1በይሁዳም፡ንጉሥ፡በኢዮሳፍጥ፡በዐሥራ፡ስምንተኛው፡ዓመት፡የአክአብ፡ልጅ፡ኢዮራም፡በእስራኤል፡ላይ፡ በሰማርያ፡መንገሥ፡ዠመረ፥ዐሥራ፡ኹለትም፡ዓመት፡ነገሠ።
2በእግዚአብሔርም፡ፊት፡ክፉ፡አደረገ፤ነገር፡ግን፥አባቱ፡ያሠራውን፡የበዓልን፡ሐውልት፡አርቋልና፥እንደ፡ አባቱና፡እንደ፡እናቱ፡አልነበረም።
3ነገር፡ግን፥እስራኤልን፡ባሳታቸው፡በናባጥ፡ልጅ፡በኢዮርብዓም፡ኀጢአት፡ተያዘ፤ከርሱም፡አልራቀም።
4የሞዐብም፡ንጉሥ፡ሞሳ፡ባለበጎች፡ነበረ፤ለእስራኤልም፡ንጉሥ፡የመቶ፡ሺሕ፡ጠቦትና፡የመቶ፡ሺሕ፡ አውራ፡በጎች፡ጠጕር፡ይገብርለት፡ነበር።
5አክአብም፡ከሞተ፡በዃላ፡የሞዐብ፡ንጉሥ፡በእስራኤል፡ንጉሥ፡ላይ፡ዐመፀ።
6በዚያም፡ጊዜ፡ንጉሡ፡ኢዮራም፡ከሰማርያ፡ወጥቶ፡እስራኤልን፡ዅሉ፡አሰለፈ።
7ወደይሁዳም፡ንጉሥ፡ወደ፡ኢዮሳፍጥ፦የሞዐብ፡ንጉሥ፡ዐምፆብኛልና፥ከእኔ፡ጋራ፡በሞዐብ፡ላይ፡ለሰልፍ፡ ትኼዳለኽን፧ብሎ፡ላከ።ርሱም፦እወጣለኹ፤እኔ፡እንደ፡አንተ፥ሕዝቤም፡እንደ፡ሕዝብኽ፥ፈረሶቼም፡እንደ፡ ፈረሶችኽ፡ናቸው፡አለ።
8ደግሞም፦በምን፡መንገድ፡እንኼዳለን፧አለ፤ርሱም፦በኤዶምያስ፡ምድረ፡በዳ፡መንገድ፡ብሎ፡መለሰ።
9የእስራኤል፡ንጉሥና፡የይሁዳ፡ንጉሥ፡የኤዶምያስም፡ንጉሥ፡ኼዱ፤የሰባትም፡ቀን፡መንገድ፡ ዞሩ፤ለሰራዊቱና፡ለተከተሏቸውም፡እንስሳዎች፡ውሃ፡አልተገኘም።
10የእስራኤልም፡ንጉሥ፦ወዮ! እግዚአብሔር፡በሞዐብ፡እጅ፡አሳልፎ፡ይሰጣቸው፡ዘንድ፡እነዚህን፡ሦስቱን፡ ነገሥታት፡ጠርቷልና፥ወዮ፡አለ።
11ኢዮሳፍጥም፦በርሱ፡እግዚአብሔርን፡የምንጠይቅበት፡የእግዚአብሔር፡ነቢይ፡በዚህ፡ አይገኝምን፧አለ።ከእስራኤልም፡ንጉሥ፡ባሪያዎች፡አንዱ፦በኤልያስ፡እጅ፡ላይ፡ውሃ፡ያፈስ፟፡የነበረው፡ የሣፋጥ፡ልጅ፡ኤልሳዕ፡እዚህ፡አለ፡ብሎ፡መለሰ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
12ኢዮሳፍጥም፦የእግዚአብሔር፡ቃል፡በርሱ፡ዘንድ፡ይገኛል፡አለ።የእስራኤል፡ንጉሥና፡ኢዮሳፍጥ፡ የኤዶምያስም፡ንጉሥ፡ወደ፡ርሱ፡ወረዱ።
13ኤልሳዕም፡የእስራኤልን፡ንጉሥ፦እኔ፡ከአንተ፡ጋራ፡ምን፡አለኝ፧ወዳባትኽና፡ወደእናትኽ፡ነቢያት፡ኺድ፡ አለው።የእስራኤልም፡ንጉሥ።አይደለም፥በሞዐብ፡እጅ፡ይጥላቸው፡ዘንድ፡እግዚአብሔር፡እነዚህን፡ሦስት፡ ነገሥታት፡ጠርቷል፡አለው።
14ኤልሳዕም፦በፊቱ፡የቆምኹት፡የሰራዊት፡ጌታ፡ሕያው፡እግዚአብሔርን! የይሁዳን፡ንጉሥ፡ኢዮሳፍጥን፡ ያላፈርኹ፡ብኾን፡ኖሮ፡አንተን፡ባልተመለከትኹና፡ባላየኹ፡ነበር።
