1ንጉሡም፡ላከ፤የይሁዳንና፡የኢየሩሳሌምንም፡ሽማግሌዎች፡ዅሉ፡ሰበሰባቸው።
2ንጉሡም፡ወደእግዚአብሔር፡ቤት፡ወጣ፤ከርሱም፡ጋራ፡የይሁዳ፡ሰዎች፡ዅሉ፥በኢየሩሳሌምም፡የሚኖሩ፡ ዅሉ፥ካህናቱና፡ነቢያቱም፥ሕዝቡም፡ዅሉ፡ከታናሾቹ፡ዠምሮ፡እስከ፡ታላቆቹ፡ድረስ፡ ወጡ፤በእግዚአብሔርም፡ቤት፡የተገኘውን፡የቃል፡ኪዳኑን፡መጽሐፍ፡ቃል፡ዅሉ፡በዦሯቸው፡አነበበ።
3ንጉሡም፡በዐምደ፡ወርቁ፡አጠገብ፡ቆሞ፡እግዚአብሔርን፡ተከትሎ፡ይኼድ፡ዘንድ፥ትእዛዙንና፡ምስክሩንም፡ ሥርዐቱንም፡በፍጹም፡ልቡና፡በፍጹም፡ነፍሱ፡ይጠብቅ፡ዘንድ፥በዚሁም፡መጽሐፍ፡የተጻፈውን፡የቃል፡ኪዳን፡ ቃል፡ያጸና፡ዘንድ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ቃል፡ኪዳን፡አደረገ፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡ቃል፡ኪዳን፡ገቡ።
4ንጉሡም፡የካህናቱን፡አለቃ፡ኬልቅያስን፡በኹለተኛውም፡መዓርግ፡ያሉትን፡ካህናትን፡በረኛዎቹንም፡ ለበዓልና፡ለማምለኪያ፡ዐጸድ፡ለሰማይም፡ሰራዊት፡ዅሉ፡የተሠሩትን፡ዕቃዎች፡ዅሉ፡ከእግዚአብሔር፡መቅደስ፡ ያወጡ፡ዘንድ፡አዘዛቸው፤ከኢየሩሳሌምም፡ውጭ፡በቄድሮን፡ሜዳ፡አቃጠላቸው፥ዐመዱንም፡ወደ፡ቤቴል፡ ወሰደው።
5የይሁዳ፡ነገሥታትም፡በይሁዳ፡ከተማዎች፡በነበሩት፡በኰረብታው፡መስገጃዎች፡በኢየሩሳሌምም፡ዙሪያ፡ባሉ፡ መስገጃዎች፡ያጥኑ፡ዘንድ፡ያኖሯቸውን፡የጣዖቱን፡ካህናት፥ለበዓልና፡ለፀሓይ፡ለጨረቃና፡ለከዋክብት፡ ለሰማይም፡ሰራዊት፡ዅሉ፡ያጥኑ፡የነበሩትንም፡አስወገደ።
6የማምለኪያ፡ዐጸድንም፡ጣዖት፡ከእግዚአብሔር፡ቤት፡ወደኢየሩሳሌም፡ውጭ፡ወደቄድሮን፡ፈፋ፡ አወጣው፤በቄድሮንም፡ፈፋ፡አጠገብ፡አቃጠለው፥አድቆ፟ም፡ትቢያ፡አደረገው፥ትቢያውንም፡በሕዝብ፡ መቃብር፡ላይ፡ጣለው።
7ሴቶቹም፡ለማምለኪያ፡ዐጸድ፡መጋረጃ፡ይፈትሉባቸው፡የነበሩትን፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡ውስጥ፡ያሉትን፡ የሰዶማውያንን፡ቤቶች፡አፈረሰ።
8ካህናቱንም፡ዅሉ፡ከይሁዳ፡ከተማዎች፡አወጣቸው፤ከጌባም፡ዠምሮ፡እስከ፡ቤርሳቤሕ፡ድረስ፡ካህናት፡ ያጥኑበት፡የነበረውን፡የኰረብታ፡መስገጃ፡ዅሉ፡ርኩስ፡አደረገው።በከተማዪቱም፡በር፡በግራ፡በኩል፡ በነበረው፡በከተማዪቱ፡ሹም፡በኢያሱ፡በር፡መግቢያ፡አጠገብ፡የነበሩትን፡የበሮቹን፡መስገጃዎች፡አፈረሰ።
