ፡ ብለኽ፡በመልእክተኛዎችኽ፡እጅ፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡ተገዳደርኽ።
25እኔ፡ጥንቱን፡እንደ፡ሠራኹት፥ቀድሞውንም፡እንዳደረግኹት፡አልሰማኽምን፧አኹንም፡የተመሸጉትን፡ ከተማዎች፡የፍርስራሽ፡ክምር፡እስኪኾኑ፡ድረስ፡እንድታፈርስ፡አደረግኹኽ።
26ስለዚህም፡የሚኖሩባቸው፡ሰዎች፡እጃቸው፡ዝሏል፥ደንግጠውም፡ታውከዋል፤እንደ፡ምድረ፡በዳ፡ ሣር፥እንደ፡ለምለምም፡ቡቃያ፥በሰገነትም፡ላይ፡እንዳለ፡ሣር፥ሳይሸት፡ዋግ፡እንደ፡መታውም፡እኽል፡ ኾነዋል።
27እኔ፡ግን፡መቀመጫኽንና፡መውጫኽንም፡መግቢያኽንም፥በእኔም፡ላይ፡የተቈጠኸውን፡ቍጣ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ዐውቄያለኹ።
28ቍጣኽና፡ትዕቢትኽ፡ወደ፡ዦሮዬ፡ደርሷልና፥ስለዚህ፡ስናጋዬን፡በአፍንጫኽ፥ልጓሜንም፡በከንፈርኽ፡ አደርጋለኹ፥በመጣኽበትም፡መንገድ፡እመልስኻለኹ።
29ይህም፡ምልክት፡ይኾንኻል፤በዚህ፡ዓመት፡የገቦውን፥በኹለተኛውም፡ዓመት፡ከገቦው፡የበቀለውን፡ ትበላላችኹ፤በሦስተኛውም፡ዓመት፡ትዘራላችኹ፥ታጭዱማላችኹ፥ወይንንም፡ትተክላላችኹ፥ፍሬውንም፡ ትበላላችኹ።
30ያመለጠው፡የይሁዳ፡ቤት፡ቅሬታ፡ሥሩን፡ወደ፡ታች፡ይሰዳ፟ል፥ወደ፡ላይም፡ያፈራል።
31ከኢየሩሳሌም፡ቅሬታ፡ከጽዮንም፡ተራራ፡ያመለጡት፡ይወጣሉና፤የሰራዊት፡ጌታ፡የእግዚአብሔር፡ቅንአት፡ ይህን፡ያደርጋል።
32ስለዚህም፡እግዚአብሔር፡ስለአሶር፡ንጉሥ፡እንዲህ፡ይላል፦ወደዚች፡ከተማ፡አይመጣም፥ፍላጻንም፡ አይወረውርባትም፥በጋሻም፡አይመጣባትም፥የዐፈርንም፡ድልድል፡አይደለድልባትም።
33በመጣበት፡መንገድ፡በዚያው፡ይመለሳል፥ወደዚችም፡ከተማ፡አይመጣም፥ይላል፡እግዚአብሔር።
34ስለ፡እኔም፥ስለ፡ባሪያዬም፡ስለ፡ዳዊት፡ይህችን፡ከተማ፡አድናት፡ዘንድ፡እጋርዳታለኹ።
35በዚያችም፡ሌሊት፡የእግዚአብሔር፡መልአክ፡ወጣ፥ከአሶራውያንም፡ሰፈር፡መቶ፡ሰማንያ፡ዐምስት፡ሺሕ፡ ገደለ፤ማለዳም፡በተነሡ፡ጊዜ፥እንሆ፥ዅሉ፡በድኖች፡ነበሩ።
36የአሶርም፡ንጉሥ፡ሰናክሬም፡ተነሥቶ፡ኼደ፥ተመልሶም፡በነነዌ፡ተቀመጠ።
37በአምላኩም፡በናሳራክ፡ቤት፡ሲሰግድ፡ልጆቹ፡አደራሜሌክና፡ሳራሳር፡በሰይፍ፡ገደሉት፤ወደአራራትም፡ አገር፡ኰበለሉ።ልጁም፡አሥራዶን ፡በርሱ፡ፋንታ፡ነገሠ።