15አኹንም፡ባለበገና፡አምጡልኝ፡አለ።ባለበገናውም፡በደረደረ፡ጊዜ፡የእግዚአብሔር፡እጅ፡መጣችበት፤
16እንዲህም፡አለ፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በዚህ፡ሸለቆ፡ዅሉ፡ጕድጓድ፡ቈፈሩ።
17እግዚአብሔርም፡እንዲህ፡ይላል፦ነፋስ፡አታዩም፥ዝናብም፡አታዩም፥ይህ፡ሸለቆ፡ግን፡ውሃ፡ ይሞላል፤እናንተም፡ከብቶቻችኹም፡እንስሳዎቻችኹም፡ትጠጣላችኹ።
18ይህም፡በእግዚአብሔር፡ዐይን፡ቀላል፡ነገር፡ነው፤ደግሞም፡ሞዐባውያንን፡በእጃችኹ፡አሳልፎ፡ይሰጣል።
19የተመሸጉትንና፡ያማሩትን፡ከተማዎች፡ዅሉ፡ትመታላችኹ፥የሚያፈሩትንም፡ዛፎች፡ዅሉ፡ ትቈርጣላችኹ፥የውሃውንም፡ምንጮች፡ዅሉ፡ትደፍናላችኹ፥መልካሞችንም፡ዕርሻዎች፡ዅሉ፡በድንጋይ፡ ታበላሻላችኹ።
20በነጋውም፡የቍርባን፡ጊዜ፡ሲደርስ፥እንሆ፥ውሃ፡በኤዶምያስ፡መንገድ፡መጣ፥ምድሪቱም፡ውሃ፡ሞላች።
21ሞዐባውያንም፡ዅሉ፡ነገሥታት፡ሊወጓቸው፡እንደ፡መጡ፡በሰሙ፡ጊዜ፡በወገባቸው፡ሰይፍ፡የሚታጠቁ፡ ዅሉ፡ተሰበሰቡ፤ወጥተውም፡በአገሩ፡ድንበር፡ላይ፡ቆሙ።
22ማልደውም፡ተነሡ፤ፀሓይም፡በውሃው፡ላይ፡አንጸባረቀ፥ሞዐባውያንም፡በፊታቸው፡ውሃው፡እንደ፡ደም፡ ቀልቶ፡አዩና፦ይህ፡ደም፡ነው፤
23በርግጥ፡ነገሥታት፡ርስ፡በርሳቸው፡ተዋጉ፥ርስ፡በርሳቸውም፡ተጋደሉ፤ሞዐብ፡ሆይ፥እንግዲህ፡ወደ፡ ምርኮኽ፡ኺድ፡አሉ።
24ወደእስራኤል፡ሰፈር፡በመጡ፡ጊዜ፡እስራኤላውያን፡ተነሥተው፡ሞዐባውያንን፡መቱ፥እነርሱም፡ከፊታቸው፡ ሸሹ፤ሞዐባውያንንም፡እየመቱ፡ወደ፡አገሩ፡ውስጥ፡ገቡ።
25ከተማዎችንም፡አፈረሱ፤በመልካሞቹም፡ዕርሻዎች፡ዅሉ፡ላይ፡እስኪሞሉ፡ድረስ፡እያንዳንዱ፡ሰው፡አንድ፡ አንድ፡ድንጋይ፡ይጥል፡ነበር፤የውሃውንም፡ምንጮች፡ዅሉ፡ደፈኑ፥የሚያፈሩትንም፡ዛፎች፡ዅሉ፡ ቈረጡ፤የቂርሐራሴትን፡ድንጋዮች፡ብቻ፡አስቀሩ፤ባለ፡ወንጭፎች፡ግን፡ከበ፟ው፡መቷት።
26የሞዐብም፡ንጉሥ፡ሰልፍ፡እንደ፡በረታበት፡ባየ፡ጊዜ፡ሰይፍ፡የሚመዙ፟፡ሰባት፡መቶ፡ሰዎች፡ከርሱ፡ጋራ፡ ወሰደ፥ወደኤዶምያስም፡ንጉሥ፡ያልፉ፡ዘንድ፡ሞከሩ፤አልቻሉምም።
27በዚያም፡ጊዜ፡በርሱ፡ፋንታ፡ንጉሥ፡የሚኾነውን፡የበኵር፡ልጁን፡ወስዶ፡ለሚቃጠል፡መሥዋዕት፡በቅጥሩ፡ ላይ፡አቀረበው።በእስራኤልም፡ዘንድ፡ታላቅ፡ቍጣ፡ኾነ፤ከዚያም፡ርቀው፡ወደ፡ምድራቸው፡ተመለሱ።