9የኰረብታው፡መስገጃዎች፡ካህናት፡ግን፡በኢየሩሳሌም፡ወዳለው፡ወደእግዚአብሔር፡መሠዊያ፡አይመጡም፡ ነበር፤ብቻ፡በወንድሞቻቸው፡መካከል፡ቂጣ፡እንጀራ፡ይበሉ፡ነበር።
10ማንም፡ሰው፡ወንድ፡ልጁን፡ወይም፡ሴት፡ልጁን፡ለሞሎክ፡በእሳት፡እንዳያሳልፍ፡በሄኖም፡ልጆች፡ሸለቆ፡ የነበረውን፡ቶፌትን፡ርኩስ፡አደረገው።
11የይሁዳም፡ነገሥታት፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡መግቢያ፡አጠገብ፡በከተማው፡አቅራቢያ፡በነበረው፡በጃን፡ ደረባው፡በናታንሜሌክ፡መኖሪያ፡አጠገብ፡ለፀሓይ፡የሰጡትን፡ፈረሶች፡አስወገደ፤የፀሓይንም፡ሠረገላዎች፡ በእሳት፡አቃጠለ።
12የይሁዳም፡ነገሥታት፡ያሠሩትን፡በአካዝ፡ቤት፡ሰገነት፡ላይ፡የነበሩትን፡መሠዊያዎች፥ምናሴም፡ያሠራውን፡ በእግዚአብሔር፡ቤት፡በኹለቱ፡ወለሎች፡ላይ፡የነበሩትን፡መሠዊያዎች፡ንጉሡ፡ አስፈረሳቸው፥አደቀቃቸውም፥ትቢያቸውንም፡በቄድሮን፡ፈፋ፡ጣለ።
13በኢየሩሳሌምም፡ፊት፡ለፊት፡በርኵሰት፡ተራራ፡ቀኝ፡የነበሩትን፥የእስራኤል፡ንጉሥ፡ሰሎሞን፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ለሲዶናውያን፡ርኵሰት፡ለዐስታሮት፡ለሞዐብም፡ርኵሰት፡ለካሞሽ፡ለዐሞንም፡ልጆች፡ርኵሰት፡ለሚልኮም፡ ያሠራቸውን፡መስገጃዎች፡ንጉሡ፡ርኩስ፡አደረገ።
14ሐውልቶቹንም፡ዅሉ፡አደቀቀ፥የማምለኪያ፡ዐጸዶቹንም፡ቈረጠ፥በስፍራቸውም፡የሙታንን፡ዐጥንት፡ ሞላበት።
15ደግሞም፡በቤቴል፡የነበረውን፡መሠዊያ፥እስራኤልንም፡ያሳተ፡የናባጥ፡ልጅ፡ኢዮርብዓም፡ያሠራውን፡ የኰረብታውን፡መስገጃ፥ይህን፡መሠዊያና፡መስገጃ፡አፈረሰ፤ድንጋዮቹንም፡ሰባበረ፥አድቆ፟ም፡ትቢያ፡ አደረገው፥የማምለኪያ፡ዐጸዱንም፡አቃጠለው።
16ኢዮስያስም፡ዘወር፡ብሎ፡በተራራው፡የነበሩትን፡መቃብሮች፡አየ፤ኢዮርብዓምም፡በበዓል፡ጊዜ፡ በመሠዊያ፡አጠገብ፡ሲቆም፡እነዚህን፡ነገሮች፡የተነባ፡የእግዚአብሔር፡ሰው፡እንደተናገረው፡እንደእግዚአብሔር፡ ቃል፥ልኮ፡ከመቃብሮቹ፡ዐጥንቶቹን፡አስወጣ፥በመሠዊያውም፡ላይ፡አቃጠላቸው፥አረከሰውም።ዘወርም፡ ብሎ፡ወደተናገረው፡ወደእግዚአብሔር፡ሰው፡መቃብር፡ዐይኖቹን፡አቅንቶ፦
17ያ፡የማየው፡የመታሰቢያ፡ምልክት፡ምንድር፡ነው፧አለ።የዚያችም፡ከተማ፡ሰዎች፦ከይሁዳ፡ወጥቶ፡ በቤቴል፡መሠዊያ፡ላይ፡ይህን፡ያደረግኸውን፡ነገር፡የተናገረው፡የእግዚአብሔር፡ሰው፡መቃብር፡ነው፡ብለው፡ ነገሩት።
18ርሱም፦ተዉት፥ማንም፡ዐጥንቱን፡አያንቀሳቅሰው፡አለ፤እነርሱም፡ከሰማርያ፡ከወጣው፡ከነቢዩ፡ዐጥንት፡ ጋራ፡ዐጥንቱን፡ተዉ።
19በሰማርያም፡ከተማዎች፡የነበሩትን፥እግዚአብሔርን፡ያስቈጡት፡ዘንድ፥የእስራኤል፡ነገሥታት፡የሠሩትን፡ የኰረብታውን፡መስገጃዎች፡ኢዮስያስ፡አስወገዳቸው፥በቤቴልም፡እንዳደረገው፡ነገር፡ዅሉ፡እንዲሁ፡ አደረገባቸው።
20በዚያም፡የነበሩትን፡የኰረብታውን፡መስገጃዎች፡ካህናት፡ዅሉ፡በመሠዊያዎቹ፡ላይ፡ ገደላቸው፥የሰዎቹንም፡ዐጥንት፡በመሠዊያዎቹ፡ላይ፡አቃጠለ።ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡ተመለሰ።
21ንጉሡም፡ሕዝቡን፡ዅሉ፦በዚህ፡በቃል፡ኪዳን፡መጽሐፍ፡እንደተጻፈው፡ለአምላካችኹ፡ለእግዚአብሔር፡ ፋሲካ፡አድርጉ፡ብሎ፡አዘዛቸው።
22እንደዚህም፡ያለ፡ፋሲካ፡በእስራኤል፡ላይ፡ይፈርዱ፡ከነበሩ፡ከመሳፍንት፡ዘመን፡ዠምሮ፡በእስራኤልና፡ በይሁዳ፡ነገሥታት፡ዘመን፡ዅሉ፡አልተፈሰከም።
23ነገር፡ግን፥በይሁዳ፡ንጉሥ፡በኢዮስያስ፡በዐሥራ፡ስምንተኛው፡ዓመት፡ይህ፡ፋሲካ፡በኢየሩሳሌም፡ ለእግዚአብሔር፡ተፈሰከ።
24ደግሞም፡ካህኑ፡ኬልቅያስ፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡ባገኘው፡መጽሐፍ፡የተጻፈውን፡የሕጉን፡ቃል፡ያጸና፡ ዘንድ፥መናፍስት፡ጠሪዎቹንና፡ጠንቋዮቹን፡ተራፊምንና፡ጣዖታትንም፡በይሁዳ፡አገርና፡በኢየሩሳሌም፡ የተገኘውን፡ርኵሰት፡ዅሉ፡ኢዮስያስ፡አስወገደ።
25እንደ፡ሙሴም፡ሕግ፡ዅሉ፡በፍጹም፡ልቡ፡በፍጹምም፡ነፍሱ፡በፍጹምም፡ኀይሉ፡ወደ፡እግዚአብሔርም፡ የተመለሰ፡እንደ፡ርሱ፡ያለ፡ንጉሥ፡ከርሱ፡አስቀድሞ፡አልነበረም፤እንደ፡ርሱም፡ያለ፡ንጉሥ፡ከርሱ፡በዃላ፡ አልተነሣም።
26ነገር፡ግን፥ምናሴ፡ስላስቈጣው፡ነገር፡ዅሉ፡እግዚአብሔር፡በይሁዳ፡ላይ፡ከነደደው፡ከታላቁ፡ቍጣው፡ ትኵሳት፡አልተመለሰም።
27እግዚአብሔርም፦እስራኤልን፡እንዳራቅኹት፡ይሁዳን፡ከፊቴ፡አርቀዋለኹ፤ይህችንም፡የመረጥዃትን፡ ከተማ፡ኢየሩሳሌምንና፦ስሜ፡በዚያ፡ይኾናል፡ያልኹትን፡ቤት፡እጥላለኹ፡አለ።
28የቀረውም፡የኢዮስያስ፡ነገር፥የሠራውም፡ሥራ፡ዅሉ፥በይሁዳ፡ነገሥታት፡ታሪክ፡መጽሐፍ፡የተጻፈ፡ አይደለምን፧ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
29በርሱም፡ዘመን፡የግብጽ፡ንጉሥ፡ፈርዖን፡ኒካዑ፡ከአሶር፡ንጉሥ፡ጋራ፡ሊጋጠም፡ወደኤፍራጥስ፡ወንዝ፡ ወጣ፤ንጉሡም፡ኢዮስያስ፡ከርሱ፡ጋራ፡ሊጋጠም፡ወጣ፤ፈርዖንም፡በተገናኘው፡ጊዜ፡በመጊዶ፡ገደለው።
30ከሞተም፡በዃላ፡ባሪያዎቹ፡በሠረገላው፡አድርገው፡ከመጊዶ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡አመጡት፥በመቃብሩም፡ ቀበሩት።የአገሩም፡ሰዎች፡የኢዮስያስን፡ልጅ፡ኢዮአክስን፡ወሰዱት፥ቀብተውም፡በአባቱ፡ፋንታ፡አነገሡት።
31ኢዮአክስም፡መንገሥ፡በዠመረ፡ጊዜ፡የኻያ፡ሦስት፡ዓመት፡ጕልማሳ፡ነበረ፤በኢየሩሳሌምም፡ሦስት፡ወር፡ ነገሠ።እናቱም፡ዐሚጣል፡ትባል፡ነበር፥ርሷም፡የልብና፡ሰው፡የኤርምያስ፡ልጅ፡ነበረች።
32አባቶቹም፡እንዳደረጉ፡ዅሉ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ክፉ፡አደረገ።
33በኢየሩሳሌምም፡እንዳይነግሥ፡ፈርዖን፡ኒካዑ፡በሐማት፡ምድር፡ባለችው፡በሪብላ፡አሰረው፤በምድሩም፡ ላይ፡መቶ፡መክሊት፡ብርና፡አንድ፡መክሊት፡ወርቅ፡ፈሰሴ፡ጣለበት።
34ፈርዖን፡ኒካዑም፡የኢዮስያስን፡ልጅ፡ኤልያቄምን፡በአባቱ፡በኢዮስያስ፡ፋንታ፡አነገሠ፥ስሙንም፡ ኢዮአቄም ፡ብሎ፡ለወጠው።ኢዮአክስንም፡ወስዶ፡ወደ፡ግብጽ፡አፈለሰው፤በዚያም፡ሞተ።
35ኢዮአቄምም፡ብሩንና፡ወርቁን፡ለፈርዖን፡ሰጠው፤እንደ፡ፈርዖንም፡ትእዛዝ፡ገንዘብ፡ይሰጥ፡ዘንድ፡ ምድሩን፡አስገበረ፤ለፈርዖን፡ኒካዑም፡ይሰጥ፡ዘንድ፡ከአገሩ፡ሕዝብ፡ዅሉ፡እንደ፡ግምጋሜው፡ብርና፡ወርቅ፡ አስከፈለ።
36ኢዮአቄምም፡መንገሥ፡በዠመረ፡ጊዜ፡የኻያ፡ዐምስት፡ዓመት፡ጕልማሳ፡ነበረ፤በኢየሩሳሌምም፡ዐሥራ፡ አንድ፡ዓመት፡ነገሠ፤እናቱም፡ዘቢዳ፡ትባል፡ነበር፤ርሷም፡የሩማ፡ሰው፡የፈዳያ፡ልጅ፡ነበረች።
37አባቶቹም፡እንዳደረጉ፡ዅሉ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ክፉ፡አደረገ።